Connect with us

Ethiopia

የዘረኝነት በሽታ ወዴት ይወስደን ይሆን?

Published

on

የዘረኝነት በሽታ ወዴት ይወስደን ይሆን?

የዘረኝነት በሽታ ወዴት ይወስደን ይሆን? | በጸሎት ፍ. በድሬቲዩብ

ከቅርብ ግዜ ወዲህ በየአካባቢው የሚነሱ ግጭቶች መድረሻቸው የዘር ጥፋትና ፍጅት ሆኗል፡፡ የሩቁን ትተን የቅርቦቹን እናስታውስ?! በያዝነው ዓመት መጀመሪያ ላይ በአወዳይ ከጫት ንግድ ጋር ተያይዞ የተፈጠረ አለመግባባት ወደግጭት ሲዞር የዘር መልክ ለመያዝ ግዜ አልፈጀበትም፡፡ እናም ይህ ግጭት እምብዛም ባልተለመደ ሁኔታ ጥብቅ ትስስር የነበራቸውን የኦሮሞ እና የሶማሌ ሕዝቦች ጎራ ለይተው በመጨፋጨፍ ለሞት፣ ለመቁሰልና ለመፈናቀል አደጋ ዳረገ፡፡ የማይረሳ ቂምና ቁርሾንም ለትውልድ አስቀመጠ፡፡

ባለፉት ሁለት ዓመታት በኦሮሚያ ክልል በዋንኛነት ከመልካም አስተዳደር ጉድለት ጋር እንደሚያያዝ በመንግሥት በኩል በታመነ ችግር መነሻ በተከሰቱ በአንድ ዘር ላይ ያነጣጠሩ ግጭቶች ብዙ ጥፋት ደርሶ ተመልክተናል፡፡ «ከአካባቢያችን ለቃችሁ ውጡልን!» በሚሉ የተሳሳቱ የጎጠኝነት አስተሳሰብ መነሻ የባለሃብቶች ንብረት እንዲወድም የተደረገባቸው አካባቢዎችን አስተውለናል፡፡

በአማራ ክልልም አንዳንድ አካባቢዎች ተመሳሳይ ጥፋቶች ተመዝግበዋል፡፡

አሁን ደግሞ ትላንትና «ስፖርት ለወዳጅነት» የሚለው ዓለም አቀፍ መርህ ተረስቶ በወልድያ ከነማ እና በመቐሌ ከነማ በወልድያ ስታዲየም ሊያደርጉት የነበረው ጨዋታ በግጭት ምክንያት ሊቋረጥ ግድ ሆነ፡፡ ግጭቱ ሰዎችን ለሞት ከመዳረጉም በላይ ዘር የለየ የንብረት ውድመትን አስከትሏል፡፡

ይህ ቅሬታ በመቐሌ ከተማ ትላንት ሲሰማ በሁኔታው የተቆጡ ወጣቶች ባስነሱት ረብሻ አሁንም ከባድ ጉዳትን ያስከተለ ኪሳራ መድረሱን ሰምተናል፡፡

ነገሩ ለሰሚ ግራ ነው፡፡ ኢትዮጵያ እስከዛሬ በታሪክዋ ከመሳፍንታዊ አገዛዝና ሽኩቻ በዘለለ ዘር ላይ ያነጣጠረ የጥላቻ እንቅስቃሴና ግጭትን አስተናግዳ አታውቅም፡፡ እና ይህ ነገር ከየት መጣ? እያደገ የመሄዱስ ጉዳይ እንዴት ይታያል? የሚለው እጅግ አሳሳቢና የወደፊቱን የሀገሪቱን መጻኢ ዕድል የመወሰን አቅም ያለው ነው፡፡

ከኢህአዴግ ወደስልጣን ከመጣ በኃላ በስፋት የሚታየው የብሔርተኝነት አደረጃጀትና አገዛዝ ካስከተላቸው መጥፎ ሁኔታዎች አንዱና ዋናው ይህ በዘር የማስብ ጉዳይ ይመስለኛል፡፡ ገዥው ፓርቲ ኢህአዴግ «ዴሞክራሲያዊ ብሔረተኝነት» እያለ የሚያሞካሸው ብሔር ተኮር አደረጃጀት «ቆሜለታለሁ፣ ታግዬለታለሁ» የሚለውን ብሔር ብሔረሰብ በዘርና በጎሳ አሰልፎ ጦር ወደመማዘዝ ማድረሱ እንደተራ ገጠመኝ ማየት የሚቻል አይደለም፡፡ አማራ፣ ኦሮሞ፣ ትግሬ… ብሎ በብሔር ከመደራጀት ጀምሮ ሰዎች በኪሳቸው ይዘው በሚንቀሳቀሱት መታወቂያ ሳይቀር ብሔራቸው በጉልህ እንዲጻፍ መሆኑ እንደአንድ ትልቅ ችግር መታየት የጀመረው ከቅርብ ግዜ ወዲህ ነው፡፡ በኦሮምያና በሶማሌ ግጭት ተከትሎ ከጅጅጋ አካባቢ ሰዎች ተለቅመው የተባረሩት በመታወቂያቸው መሆኑን ማስታወስ ተገቢ ነው፡፡

እናም ይህ የፌዴራል ሥርዓት ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በቋንቋቸው እንዲማሩ፣ እንዲዳኙ፣ እንዲሰሩ፣ ባህልና ወጋቸውን እንዲያሳድጉ፣ እንዲጠብቁ ማድረጉ በአዎንታ መታየት የሚገባው መሆኑን በግሌ እስማማለሁ፡፡ ነገርግን ሰዎች ኢትዮጵያዊነታቸውን ጥለው በዘር፣ በጎሳ እልፍ ሲልም በጎጥና በቀበሌ እንዲያስቡ፣ እንዲለያዩ በቀጥታና በተዘዋዋሪ ሲደረጉ የነበሩ ጥረቶች ለዛሬው ኪሳራ ትልቅ መሰረት መሆኑን መዘንጋት አይገባም፡፡ ዛሬ ላይ እንደህወሐት ያሉ ታጋይ ድርጅት አዲስ አመራሮች ሳይቀር ከአንድ ጎጥ ወይንም ቀበሌ ሆን ብለው የተሰባሰቡ ቡድንተኞች አድርጎ ለመሳል የሚኬድበት ርቀት ወደድንም ጠላንም መነሻው የብሔር ፖለቲካችን የበሰበሰ አስተሳሰብና አገነባብ ውጤት ነው፡፡

የአሁኑ ጅምር እጅግ አደገኛና አገሪቱን ወደማያባራ ቀውስ የሚከት ነው፡፡ ነገሩ በዚሁ ከቀጠለ ማናችንም በሠላም ወጥተን ስለመግባታችን ምንም ዋስትና ሊኖረን አይችልም፡

እናም ይህንን የገዘፈ አገራዊ ቀውስና ችግር በአግባቡ የሚረዳ አመራር በዚህ ወቅት ያስፈልገናል፡፡ ዛሬ ኢትዮጵያዊነትን በየመድረኩ በመዘመር ወይንም በዓመት አንድ ቀን በማክበር ብቻ የሚመጣ ለውጥ የለም፡፡ ዛሬ «የፌዴራል ሥርዓታችን ዴሞክራሲያዊ ነው» በሚሉ የተሰለቹ መዝሙሮችን ሲያንቆረቁሩ በመዋል ችግሮቹ አይፈቱም፡፡ ፈጣን መፍትሔ የግድ ይላል፡፡ በቅድሚያ የፌዴራል ሥርዓቱ ጉድለቶች በጥናትና በምርምር ይለይ፡፡ ለችግሮቹም የተለያዩ አማራጭ መፍትሔዎች ሊኖሩ እንደሚችሉ ታሳቢ በማድረግ «የእኔ ብቻ መንገድ ትክክል ነው» የሚል ግትር አቋሞች ይራገፉ፡፡ ጥናትን መሠረት አድርጎ በኢትዮጵያ ጉዳይ የሚመለከታቸውን ኢትዮጵያዊያን ወገኖች ሁሉ በማሳተፍ ለውጥ እንዲመጣ ተከታታይ ሥራ ይከናወን፡፡ ይህን ማድረግ እስካልተቻለ ድረስ ዛሬ የተለኮሰው የዘረኝነት እሳት ሁላችንንም መማገዱ አይቀሬ ይሆናል፡፡ DireTube

Trending

By continuing to use the site, you agree to the use of cookies. more information

The cookie settings on this website are set to "allow cookies" to give you the best browsing experience possible. If you continue to use this website without changing your cookie settings or you click "Accept" below then you are consenting to this.

Close