Connect with us

Ethiopia

የመንግሥት ሠራተኞች አለባበስ

Published

on

የመንግሥት ሠራተኞች አለባበስ

አራት ኪሎ በሚገኝ የአንድ የመንግሥት መሥሪያ ቤት ሠራተኞች ክበብ ውስጥ ከጓደኞቼ ጋር ተገኝቻለሁ። ከጠዋቱ አራት ሰዓት ገደማ ይሆናል። ማኪያቶ አዝዘን እስኪመጣልን ድረስ እያወራን ነው። አንድ ሰው ወደ ክበቡ መጣ አለባበሱን አይቼ ተራ ዱርየ መስሎኝ ነበር። ሱሪው ከእንትኑ በታች ወርዷል። ሁለት እግሩን ወዲያና ወዲህ አራርቆ ነው የሚሄደው፤ ፀጉሩ ከማደጉ ብዛት መቀስ ነክቶት አያውቅም። ውሃም ማበጠሪያም በውስጡ አላለፈም። ልክ እንደመጣ ማስታወሻ ደብተሩን /ሲነር ላየን/ አስቀምጦ ወደ ክበቡ እጅ መታጠቢያ ሄደ።

ቧንቧውን ከፍቶ በግራ እጅ ሱሪውን ሽቅብ እየጐተተ በአንድ እጁ ፊቱን ታጥቦ ጨረሰ። ይሄ ሰውየ ወጣት ነው። በአጣብቂኝ ጂንስ ከጉልበቱ በታች ተጨናንቋል ጫማውንም አየሁት ሊስትሮ አይቶት አያውቅም። የአለባበሱ ምግባረቢስነት ሲገርመኝ ጭራሽ ከማደሪያው ወጥቶ እዚህ /ሥራ ቦታው/ ፊቱን ይታጠባል። ያውም በአራት ሰዓት። ምንነቱንና ማንነቱን ለማወቅ ወደ ጓደኛዬ ዞር ስል እሱም እንደኔው ገርሞት እያየው ነበር። ጠየቅሁት! ይሄ ወጣት ምንድን ነው? ማንነው? አልኩት። እሱም «ይሄን ጥያቄ እንደምትጠይቀኝ በእርግጠኝነት አውቄ ነበር። ለማንኛውም ወጣቱ የመንግሥት ሠራተኛ ነው» አለኝ። ይህ ሥነምግባር የጐደለው ወጣት ብዙ ጥያቄዎችን አጫረብኝ ለምሳሌ አለቃው ለሥራ (ለኢንተርቪው ወይም ለመሳተፍ) ጉዳይ ሰው መላክ ቢያስፈልገው ይህን ጋጠወጥ ሊልከው ነው? በሚሄድበት ሥራ ቦታ ለላኪው መሥሪያ ቤት የሚያላብሰው ገጽታ ለድርጅቱ ጥሩ ነው? ወይስ እሱ አለባበሱን ስላላሟላ ሌላ ሰው ተፈልጐ የጀመረውን የራሱን ኃላፊነት ትቶ በምትክ ሊላክ ነው? ለመሆኑ የመንግሥት ሠራተኞችን አለባበስ የሚመለከት መመሪያ የለም? ካለስ ለምን ተግባራዊ አልተደረገም? ይህ ጉዳይ የፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ሚኒስቴሩ ኃላፊነት አይደለምን?

የመንግሥት ሠራተኛው ሥራ ላይ በሚሆ ንበት ጊዜ እንደ መሥሪያ ቤቱ ሁኔታ ከእሱ (ከሠራ ተኛው) በሚጠበቀው መሠረት አለባበሱን አስተካክሎ መገኘት እንዳለበት ለሠራተኛው ተነግሮታል? ያውቃል? መጠነኛም ቢሆን ስለአለባበስ ደንብ ሥልጠና ተሰጥቶታል? ለመሆኑ መልካም የሥራ ላይ አለባበስ በቂና ተገቢ እንዲሆን ስለማድረግ (Dressing Decently) ምን እንደሆነ የሚያሳይ ማኑዋል ወይም ብሮሸር ወይም ሰርኩላር ተዘጋጅቷል? አሁንም ቢሆን አልዘገየንም። የኡጋንዳ ፐብሊክ ሰርቪስ መሥሪያ ስለመንግሥት ሠራተኞች አለባበስ ሥነ-ምግባር ወይም ግብረገብነት መመሪያ አውጥቶ ያሰራጨው ባለፈው ነሐሴ ወር የመጀመሪያ ሳምንት ላይ ነው። አንድ የሥራ ኃላፊም ከረቫት አላደረገም ተብሎ ከሥራና ከደመወዝ ታግዷል።

ተገቢ አለባበስ የሚባለው እንደ ሥራ መስኩ ወይም እንደ ድርጅቱ አይነት ሊለያይ ይችላል። የአንደኛ ደረጃ ተማሪዎች አለባበስ አንዱ ነው። የኮሌጅ ተማሪዎች አለባበስ ሌላ ነው፤ ዩኒፎርም ሁሉም አንድ ዓይነት ልብስ የሚለበስበት ሁኔታም አለ። ሁሉም በየራሱ ተገቢ ነው የሚለው የአለባበስ ሥርዓት አለው። የእኛ አነሳስ የመንግሥት ሠራተኞችን ብቻ የሚመለከት በመሆኑ ሁሉም አንድ ዓይነት ጨርቅ ይልበሱ አንልም። ወይም በየሥራ መደቡ ለይተን የሥራ ሂደት ማሪ …፣ የቢሮ ፀሐፊዎች … ፣ የቢሮ ኃላፊዎች … ፣ የወረዳ ወይም የክፍለ ከተማ ሠራተኞች ወዘተ እያልን የጨርቅ ቀለም እንምረጥላቸው እያልን በግለሰብ ነፃነታቸው ውስጥ ጣልቃ እንግባ አላልንም። እያልን ያለነው የሚለብሱት ልብስ የመንግሥትን መሥሪያ ቤት ደረጃ በሚመጥን ሁኔታ ይሁን የሚል ነው። የሰውነት ክፍሎች በተገቢው መንገድ መሸፈን አለባቸው (Body Parts should be covered) የመንግሥት ሠራተኞችን የአለባበስ ደረጃ ሥነምግባር /ግብረገባዊ/ ለማድረግ የሚከተሉት ነጥቦች ትኩረት ሊያገኙ ይገባል። ለምሳሌ፡-

የሴቶችን አለባበስ በሚመለከት፡-
– የደረት አካባቢ በተለይ ጡት በከፊልም ሆነ እጅግ በጥቂቱም ቢሆን መታየት የለበትም።
– ብብት መታየት የለበትም
– እጅጌ የሌለው ሸሚዝ (የላይ ልብስ) ወይም ክንድን የሚያጋልጥ ስስ ልብስ መልበስ አይፈቀድም።
– እምብርት አይታይም። ከእንብርት በታች ባሉት አካላት ላይም ብርሃን አስተላላፊ የሆኑ ስስ ቀሚሶች አይፈቀድም፤ ከፍተኛ ተረከዝ (ሂል) እና የሚጮህ ጫማ ክልክል ነው።
– የተፈጥሮ ፀጉርን ወይም ተቀጣይ (አርቴፊሻል) ፀጉሮችን እጅግ በደመቁ የቀለም ዓይነቶች በበዙበት ሁኔታ ተሠርቶ መምጣት አይፈቀድም፡-
– ከጉልበት በላይ አጭር የሆኑ ቀሚሶች አይፈቀዱም። ቀሚሶች ሁሉ ከጉልበት በታች መሆን አለባቸው። የጉልበት አካልን ከፊትም ሆነ ከበስተኋላ መታየት የለባቸውም።
– የተጋነነ ጠረን ያለው ሽቶ መቀባት አይቻልም።
– የከንፈር ቀለም በጣም የደመቀ መሆን የለበትም፤ ወይም እንደ ቫዝሊን ከመሳሰሉት በስተቀር የተቀረው ማጌጥ በሥራ ቦታ አይፈቀድም።
– የሴቶች ጥፍር ከ3 ሴንቲሜትር መብለጥ የለበትም። በቀለም መድመቅ ወይም በተለያዩ ቀለማት መቀባትም አይቻልም። ማስቲካ ማኘክ ክልክል ነው።

እነኝህ በመንግሥት የሥራ ሰዓትና ቦታ እንጂ በግላቸው ጊዜ ወይም ከሥራ ውጪ በሆኑበት ሁኔታ ራቁታቸውን አይሁኑ እንጂ እንደፈለጉ መልበስና ማጌጥ ይችላሉ።

የወንዶችን አለባበስ በተመለከተ፦
– የተጣበቀ /ታይት/ ሱሪ መልበስ አይፈቀድም፤ በወገብ ላይ የማይቆም ወደታች እየተንሸራተተ የሚወርድ፣ ስንጥቅን የሚያጋልጥ ሱሪ አይፈቀድም።
-እጅጌ የሌለው ሸሚዝ ክልክል ነው።
– ሱሪው የጨርቅ መሆን አለበት።
– ጂንስ ሱሪ ጠባብም ይሁን ሰፊ ክልክል ነው። ጂንስ የመስክ (የመዝናኛ) እንጂ የቢሮ ልብስ አይደለም። ሲጀመርማ በ1873 ለማዕድን ቆፋሪዎች ተብሎ ነበር የተሰራው።
– ለቀቅ ያለና ደረጃውን የጠበቀ ጃኬት መልበስ ይቻላል።
– መደበኛው የሥራ ልብስ ሙሉ ልብስ የጨርቅ ነው።
– ካኪ ሱሪ በመደበኛ የሥራ ሰዓት አይፈቀድም። ለዕረፍትና ለመዝናናት ወይም ሥራው እንግዳ መቀበል የማይበዛበት ከሆነ ሊለበስ ይችላል። ነገር ግን አይበረታታም፣ አይመከርም።
– የመንግሥት ሠራተኞች የፀጉር ሁኔታ ሁልጊዜም ቢሆን በአጭሩ የተከረከመ፣ በደንብ የተበጠረና ንጽህናው የተጠበቀ መሆን አለበት። ፀጉርን አንጨፍርሮ በጣት እየጠመዘዙና እየፈተሉ መገኘት ሥነ-ምግባር ወይም ግብረገብነት የጐደለው ነው።
– የወንዶች የሥራ ላይ ጫማ ጥቁር እና የቆዳ ጫማ ነው። ሌሎች የቆዳ ጫማ ቀለሞች ለመንግሥት ሥራ ፕሮቶኮል አይመጥኑም፤ አይበረታቱም።
– ሸራ ጫማ ወይም ማንኛውም ዓይነት የእንቅስቃሴ ጫማ (አዲዳስ፣ ፑማ ፣ናይኬ…) ለመንግሥት መሥሪያ ቤት አይፈቀድም።
– ነጠላ ጫማ ወይም ክፍት ጫማ በፍፁም ክልክል ነው። በእግር ህመም ምክንያት በሐኪም ትዕዛዝ ካልሆነ በቀር ነጠላ ጫማ አድርጐ መሥሪያ ቤት አይኬድም። ነውር ነው። ሲረግጡበት ከወለሉ ጋር እየተጋጨ የሚጮህ ጫማም አይፈቀድም።
– ጫማ ሁልጊዜም ቢሆን የተጠረገ መሆን አለበት። የቆሻሻ ጫማ አድርጐ ቢሮ መምጣት ያስቀስፋል።

እዚህ ላይ በአለባበስ ሥነምግባር ዙሪያ የጠቃቀስናቸው ለመንግሥት ሠራተኞች በቢሮ ሰዓታቸው ብቻ ቢከበሩ ጥሩ ነው በሚል እንጂ «የግድ መሆን አለባቸው» የምንላቸው አይደሉም። ከእነኝህ ውስጥ ሊቀነሱ ወይም ሊጨመሩ የሚችሉ ጉዳዮች ሊኖሩ ይችላል። የሚመለከተው የፐብሊክ ሰርቪስ ሚኒስቴሩ ወይም በየመሥሪያ ቤቱ ያሉ ሥራ አስፈፃሚዎች በሚመቻቸው መንገድ ለተቋማቸው እንቅስቃሴ ይመጥናል የሚሉትን የአለባበስ ሥነምግባር ሊመርጡና ሊከተሉ ይችላሉ።

ጉዳዩ የአለባበስ ሥነምግባርን የሚመለከት እንጂ የጨርቆቹን ጥራት የሚመለከት አይደለም። በጥራትማ ቢሆን ከጂንስና ከካኪ ሱሪ የሚሻል የለም፤ ጂንስን በሚመለከት በ1871 ተጀምሮ በ1873 የባለቤትነት መብት (ፓተንት) ካገኘበት ጊዜ አንስቶ እስከ ዛሬ ድረስ 144 ዓመታት ሙሉ ተወዳጅ እንደሆነ ዘልቋል። ወደፊትም ተወዳጅነቱ የሚቀንስ አይመስልም። የፈጠራው ባለመብቶች ጃኮብ ዴቪስ እና ሌቫይ ስትራውስ (Levi Strause) ናቸው። ህጋዊ የጂንስ ብራንድም ሦስት ብቻ ነው። (davis, Lee, wrangler) የተቀረው ሁሉ ከእነዚህ ብራንዶች ፈቃድ እየገዛ ወይም በፎርጅድ እያበዛ ለገበያ የሚያቀርብ ነው። ጂንስን ተወዳጅ ያደረገው ጂኖዋ (ጣሊያን) ውስጥ ይበቅል ከነበረ Jean ከሚባል የጥጥ ዓይነት የሚሰራው ዴኒም (Denim) የሚባለው ጠንካራና ለስላሳ ክር ነው። መጀመሪያ ለማዕድን አውጪዎች ናሙናዎችን በኪሳቸው ለመያዝ ሌላው የጨርቅ ሱሪ ስላልቻለላቸው ይህን አማራጭ በመምረጣቸው ነው። በጂንስ ሱሪ ላይ በየኪሱ ዳር-ዳር የተመታው ከምሱር በተጠቃሚዎቹ ጥያቄ መሠረት ነው። ጂንስ ጠንካራና ምቹ ልብስ ነው። ጥያቄው የምቾትና የጥንካሬ ጉዳይ ሳይሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ ለመንግሥት ሠራተኞች በመንግሥት የሥራ (የቢሮ) ሰዓት የማይፈቀድ መሆኑ ነው።

በሌላ በኩልም ጉዳዩ የዕድሜ ጉዳይ አለመሆኑ ነው። ሰውየው ወጣት በመሆኑ ዕድሜው ነው ጂንስ ይልበስ ወይም ከእንትኑ በታች ስንጥቁን እያሳየ ሱሪውን አስሬ ሽቅብ እየጐተተ ይጠቀም ማለት አይቻልም። እንዲያውም ወጣትነት የሚያምረው ሥነምግባር ያለው የአለባበስ ሥርዓት ሲከተል ነው። ሙሉ ልብሱን ለብሶ ከረባት አስሮ ፀጉሩን አሳጥሮና አበጥሮ ጫማውን ጠርጐና አሳምሮ ቢቀርብ ወጣቱ የበለጠ ያምራል፤ ያኮራል፤ ይከበራል። ወጣትነት መንዘላዘያ አይደለም።

የአለባበስ ሥነ-ምግባር ተጨማሪ ወጪን አይጠይቅም። የገቢ (የደመወዝ) ጭማሪን ጥያቄ አያስነሳም። የሚገዛውን ልብስ ለራሱ ለቤተሰቡና ለመሥሪያ ቤቱ ዋስትና ከልብስ አምራችና ሰፊ ድርጅቶች ጋር በመነጋገር በየወሩ ከደመወዙ በሚቀነስ ሂሳብ በዱቤ የሚያገኝበትን ሁኔታ ሊያመቻችለት ይችላል። ከዚህ በተረፈ ልብሱን ገዝቶ መልበስ የራሱ ኃላፊነት ነው።

የአለባበስ ሥነምግባር መመሪያ ያስፈልገናል፤ እስካሁን ሳለየው ቀርቼ ሊሆን ይችላል እንጂ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱና በየተቋሙ ያሉ ሥራ አስፈፃሚዎች ይህን ሳያደርጉ የሚቀሩ አይመስለኝም። ጉዳዩ የማስፈፀም ብቃት ማነስ ሊሆን ይችላል። ያዝ ለቀቅ ሊበዛበት ይችላል። አይቶ እንዳላየ ወይም በምን አገባኝ ስሜት ጐመን በጤና ዓይነት ነገር ቸልተኝነትን ሊፈጥር ይችል ይሆናል። በዚህ ሁኔታ ደግሞ የትም መድረስ አይችልም።

መጪው ዘመን የኢትዮጵያ ከፍታ የሚበሰርበት ዘመን ነው። እውነትም ነው። የአገሪቱ ከፍታ የሚረጋግጠው በብዙ መልኩ ቢሆንም ለመንግሥት ሥራ ክብር በመስጠት፤ በመመሪያ መሠረት ተግባራዊ በማድረግ የሥነ-ምግባር መርሆዎችን ለውጤት ማብቃት አለብን። ለኢትዮጵያ ከፍታ ብስራት እንሠራለን!

ግርማ ለማ  ethpress

Trending

By continuing to use the site, you agree to the use of cookies. more information

The cookie settings on this website are set to "allow cookies" to give you the best browsing experience possible. If you continue to use this website without changing your cookie settings or you click "Accept" below then you are consenting to this.

Close