Connect with us

Ethiopia

ሆድን በጎመን ቢደልሉት ጉልበት በዳገት ይለግማል

Published

on

ሆድን በጎመን ቢደልሉት ጉልበት በዳገት ይለግማል

ሆድን በጎመን ቢደልሉት ጉልበት በዳገት ይለግማል | አንድነት በጋሻው – ከመርሐቤቴ

አሁን ላይ የኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት እጅጉን የተከዳዱና የተናናቁ ይመስላሉ። የአራት ኪሎው መንግስት ስልጣኔ የተረጋጋ ነው ቢልም በአንድ የምርጫ ዘመን ሁለት ጊዜ መንግስት መመስረቱ ግን የተረጋጋ ስላለመሆኑ ምልክት ነው የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡

በቅርቡ ሁለት ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች የስራ መልቀቂያ አስገብተዋል።
ብዙም ሳይርቅ ሶሰት አዳዲስ ሹመቶችን ሰጥቷል፡፡ አንድ ሚኒሰትር በአራት ዓመታት ውስጥ አራት የስራ ሃላፊነቶች ላይ ተቀምጦ ነበር። ለአብነትም አቶ ከበደ ጫኔ የንግድ ሚኒስትር ከዛም የኢህአደግ ጽህፈት ቤት ሃላፊ የገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አሁን ደግሞ የፌዴራልና አርብቶ አደር ጉዳዮች ሚኒስትር ተደርገዋል፡፡

ይህ የሚያመለክተው ታዲያ መገለባበጡ የሆነ ነገር መኖሩን ቢጠቁምም ፓርቲው ደግሞ ሚስጥሩን ማውጣት አይፈልግም።እነ መላኩ ፋንታን ያጣው የገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣንም እስካሁን ተረጋግቶ የሚመራው ሰው አላገኘም።

ሀገሪቷ በርካታ ሙስናዎች የሚከወኑባት፣ የተጀመሩ ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ገንዘብና ጊዜ የማይጠናቀቁባት፣ የዜጎች መብት ታፍኗል ፍትሃዊ የሀብት ክፍፍል የለም የሚሉና ሌሎች በርካታ የህዝብ ቅሬታዎች የሚቀርቡባት ሆናለች።

ለመንግስት ሰዎች እነዚህ ጥያቄዎች ቢቀርቡም መንግስት ጥያቄዎቹ ከእውነት የራቁ ናቸው እያለ በማስተባበል ስራ ተጠምዷል።

ይልቁንም መንግስት ሀገሪቷ በልማት ጎዳና ላይ ናት፣ በተለይም ከዓለምና ከአፍሪካ በኢንቨስትመንትና በመሰረተ ልማት ዝርጋታዎች የሚስተካከላት የለም የሚል የሚሰለች አስተያየትን ይደሰኩራል።

አሁን ደግሞ ሰሞኑን የሙስና ዘመቻ ጀምሪያለሁ በማለት መካከለኛ አመራሩ ላይ ያነጣጠረ እስርን እያካሄደ ነው።

ቀደም ብሎ በሙስና አልደራደርም እናም ትላልቅ ባለስልጣናት ሳይቀሩ በቁጥጥር ስር ይውላሉ ይህ የሚሆነው ግን መረጃና ማስረጃ ከተገኘ ነው ሲል ቆይቷል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማሪያም ደሳለኝ እጅ እንቆርጣለን በማለት ሲናገሩ ቢቆዩም አሁንም ሙስና የበለጠ ሀገሪቷን እንዳትንቀሳቀስ እያደረጋት ነው።

የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ደግሞ ሌብነት ስራ ነው እስካልተያዘ ድረስ የሚል ሙስናን ሊያበረታታ የሚችል ሀሳብን መሰንዘራቸው በርካቶች በዚህ ዘርፍ እንዲሰማሩ አደረጋቸው የሚሉ በርካታ የፖለቲካ ሰዎች አሉ።

አሁን በቅርቡ ለሀገሪቷ ከፍተኛ በጀትን የሚጠይቅ ተቋምን በበላይነት ይመሩ የነበሩ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ስለመዋላቸው መንግሰት ይፋ አደርጓል።

የፌዴራል ጠቅላይ አቃቢ ህጉ ጌታቸው አምባዬ በቢሊዮን ብር የሚገመት ንብረት መንግስት ላሰበው ነገር አለመዋሉን አስታውቀዋል።ይህ እንግዲህ ፕሮጀክቶችን ያስተዳድራሉ ብሎ ኢህአዴግ የሾማቸው ቱባ ባለስልጣናት በፊርማቸው ያጠፉት ገንዘብ መሆኑ ነው ዘግይተውም ቢሆን አቶ ጌታቸው ይፋ ያደረጉት።

ለመሆኑ የሙስናውን መበራከት ማን ፈቀደው ለምንስ አገሪቷ ራቁቷን እየቀረች ለግለሰቦች ሲባል ለምን ዝም ይባላል እውነት እየተያዙ ያሉት በትክክል በሙስናው እጃቸው ያለበት ናቸው ወይስ በፖለቲካ ውስጥ የሚፈሩና የማይደፈሩ አስተያየቶችን የሚሰጡ ናቸው የሚለውን እንመለከታለን።

ሙስና በሀገሪቷ የተፈቀደ የስራ መስክ አስኪመስል ድረስ በጠራራ ጸሀይ ነው እየተከወነ ያለው።ግን ማስረጃና መረጃው ይደበቅና በስልታዊ መንገድ ይሰራል።መንግስት ደግሞ መረጃና ማስረጃ ከሌለ የበላም ቢሆን ንጹህ ነው ይለናል በመሃል ሀገሪቷ ዕዳ ከፋይና ሹመኛ ቀላቢ ሆነች።

ህብረተሰቡ መጠቆም ቢፈልግ ያንን ጥቆማ መሰረት አደርጎ የሚከታተል ነጻና ገለልተኛ ተቋም አለመኖሩ ደግሞ ሙስናን ሀ ብለው የጀመሩ ሁሉ እንዲቀጥሉበት ዕድል ሰጣቸው።

በአንድ ወገን መንግስት ሙስና ካልወደመ እያለ ቢሰብክም ይህ ግን አራት ኪሎ ሙስናን ለመዋጋት ቆርጦ መነሳቱን በትክክል አያሳይም።

ምክንያቱም የፌዴራል መንግስት ማስረጃና መረጃ ሲገኝባቸው ነው ተጠርጣሪዎችን የምይዘው ይላል ሙስና በባህሪው ደግሞ መረጃንና ማስረጃነ በማጥፋት የሚከናወንና ስልታዊ ተግባር ነው።

እናም የፌዴራል መንግስት የጸረ ሙስና ትግል እንደሚጀምርና እንደጀመረ በተደጋጋሚ ቢናገርም ህብረተሰቡን መሰረት ያላደረገ በመሆኑ በዘመቻ ብቻ የሚሰራ ስራ አስመስሎታል።

በአንድ ወቅት ህብረተሰቡ ሙስና በዝቷል ተንሰራፍቷል እያለ ቢጮህም መንግስት /ኢህአዴግ/ ራሱን የሚያስተካልና ከስህተቱ የሚማር ነው በማለት ህብረተሰቡን ችላ እያለ መጣ።
አሁን ሀገሪቷ የእዳ እንጅ የሀብት ክምችት የላትም።

10 ያባረረ አንድ አይዝም ያስባላት ስኳር
ኢትዮጵያ አቅሟን አላወቀችም እስኪባል ድረስ የምትሰራው ስራ አይታወቅም።በአንድ ወቅት 10 የስኳር ፋብሪካዎችን እንገነባለን ብለው ዕቅድ ውስጥ እንዲገባ የቀድሞው መሪ መለስ ዜናዊ ይፋ አደረጉ።
እኒህ ግለሰብ ስኳር ፋብሪካ ለመገንባትና ለማስተዳደር የሚያስፈልጉ ሁናቴዎችን ቢያስቀምጡም አሁን ላይ ግን አንዱም ፋብሪካ ስኳር ሲሰጥ አልታየም።

ይልቁንም ለስኳር ፋብሪካዎች መገንቢያ ተብሎ በብድር የተገኘው ገቢ ግለሰቦችን የሀብት ማማ ላይ አስቀመጣቸው ይላሉ ለዘርፉ የቀረቡ ምንጮች ።

አሁን ስኳር ፋብርካ ማጣት ብቻ ሳይሆን ካለ ስኳር ዕዳን እየገፈገፈች ያለች ሀገር ይዘናል።
ለዚህ ማሳያው አሁን ላይ መንግስት በቁጥጥር ስር አውያቸዋለሁ ብሎ እንደ ኑሮ ውድነት በየቀኑ ቁጥራቸው የሚጨምረው ግለሰቦችን ማንሳት ይቻላል። በርካቶቹ ከስኳር ጋር በተያያዘ በቁጥጥር ስር የዋሉ ናቸው።

አስቀድሞ ነበር መጥኖ መደቆስ እንዲሉ ኢትዮጵያ ስኳር አመርታለሁ ከዛም ወደ ውጭ ልኬ የስኳርንና የውጭ ምንዛሬን እጥረት ያከትማል ብትልም ባለስልጣኖቿ አፍንጫሽን ላሽ ብለዋታል።
እናም አሁን መንግስት ሙስና ሙስና ቢል ህዝቡ ቀድሞ ያለውን ስላልሰማ የመጣ ጦስ ነው ይላሉ ያነጋገርኳቸው የአዳማ፣ባሀርዳር፣ መቀሌና ሀዋሳ ነዋሪዎች።

ከዛ ይልቅ ለዚህ ሁሉ የሙስና መንሰራፋት መንስኤዎቹ አሁን ላይ በቁጥጥር ስር የዋሉት ግለሰቦች ብቻ ናቸው ወይ የሚለው አጠያያቂ ሆኗል። በርካቶቹ ስኳር ፕሮጀክቶቹን እንዲጓተቱ ያደረጉ ናቸው ወይስ ስኳር የላሱ ናቸው የሚል ዘና የሚያደርግ አስተያየትን እየሰጡ ናቸው።

ለዚህ ምክንያታቸው አሁን የታየዙት ግለሰቦች በመካከለኛ አመራርነት ላይ ያሉና ይህን ያህልም ከባድ ውሳኔዎችን መወሰን የማይችሉ ናቸው ይላሉ። እንዲያውም ሌሎች ጥያቄዎች እየተነሱ ናቸው።

የዚህ መነሻ ደግሞ መንግስት በቅድሚያ በሙስና የተጠረጠሩ ከፍተኛ ባለስልጣናትን፣ ደላሎችንና ባለሀብቶችን በቁጥጥር ስል አዋለ የሚለው ዜና በመሰማቱ ህብረተሰቡ የጠበቀው ምናልባትም ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች ሊሆኑ ይችላሉ ብሎ ነበር።

ግን በሙስና የተጠረጠሩ ተብሎ ይፋ ሲደረግ ብዙ የሚታወቁ ስሞች አልነበሩም።ይህ ደግሞ በርካቶች የጠበቁት ሳይህን በመቅረቱ የጸረ ሙስናው ዘመቻ ያን ያህል ውጤት አያመጣም የሚል ሆነ።

የፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ህጉ ጌታቸው አምባዬ ታዲያ ከፍተኛ አመራር ማለት ሚኒስትሮች ብቻ አይደሉም የሚል የሀ ሁ ማብራሪያን ለጋዜጠኞች ሰጡ።

ይህች ማብራሪያ ለብዙዎች የተስማማች አልሆነችም ምክንያቱም ዋናው ማብራሪያው ሳይሆን ተግባሩን መከወን ነውና።ለአብነት ብናነሳ እንኳን ስኳር ኮርፖሬሽን ላይ በየፋብርካዎቹ በየፕሮጀክትቹ በሃላፊነት ደረጃ ላይ ያሉት በቁጥጥር ስር ውለዋል።

ይሁንና እነዚህ በርካታ ጥፋቶች ሊሰሩ የሚችሉት በከፍተኛ መሪዎች ማለትም በዋና ዳይሬክተርና በምክትሎች ሊሆን ይችላል የሚሉ መላምቶች አሉ። በመሆኑም የቀድሞው የስኳር ኮርፖሬሽን ዋና ዳይሬክተሮች እንደምን ከዚህ ሁሉ ችግር ንጹህ ሆኑ ይህን ሁሉ ዝርክርክነት አለመቆጣጠራቸውስ እንደት ከደሙ ንጹህ ሊያደርጋቸው ይችላል የሚሉ ትንታኔዎች እየተሰጡ ናቸው።

ምንም አንኳን ስኳር ኮርፖሬሽንን በዋና ዳይሬክተርነት የመሩት የቀድሞ አመራሮች ተጠያቂ ይሁኑ የሚል መረጃና ማስረጃ ባይገኝም በርካታ አሻጥሮች ሲሰሩ፣ 10 ፋብርካዎች ተጀምረው አንዱም አለመሰራቱ፣ በተቋሙ ግልጸኝነት እንዳይኖር መሆኑ፣ ኮርፖሬሽኑ ስኳርን በተመለከተ የተምታቱ ምላሾችን ሲሰጥ ዝም ብለው መመልከታቸው አመራሮቹን እንደት ነጻ ሊያደርግ ይችላል በሚል የሚጠይቁ ፖለቲከኞች፣ የኢኮኖሚ ምሁራንና ሌሎችም ተበራክተዋል።

ያህ ሆነ ይህ እነዚህ የቀድሞ ዋና ዳይሬክተሮች፣ የቦርድ አመራሮችና ሌሎችም ከዚህ ሁሉ ጥፋትና ዝርክርክነት ነጻ ይሆናሉ ብሎ ማሰብ ጀልባን በአስፓልት ላይ እንደመንዳት ይቆጠራል። እናም የጸረ ሙስና ትግሉ መጀመር ያለብት የዳይሬክቶሬት መሪዎችን፣ የስራ ሂደት ባለቤቶችንና ሌሎች በመካከለኛና በጀማሪ አመራርነት ብሎም በባለሙያነት መደብ ላይ ያሉትን በመያዝ አልነበረም የሚሉ ፖለቲከኞች አሉ።

በርግጥ የፌዴራልና የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣንን በዋና ዳይሬክተርነት ሲመሩ የነበሩትና አቶ ዛይድ ወልደገብርኤልና ኢንጅነር ፍቃደ ሃይሌ በቁጥጥር ስል ውለዋል። ግን እሱም ቢሆን አጥጋቢ አይደለም። የሁለቱም ሁኔታ አንድ አይነት ነው። ሁለቱ የቀድሞ ዋና ዳይሬክተሮች ከሃላፊነታቸው ሲኑ ወደዬ ሿሚዎቻቸው ጋር በመሄድ አማካሪ የተባለን ብዙሃኑ የኢህአዴግ አመራር ከቦታው ሲነሳ የሚሰጠውን ቦታ አገኝተው ነበር ምንም እንኳን አቶ ዛይድ ወደ ካናዳ አምርተው የነበረ ቢሆንም ። ግን ሁለቱም ተይዘዋል።

አሁን እዚህ ላይም ትል ጥያቄ ይነሳል።በመጀመሪያ አመራሮቹ ከቦታቸው ሲነሱ በግልጽነት ለምን እንደተነሱ፣ ለምንስ አማካሪ እንደሚሆኑ መታወቅ ነበረበት።ይህ የሚያሳየው መንግሰት ለዜጎች ግልጽነትና ተጠያቂነትን ሰጥቻለሁ ብሎ በአደባባይ ቢለፍም፣ ቢለጥፍም ይህንን ነገር ከህዝቡ ነጥቆ የግል ምስጢር አደረገው።ያ ደግሞ ህዝቡ እንዳያውቅና በሀሉም ነገር ላይ አስተያየት እንዳይሰጥ ገድቦታል። አሁንም እስሩ የቀጠለ ሲሆን የቀድሞ የስኳር ኮርፖሬሽን ምክትል ዋና ዳይሬክተርና የገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ አለምጸሀይ ግደይም በቁጥጥር ስር ውለዋል።

ሙስናውን ማን አጠናከረው?
ሙስና በአንድ ጊዜ የሚጀመር ከዛም የሚቆም አለመሆኑን መግለጽ የአደባባየ ሀቅ ነውና ምሁር አሊያም አዋቂ አያሰኝም። ይህንን ስልታዊ ነገር ታዲያ ማስረጃና መረጃ ብሎ ማስቆም የዋህነት ነው። አሁን በኢህአዴግ የሚመራው የሃይለማሪያም ደሳለኝ መንግስት ታዲያ መረጃ ማስረጃ ካለተገኘ ማንም አይያዝም እያለ መደስኮሩ ለሙስኞች ማበረታቻና ዋስትና ይመስላል። ያማለት መንግስት ሙስናን አስተዋወቀ፣ በነጮቹ ቋንቋ ሙስናን ስፖንሰር አደረገው እንደማለት ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማሪያምም ሆኑ የቀድሞ አለቃቸው ሙስና ላይ ያደረጓቸው ንግግርች ያልተሳኩና በእግር ኳስ ቋንቋ ሀገሪቷን ነጥብ ያስጣሉ ናቸው።

አቶ መለስ በአንድ ወቅት አንድ እጃችን ታስሯል እናም ሙሰኞች አላሰራን አሉ ብለው በይፋ የሙሰኞች ጥንካሬ ከደህንነትና ከእርሳቸውም በላይ ስለመሆኑ ተናገሩ። ያኔ የኢትዮጵያን ፖለቲካ በቅርበት ይከታተሉ የነበሩ ሰዎች ሙሰኞች ከመንግስት አቅም በላይ መሆናቸውን ከፍተኛው አስፈጻሚ ተናገሩ ሲሉ ተደመጡ። ሙሰኞች ደግሞ ጀብደኝነትና ጀግንነት ስለተሰማቸው ቀጠሉበት ብለዋል።

የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ያኔ ይህን ከመናገር ከመናገር ይልቅ ለጸረ ሙስና ትግል የሚያግዙ ተቋማትንና ስርዓትን ማቋቋም ላይ ቢያተኩሩ ኖሮ የተሻለ ውጤት ይገኝ ነበር ይላሉ የፖለቲካ ተንታኞች።

በእርግጥ ሀገሪቷ ገለልተኛ የምትላቸው ተቋማት አሉ እንደ ስለ ምግባርና ጸረ ሙስና ኮሚሽን አይነት ግን ይህ ተቋም ከስነ ዜጋ መማሪያ መጽሃፍ የተሻለ ግንዛቤ ላይ ከማተኮር የዘለለ ፋይዳ የለውም ጥንካሬውንም አላሳየም በሚል በበርካቶች ይተቻል።

ሀብት ማሳወቅና ማስመዝገብ እንቁልልጭ

ኢህአዴግን ከሚያስደስቱት ስራዎች መካከል አንዱ ዘመቻ ይመስላል። ስራዎችን የሚሰራው በዘመቻ ብቻ ነው ማለት ከባድ አይሆንም። የፍትህ ሳምንት በዘመቻ፣ የጸረ ሙስና ሳምንት፣ የኤች አይቪ ሳምንት ብቻ ሁሉም ማለት ይቻላል የማይቀጥሉና ወቅታዊ ብቻ የሆኑ ናቸው።

በአንድ ወቅት በኢህአዴግ የሚመራው መንግስት የሀብት ምዝገባና ማሳወቅ ስራን እሰራለሁ ብሎ ዘመቻ ጀመረ። ያኔ ከቀድሞው የሀገሪቷ ርዕሰ ብሔር መቶ አለቃ ግርማ ወልደጊዮርጊስ ጀምሮ በየደረጃው ሁሉም ሃብቴን ላስመዘግብ ሲል ተሰማ።

እናም ሀብት ከተመዘገበ በኋላ ልክ እንደ ስሙ ሀብት የማሳወቅ ስራ ይሰራል ተብሎ መንግስት ለህዝቡ ቃል ገብቶ ነበር። ግን አሁን ላይ መንግስት ያችን ስራ የት አደረስካት ተብሎ ሲጠየቅ አይ እኔ አላልኩም የሚል ምናልባትም በህገ መንግስት ከሚተዳደር መንግስት የማይጠበቅ ክህደትን ፈጸመ።
በዚህ ሁኔታ እንግዲህ መንግስት የፌዴራል ስነ ምግባርና ጸረ ሙስና ኮሚሽንን የሙስና ወንጀልን የመመርመር ሃላፊነትን ለፌዴራል ፖሊስ አሳልፎ እንዲሰጥ ታዘዘ።

ክስ የመክሰስን ደግሞ በጌታቸው አምባዬ ለሚመራወ ጠቅላይ አቃቤ ህግ ተላልፎ የተሰጠበት ሲሆን በተቋሙ ውስጥ ይገኙ የነበሩ የምርመራ ስራዎች፣ በሙስና የተጠረጠሩ ሰዎች መዝገቦችና ሌሎች ጭምር ለፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ተሰጡበት።

ተቋሙ አሁን ያችን የምርመራ ስራ እንኳን አጥቶ በአንድ እጁ እያጨበጨበ ነው። እናም ጥርስ የሌለው አንበሳ የነበረ ተቋም ጭራሽ አንበሳነቱን ለሌላ ጥርስ አልባ አንበሳ አስረክቧል።
የዚህ ጹሁፍ አዘጋጅ በአንድ ወቅት የፌዴራል ስነ ምግባርና ጸረ ሙስና ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነርን አግኝቶ ነበር።

እናመ በአንድ ወቅት የሀብት ምዝገባና ማሳወቅ ስራ ይሰራል ተብሎ ነበር። የቀድሞውን ፕሬዚዳንት ጨምሮ መመዘግበ ተጀምሮ ነበር ሁሉም በየደረጃው ያ ነገር ይፋ የሚሆነው መቼ ነው አልዘገየም ወይ አላቸው።
አይ ለህዝብ ይፋ አይደረግም፣ ይልቁንም መረጃ ፈልጎ ተቋሙ ድረስ የመጣ ማንኛውም ግለሰብ ከመጣ ይስተናገዳል መረጃውን በግሉ እናሳውቃለን የሚል ምላሽ ሰጡ። አይ ግን እኮ ተቋሙ ቃል የገባው በዚህ ልክ አልበረም ስላቸው ንግግራችን ከዚህ በላይ መሄድ እንደሌለበት ነገሩኝ እኔም ጉዳዩን እርሳቸውን የማይመጥንና መንግስት አውቆ የሰራው ነው ብዬ ተውኩት። እዚህ ላይ አንድ ነገር ፍንትው ብሎ ይታያል። ሙስናን የፈጠሩት በየጊዜው እየተለቀሙ የሚያዙት መካከለኛ ባለስልጣናት አይደሉም። ይህ ተግባር መሰረቱን የጣለው ቀደም ብሎ በስርዓቱ ጉምቱሰ ሰዎች መሆኑን የሚያመለክቱ ናቸው።
ይታያችሁ የኢትዮጵያ ህዝብ የባለስጣናትን ሀብት ለማወቅ ከየአቅጣጫው ወደተቋሙ ሲያመራ።አናሳዝንም ወይ
ህዝቡ በተደጋጋሚ ይጠይቃል መንግስት ዝምታን ይመርጣል።
የአዲስ አበባ ቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ ዕጣ እንዲወጣ ያስደረገውን የ40/60 ቤቶች ማየት በቂ ነው።
ዕቅዱ የሚለው ባለ አንድ ፣ ባለሁለትና ባለሶስት መኝታ ቤት ይገነባል ከዚያም ለባለዕድለኞች ይተላለፋለ ነው። ግን ህዝብ ምንያመጣል በሚል አንድ መኝታ ቤት ተመዝግበው ሲቆጥቡ የነበሩትን ትቶ ላላታሰበበትና ማንም ላልተመዘገበበት 4 መኝታ ቤት ተጨንቆ መገንባት። በዚህ መሃል ታዲያ ሙስና አይኖርም ወደዳቸሁም ጠላችሁም ግልጽነትና ተጠያቂነት አለ ብሎ የሚናገር አንደበት ከዬት ይገኛል።

በሽታውን ያልተናገረ መዲሃኒት አይገኝለትም
በተለያዩ ሀገራት መንግስታት ነጻና ገለልተኛ አማካሪዎች፣ ፖሊሲ አውጭዎች፣ ተቋማትና ምክር ቤቶች አሏቸው። እነዚህ ሁሉ ገለልተኛና ነጻ የሚሆኑት በፖለቲከኞች ጫና እንዳይደረግባቸውና ተቋማቱና ግለሰቦቹ የሚሰሩት ስራ ሳይንሳዊና ችግር ፈቺ ሆኖ እንዲቀጥል ስለሚፈለግ ነው።

ይቺኑ ነገር ወደራሳችን ስናመጣ ወዲያው ትፈርሳለች። የኢትዮጵያ ገለልተኛ ተቋማት ሃላፊዎች የሚሾሙት በምክር ቤቱ፣ የሚቆጣጠራቸው ራሱ ምክር ቤቱ ነው። ምክር ቤቱ ማለት ደግሞ 100 በ100 በአንድ ፓርቲ ብቻ የተያዘ ነው። ይህ ማለት የኢፊዲሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሌላ አነጋገር የኢህአዴግ ምክር ቤት ነው ማለት ነው። ስለዘህ ምርጫ ቦርድ፣ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን፣ የስነ ምግባርና ጸረ ሙስና ኮሚሽን፣ የህዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም፣ ፍርድ ቤቶች፣ መገናኛ ብዙሃንና ሌሎችም ሙሉ በሙሉ በአስፈጻሚዎች ጫና ስር ያሉ ናቸው።

ሙስና ተሰርቷል ይቁም የመንግስት ከፍተኛ ባለስልጣናት በሙስና ተዘፍቀዋል የሚል ሪፖርትን የስነ ምግባርና ጸረ ሙስና ኮሚሽን ቢናገር የዚህ ተቋም አመራሮች አንድ ቀን ከስልጣናቸውና ወንበራቸው ጋር አይቆዩም። ስለዚህ የዚህ ተቋም አመራሮች ለሃላፊነታቸው ሲሉ ህዝቡን ሳይሆን ፓርቲውን ያገለግላሉ። ይህ ደግሞ የሞት ሞት የሆነና ሙስናን ያጎረመሰ ብሎም ያጎመራ ሆኗል ይህ ቀጣይ እንዳይህን ማን ያረጋግጥልናል
የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢው ፕሮፌሰር መርጋ በቃናን መንግስታቸው ስቶክሆልም ስዊድን የላካቸው ምርጫ ቦርድን እንዲመሩ የሾማቸው እራሱ ስለሆነ አይደለም እንዴ ብለን ብንጠረጥርስ ።

የክልሎች በጀት በአነድ ሰው ቤት
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በጀት 2 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር፣ የጋምቤላ ክልል በጀት 2 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር ፣ የአፋር ክልል በጀት 3.5 ቢሊዮን ብር ሲሆን፣ በቅርቡ በዘመቻ መልክ በቁጥጥር ስር ዋሉ የተባሉ ሙሰኞች የተገኘባቸው ገንዘብ ወይም ህበት ግን 4 ቢሊዮን 5ቢሊዮን መሆኑ ሀገር አለኝ ወይ ያሰኛል።

እናም ግለሰቦች ይህን ያህል ገንዘብን እያጠፉ እስካሁን ዝም ያላቸው ጸሀዩ መንግስታችን ለምን ይሆን ሙስናው በባለሀብቶችና በሚኒስትሮች ደረጃ እየተሰራ ነው የሚሉ ጭምጭምታዎችን አቶ ሃይለማሪያምና መንግስታቸው ለምን ዝም አሏቸው።

ትራንስፓረንስ ኢንተርናሽናል
የዓለም ሀገራትን የሙስና ደረጃ የሚያወጣው ተቋም ሀገሪቷ የሙስና ተጋላጭነትን በተመከተ በየዓመቱ ሪፖርቱን ይፋ ያደርጋል።በዚህም መሰረት ሙስናን መከላከል ባለመቻልና ተጋላጭነትን ባለመከላከል ረገድ የራሳችንን ሀገር እናገኻለን።በዚህም ኢትዮያ በከ172 ሀገራተ 108ኛ ላይ ትገኛለች።
ይህ ደግሞ ህዝቡ በመንግስት ላይ በተደጋጋሚ ያቀርበው ለነበረው ቅሬታ ምላሸ የሰጠ ይመስላል። ባለስልጣናት ከባለሀብቶች ጋር በመመሳጠር የህዝብን ሀብት መዝብረዋል እናም መንግስት ሙስናን ለመከላከል ቁርጠኛ አለመሆኑን ተናግረው ነበር።

አገር ሲታመስ አብረህ እፈስ የሚለውን ብሒል አንቀበልምና መፍትሄ ማስቀመጥ ወድጃለሁ

መፍትሄው
ኢህአዴግ ቁጭ ብል መወያየትን መምረጥና አባላቱን ብቻ ከመስማት፣ የደህንነት ሃይልን፣ ፖሊስን መከላከያንን ሌሎቹን እንደብቸኛ አማራጭ ከመቁጠር ተቆጥቦ ውይይትን ብቻ መምረጥ አለበት።
ሌላው ህገመንግስቱን ማክበር መጀመር ያለበት እርሱ መሆኑን ማወቅ።

መገናኛ ብዘሃንን፣ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ምሁራን የሚያጠኗቸውን እነደግብዓት መውሰድና መስማትን ቢለምድ በቅርብ ጊዜ የሚለወጥ ነገር ይኖራል የሚል እምነት አለኝ።

መገናኛ ብዙሃንን፣ የፍትህና የዴሞክራሲ ተቋማትን፣ ምክር ቤቶችንና ሌሎችንም ተቋማት የምር ገለልተኛ ማድረግ፣መሪን ሳይሆን መርህን ተከትሎ መስራትን ባህሉ ቢያደርግ የተሻለ ብቻ ሳይሆን የተመረጠ አገር ይኖረናል።

እንጅ ሁልጊዜ ኢህአዴግ ከዓለም አንደኛ ከአፍሪካ አንደኛ እያለ በባዶ ቦታ ገጽታን ለመገንባት መሞከር ሆድን በጎመን መደለል ነውና ይህ መቆም አለበት።

በሁሉም መስክ መወያየት ውይይቱን ወደስራ መቀየር ከተቻለ ለወሬና ገጽታን ለመገንባቱ ይደረሳል።
ከ8 ሚሊዮን በላይ ዜጎች በድርቅ እየተጎዱ፣ የእርስ በእርስ ግጭቶ እየተበራከቱ፣ ሙስና ቤቱን እየተቆጣጠረ፣ ኑሮ ጣሪያ ነክቶ ፣እዚህም እዚያም ዜጎች በመንግስት ላይ እያኮረፉ አሁንም አገራቸን በኢንቨስትመንት አንደኛ ምናምን እያሉ መኮፈስ የትም አያደርስም ከዜሮ ያስጀምረናል። DIRETUBE

 

Trending

By continuing to use the site, you agree to the use of cookies. more information

The cookie settings on this website are set to "allow cookies" to give you the best browsing experience possible. If you continue to use this website without changing your cookie settings or you click "Accept" below then you are consenting to this.

Close