Connect with us

Ethiopia

ልዩነት እንዴት ውበት ይሆናል?

Published

on

ልዩነት እንዴት ውበት ይሆናል?

ልዩነት እንዴት ውበት ይሆናል? | በጸሎት ፍ. በድሬቲዩብ

ነገ ህዳር 29 ነው፡፡ ባልሳሳት ሕገመንግሥቱ የጸደቀበት 23ኛ ዓመት ነው፡፡ ይህ ቀን በፌዴሬሽን ምክርቤት ውሳኔ መሠረት የህገመንግሥት ቀን ተብሎ መከበር ከጀመረ እነሆ 12ኛ ዓመት ሞላው፡፡ ሕገመንግስቱ በዋንኛነት የብሔር ብሔረሰቦችን መብት አስጠብቋል ተብሎ በገዥው ፓርቲ ስለሚገመትና የሉዐላዊ ሥልጣን ባለቤቶች ደግሞ (በሕገመንግሥቱ መሠረት) ብሔር ብሔሰቦችና ሕዝቦች በመሆናቸው ዕለቱም የብሔር ብሔረሰቦች ቀን በሚል ሲከበር ቆይቷል፡፡ የዘንድሮውም በዓል ተረኛ አዘጋጅ በሆነው አፋር ክልል በመከበር ላይ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ሕገመንግሥት «ብሔር ብሔረሰብ እና ሕዝቦች» ብሎ ቃሉን ያስፍረው እንጂ ባለፉት 25 ዓመታት ማንነው ብሔር? ማንነው ብሔረሰብ? ማንነው ሕዝብ? ለሚለው ምላሽ መስጠት አልቻለም፡፡ ስለሆነም ሰዎች ሲፈልጉ ብሔር፣ ሲያሻቸው ብሔረሰብ በማለት እየቀላቀሉ ስሜውን ለመጠቀም ተገደዋል፡፡ እንደማሳያ ያህል ሰፊውን የኦሮሞ ሕዝብ አንዳንድ ጊዜ ብሔር፣ አንዳንዴ ደግሞ ብሔረሰብ እየተባለ ሲጠራ የምንሰማው በዚህ ምክንያት ነው፡፡

በፌዴሬሽን ምክርቤት ዕውቅና ያላቸው ከ74 በላይ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በኢትዮጵያ ውስጥ እንዳሉ ይታወቃል፡፡ ባለፉት 25 ዓመታት ግን የትኛው ብሔር፣ የትኛው ብሔረሰብ እንደሆነ አለመታወቁ እንቆቅልሽ ነው፡፡

በዚህ አጭር ምልከታ ለመዳሰስ ያሰብነው የሕገመንግስት ቀን የማክበርን ፋይዳ ነው፡፡ ባለፉት 12 ዓመታት «ልዩነታችን ውበታችን» እየተባለ ልዩነት ሲሰበክና ሲከበር ተኖረ፡፡ ብሔር ብሔረሰቦች በልዩነታቸው ውስጥ ያለውን የጠነከረ አንድነት ከማየት ይልቅ በብሔራቸው ብቻ እንዲኮሩ የተደረገበት አካሄድ በአሁኑ ወቅት እዚህም እዚያም በየምክንያቱ ለሚፈነዱ ዘር ተኮር ግጭቶች መሠረት ሆኗል ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡

እስቲ አስበው!…ዘርህን፣ ብሔርህን መርጠህ የተወለድክ ይመስል…አንተ አማራ ነህ ፣ አንተ ትግሬ ነህ፣ አንተ ወላይታ ነህ፣ አንተ ሶማሌ ነህ…እየተባልክ ጭንቅላትህን በዘር ሐረግ ስሌት እንድታንቀሳቅሰው የማድረግ የመጨረሻ ውጤቱ ምን ይመስልሃል? ይህ አካሄድ ለአክራሪ ብሔርተኞች የማርያም መንገድ ሆኗል፡፡ የእኔ ዘር ከአንተ የተሻለ ነው የሚል አስደንጋጭ አመለካከትን ወደማብቀል ሽግግር ሲደረግ በዓይናችን እየተመለከትን ነው፡፡ «ይህ ክልል የእኔ ነው፣… መጤዎች አካባቢያችንን ለቃችሁ ውጡልን፣… መጤዎች የተፈጥሮ ሐብታችንን ጎዱብን..» የሚል ይዘት ያላቸው ዘር ተኮር ቅስቀሳዎች ባለፉት 25 ዓመታት ብልጭ ድርግም ሲሉ አስተውለናል፡፡ እነዚህ አጥፊ አመለካከቶች ብሔር ተኮር የፌዴራሊዝም አደረጃጀት ፍሬው ጎመራ በሚባልበት በዚህ ወቅት ገነው መውጣታቸው የጤንነት ምልክት አይደለም፡፡

ሰሞኑን በወልድያ ከተማ ከስፖርት ጋር የተያያዘ ግጭትና አንድ ዘርን ለይቶ የማጥቃት እንቅስቃሴ ይኸው የተጠራቀመ የቆሸሸ የዘር እሳቤ ውጤት ነው፡፡
እናም ህዳር ጠብቆ በየዓመቱ «ልዩነታችን ውበታችን» እያሉ በመዘመር በዓል የማክበር ፋይዳው ሊጠና ይገባል፡፡ በሚሊየን የሚቆጠር የዕለት ጉርስ መሸፈን ያቃተው ሕዝብ ባለበት ሀገር ሚሊየን ብሮችን እየመነዘሩ ብሔር ተኮር አስተሳሰብን በሰዎች ጭንቅላት ውስጥ ማጎልመስ ከሀገሪቱ ሠላምና መረጋጋት አንጻር ያለው ፋይዳ በጥሞና ማየትና መገምገም ይገባል፡፡

በአጠቃላይ የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በዓል አንድነትን በሚያጠናክር፣ አብሮነትን አብዝቶ በሚሰብክና ወንድማማችነትን በሚያጠናክር መልክ ማክበር ካልተቻለ ከጥቅሙ ይልቅ ኪሳራው የበዛ መሆኑ አለመዘንጋት ብልህነት ይመስለኛል፡፡ DireTube

Trending

By continuing to use the site, you agree to the use of cookies. more information

The cookie settings on this website are set to "allow cookies" to give you the best browsing experience possible. If you continue to use this website without changing your cookie settings or you click "Accept" below then you are consenting to this.

Close