Connect with us

Africa

ምክትል የማይወዱት ኢሳያስ አፈወርቂ!

Published

on

ምክትል የማይወዱት ኢሳያስ አፈወርቂ!

ምክትል የማይወዱት ኢሳያስ አፈወርቂ! | መላዕክነሽ ሽመልስ በድሬቲዩብ

ሰሞኑን የዚምቧብዌው ሰውዬ ምክትላቸውን አሰናበቱት የሚለው ዜና ግዝፍ ነስቶ ከርሟል፡፡እውነት ነው ሙጋቤ በተወዳጁ ምክትላቸው ላይ ጨክነዋል፡፡በአገሪቱ ሁለተኛ ሰው የነበሩት ኤመርሰን ማንጋግዋ ከሥልጣናቸው ይባረሩ ዘንድ ሮበርት ጋብርኤል ሙጋቤ ወስነዋል፡፡ጉዳዩ በደቡብ ምሥራቃዊው የአፍሪቃ ክፍል መወያያ መሆኑ አላበቃም፡፡የሃራሬው ሰውዬ ለዚህ ውሳኔ ያበቃቸው ምክንያት ምንም ይሁን ምን ግን አምባገነን መሪዎች የሚወስዱት እርምጃ እንደሆነ አስረጂ ሆኖ ሊቀርብ ይችላል፡፡

በርግጥ በብዙ ሥርዓቶች ውስጥ (አምባገነንም ይሁን ዴሞክራሲያዊ) ምክትል የሚባል ስልጣን (ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርም ይሁን ምክትል ፕሬዚዳንት)ያልተለመደ አይደለም፡፡በሁሉም የዓለም ማዕዘናት ጥቅም ላይ እየዋለ ያለ አሰራር ነው፡፡በአብዛኞቹ አገራት ሕጋዊነት አለው፡፡የተለያዩ ኃላፊነቶች በሕገመንገሥት፣በአዋጅ ወዘተ ይሰጡታል፡፡ምክትል ፕሬዚዳንት/መሪ/ የሌላቸው አገራት ግን (በርግጥ በቁጥር ትንሽ ናቸው)፣ወይ አምባገነን ናቸው፤አለያም ሶሻሊስት የነበሩና የሆኑ ናቸው፡፡

የሆነው ሆኖ ዚምቧብዌ ምክትል መሪ የሌላት ሌላኛዋ አፍሪቃዊት አገር ሆናለች፡፡‹ከነማን ቀጥሎ› ከተባለ መልሱ ‹ከአምባገነኑ ኢሳያስ አፈወርቂ ፣ከወታደሩ አልሲሲ (በርግጥ በግብጽ ውስጥ ምክትል ፕሬዳንትነት ሲሰራበት የኖረ ነው፡፡ከአብዮቱ በኋላ የቀረ ሆነ እንጂ)፣ከተመራጩ አምባገነን (Elective dictatorship) ፖል ካጋሜ (በነገራችን ላይ ሩዋንዳ ለመጨረሻ ጊዜ ምክትል ፕሬዚዳንት የሚባል ቦታ ያመቻቸችው ለራሱ ለካጋሜ ብቻ ነበር) ወዘተ…ቀጥሎ› የሚል ይሆናል!! በርግጥ ሁሉም ከኢሳያስ ጋር አይነጻጸሩም፡፡እርሳቸው (ኢሳያስ አፈወርቂ) የወረዳ አስተዳዳሪ እንኳ ምክትል እንዳይኖረው የሚፈልጉ ሰው ናቸው፡፡ፈርዶባቸው ምክትል አይወዱም!!

እውነት ነው ኢሳያስ አፈወርቂ ከተቃዋሚዎቻቸው እና ከኢትዮጵያ ቀጥሎ የሚጠሉት ነገር ምክትል የሚልን ቅጣይ ነው፡፡አዎ ኢሳያስ አፈወርቂ ምክትል አይወዱም፡፡እርሳቸው ሕግ አውጭም፣ሕግ አስፈጻሚም፣ሕግ ተርጓሚም ሆነው የሚመሩት ‹መንግሥት›፣ምክትል የለውም፡፡ኤርትራ ሁለተኛ ዜጋ የሆነ ሕዝብ እንጂ ሁለተኛ ፕሬዚዳንት የላትም፡፡አፍሪካዊቷ ሰሜን ኮሪያ ከኪም ጁንግ ኡን አገር ጋር ከሚያመሳስሏት ነገሮችም አንዱ ይህ ነው፡፡መዋቅራዊ ተመሳስሎ!!

ኢሳያስ አፈወርቂ የነጻይቱ ሃገር ፕሬዚዳንት ከመሆናቸው በፊት ምክትል ነበሩ፡፡የሮመዳን መሀመድ ኑር ምክትል ነበሩ፡፡አስመራን ሊቆጣጠሩ በጣም ጥቂት ጊዜ ሲቀራቸው ግን ጉባዔ እንዲጠራ አደረጉ፡፡ጠርተውም ሮመዳንን ከሊቀመንበርነት ገለል አደረጉት፡፡በርግጥ ይህንን ጉዳይ ሲከታተሉ የነበሩ ኤርትራዊያን ሮመዳን የሻዕቢያ (ኢ.ፒ.ኤል.ኤፍ) መሪ እንዳልነበረ ይሞግታሉ፡፡የድርጅቱ አድራጊ ፈጣሪ ከመጋረጃው ጀርባ የነበሩት ኢሳያስ እንጂ ሮመዳን አልነበረም ነው ነገሩ፡፡ታዲያ እርሳቸው ይህንን ያህል (ከመጋረጃው ጀርባ ሆነው) ስልጣን ከነበራቸው ሮመዳንን ለምን መሪያቸው እንዲሆን ፈለጉ የሚል ጥያቄ ሊነሳ ይችላል፡፡
መልሱ አጭር ነው፡፡

ሻዕቢ፣ጀብሃን ‹አክራሪ ሙስሊም ነው› በሚል ከደመሰሰው በኋላ በቆለኛው ኤርትራዊ በኩል(በሌላ ቋንቋ በሙስሊሙ ማሕበረሰብ ዘንድ) የነ ኢሳያስ ድርጅት (ማለትም ሻዕቢያ) የክርስቲያን ተወካይ ነው የሚለውን ቅሰቀሳ ለመከላከል ሮመዳንን ሊቀመንበር አደረገው የሚል ነው፡፡የኤርትራ ነጻነት አይቀሬ ከሆነ በኋላ ለምን ስልጣኑን ከሮመዳን ነጠቁት የሚለው ጥያቄ ቀጥሎ የሚነሳ ነው፡፡የዚህም መልስ አጭር ነው፡፡ጦርነቱ እየተገባደደ ነው፡፡ለኢሳያስ ያልተመለሰ ጥያቄ ግን አለ፡፡ሮመዳንን ሊቀመንበር አድርጎ ወደ ከተማ የሚገሰግሰው ሻዕቢያ ፣በነጻይቱ አገር ላይም ፕሬዚዳንት ሆኖ እንዳይቀጥል ወዲ አፎም ፍላጎታቸው ነው፡፡እናም ጉባኤ ጠሩበት፡፡ጉባኤውም እርሳቸውን ሊቀመንበር አድርጎ እንዲመርጥ አደረጉት፡፡ከዚያን ጊዜ ወዲህም ሕግዴፍ ምክትል ሳይኖረው ቀረ፡፡የመጀመሪያውና የመጨረሻው የሻዕቢያ ምክትል ሊቀመንበርም ኢሳያስ አፈወርቂ የተባሉት ሰው ሆኑ፡፡

እነሆ ከዚያን ጊዜ አንስቶም ኤርትራ በተባለች ምድር ምክትል የሚባል የስልጣን ቦታ ጠፋ፤ሳይመለስም ቀረ!!
አቶ ኢሳያስ ምክትል የሚልን ቦታ የሚጠሉት ለፕሬዚዳንትነት ብቻ አይደለም፡፡በየትኛውም ሚኒስቴር ውስጥ ምክትል ሚኒስትር የለም፡፡የኢኮኖሚም ሆኑ የፖለቲካ ሚኒስቴሮች አንድም ምክትል ተመድቦላቸው አያውቅም፡፡

አቶ ኢሳያስ ምክትል የሚባልን የስልጣን ቦታ የሚጠሉት ለምንድን ነው የሚለው ጥያቄ ምክንያቱ ብዙ ሊሆን ይችላል፡፡አንደኛውና ዋነኛው ግን ሰውየው ስልጣንን ጠቅልሎ የመያዝ አባዜያቸው ዘመን ተሸጋሪ ከመሆኑ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ውጭ አገር ሲሄዱ እንኳ በእርሳቸው ቦታ ተክቶ የሚሰራ ሰው እንዳይኖር አድርገው የሰሩት የፖለቲካ መዋቅር የስልጣን ጠቅላይነታቸውን የሚያመለክት ነው፡፡ሁለተኛው ምክንያት ፍርሃት ነው፡፡ብልጫ ይወሰድብኛል፣ጫና ይደረግብኛል፤ከኔ ይልቅ እርሱ ተደማጭና ተመራጭ የመሆን ዝንባሌ ካለው ለኔ አደጋ አለው የሚል ትንተና ያመጣው ሊሆን ይችላል፡፡ለማንኛውም ግን ምክትል ከሌላቸው በጣት ከሚቆጠሩ የዓለም አገራት የኢሳያስ አፈወርቂዋ ኤርትራ አንዷ ነች፡፡ DIRETUBE

Trending

By continuing to use the site, you agree to the use of cookies. more information

The cookie settings on this website are set to "allow cookies" to give you the best browsing experience possible. If you continue to use this website without changing your cookie settings or you click "Accept" below then you are consenting to this.

Close