Connect with us

Ethiopia

በቃሬዛ እስራኤል የገቡት የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት

Published

on

በቃሬዛ እስራኤል የገቡት የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት

በቃሬዛ እስራኤል የገቡት የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት | መላዕክነሽ ሽመልስ በድሬቲዩብ

ከተማው ተከቧል፡፡ነዋሪዎቿ ቀጥሎ የሚሆነውን ነገር እየተጠባበቁ ነው፡፡የአገሪቱን ፖለቲካ የሚከታተሉ ታዛቢያን የሚሉት ነገር አጥተዋል፡፡ከደቂቃዎች በኋላ የአህጉሪቱ መዲና የምታስተናግደው ትዕይንት የሚገመት አልሆነም፡፡ከአዲስ አበባ ሾላ፣ላምበረትና አካባቢው የሚካሄደው ኦፕሬሽን ከተጀመረ 30 ሰዓታት አልፈዋል፡፡

የአንበሳ አውቶቡሶች የጫኑትን ሕዝብ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ እያራገፉ ነው፡፡እንደገና በፍጥነት ወደ መነሻቸው ይመለሳሉ፡፡‹ባይብል› በሚል የምስጢር ሰነድ ውስጥ የተካተቱትን ተጓዦቹ በጥዲፊያ መጫኑ እንደቀጠለ ነው፡፡

ንብረትነታቸው የጽዮናዊቷ አገር የሆኑ ሄርኩለስ አውሮፕላኖች አውሮፕላን ጣቢያ የደረሰውን ሕዝብ በፍጥነት እየጫኑ ነው፡፡ አውሮፕላን ጣቢያ ውስጥ የተጣለው ድንኳን በመንግሥትና ከተማዋን በከበቧት ተቃዋሚዎች ይሁንታ ተሰጥቶታል፡፡ በውስጡ ግን ሲቪል የለበሱ ኮማንዶዎችን እንደያዘ የሚያውቁት የዘመቻው ኃላፊዎች ብቻ ናቸው፡፡ የኮማንዶዎቹ ሚና ኦፕሬሽኑን የሚያዘገይ አንዳች ነገር ቢከሰት እርምጃ መውሰድ ነው፡፡

ዘመቻውን የጀመሩት ሰዎች በሶስት አቅጣጫዎች የተሰማራ ተደራዳሪ፣ ሕቡዕ አድራጊና መንግሥታዊ ጫና የሚፈጥር ቡድን ተሰማርቷል፡፡ ከዋሽንግተንና ከኒዮርክ የተነሳው የአሜሪካው ቡድን ሁለት ተልዕኮዎች አሉት፡፡ በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ ዲፕሎማሲያዊ ጫና መፍጠርና ለኦፕሬሽኑ የሚሆን ገንዘብ ማፈላለግ!! የአዲስ አበባው ቡድን በነ ኡሪ ሉብራኒ የሚመራ ነው፡፡ይሄ ቡድን የሕቡዕና የይፋ ስራዎችን ይከውናል፡፡ በሕቡዕ የኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናትን በጉርሻ ይደልላል፤የወደፊት እጣፈንታቸውን እንደመደራደሪያ ያቀረቡለት የደሕንነት ሹማምንትም ነበሩ፡፡በግላጭ ደግሞ የሚያስፈልጉ መንግስታዊ ሰነዶችን ያዘጋጃል፡፡

ሶስተኛው ቡድን ቴልአቪቭ የሚገኝ ነው፡፡ በቀጥታ ጠቅላይ ሚኒስትር ይስሀቅ ሻሚር ይመሩታል፡፡ እያንዳንዷን እንቅስቃሴ ቢሮአቸው ቁጭ ብለው ይከታተላሉ፡፡

የአዲስ አበባው መንግሥት አጣብቂኝ ውስጥ ገብቷል፡፡አማጽያኑ ዋና ከተማዋን እንደከበቡ ናቸው፡፡የትኛውም ባለሥልጣን ከነዚህ ጠላቶቹ ሊያመልጥ የሚችልበት እድል እንደሌለው እየገባው መጥቷል፡፡በተለይ የሁኔታዎችን ፈጥኖ መለዋወጥ የሚረዱት በደሕንነት መሥሪያቤቱ ዙሪያ የተኮለኮሉ ሹማምንት ነገአቸው አሳስቧቸዋል፡፡ሥለዚህ እርምጃ ያስፈልጋል፡፡ራስን የማዳን ርምጃ! ከጠላት መንጋጋ የማምለጥ ርምጃ!!

የደኅነነቱ ምክትል ሹም እጁ ላይ ያለውን መና መጠቀም አለበት፡፡መናው ከአዲስ አበባ ወደ ቴልአቪቭ ለሚካሔደው ኦፕሬሽን ድጋፍ ማድረግ ነው፡፡የድጋፉን ደራጎት እንደማይነፍጉት መደራደር አማራጭ የሌለው ውሳኔ ሆኖ ታየው፡፡ ሹሙ ኮሎኔል ነው፡፡ሥራዎቹን በወታደራዊና ደሕንነታዊ መንግዶች መቃኘት ይችላል፡፡እርሱና ባልደረቦቹ የሚመሩት መንግሥት በወታደራዊ ፍልሚያ ተሸንፏል፡፡የቀረችው ብቸኛ ሀብት አዲስ አበባ ነች፡፡በዚች ከተማም ቢሆን ዛሬ አመሻሽ ምን እንደሚከሰት ሊተንበይ አይችልም፡፡ስለዚህ ራስንና ቤተሰብን ወደማዳን ርምጃ መሄድ አሁናዊና አንገብጋቢ ውሳኔን ይሻል፡፡

ይህንን ኦፕሬሽን የሚመሩትን እነ ኡሪ ሉብራኒን ማነጋገር ወቅቱ አስገድዷል፡፡እንደስከዛሬው ኦፕሬሽኑን በቢሮክራሲያዊ ቅደም ተከተሎች ማዘግየት አያዋጣም፡፡ ከእነርሱ ጋር ሰላማዊ ወዳጅነትና ተባባሪነት መፍጠር ብቻ የሚያዋጣ ተግባር ነው፡፡አደረገው፡፡የደህንነቱ ምክትል ሹም ያቀደውን አደረገ፡፡ ቤተሰቦቹን ወደ ቴልአቪቭ የሚያሸሹለት ከሆነ ለዚህ ኦፕሬሽን ሥኬት መንግሥታዊ ሥልጣኑን ተጠቅሞ ከጎናቸው እንደሚቆም ለእነ ኡሪ ሉብራኒ ነገራቸው፡፡ተስማሙ፡፡ቤተሰቦቹን ወደ ቴልአቪቭ ወሰዱለት፡፡እርሱን ግን በጥብቅ ክትትል ውስጥ አስገቡት፡፡

በቀጣይ በአዲስ አበባ የሚሆነው ነገር፣በኢትዮጵያ የሚከሰተው ጉድ አይታወቅም፡፡ኮሎኔሉ የደሕንነት ምክትል ሹም በአገሪቱ ውስጥ ለተፈጸሙት እኩይ ተግባራት በሙሉ ተጠያቂ ከመሆን እንደማያመልጥ ገብቶታል፡፡እናም በእርሱ ላይ ከሚመጣ አንዳች አደጋ ለመዳን እነዚህን አይሁዶች መቅረብ ብቸኛ ምርጫው ሆኗል፡፡አለቃው፣ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ራሳቸውንና ቤተሰባቸውን አሽሽተዋል፡፡እንደርሳቸው መወሰን አለበት፡፡
—-
በሒልተን ሆቴል ግቢ ውስጥ የአምባሳደሩ መኖሪያ ቤት አለ፡፡በአምባሳደር አሸር ናአም ቪላ ውስጥ የእስራኤል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባልደረቦችና የሞሳድ ባልደረቦች ከአዲስ አበባ እስከ ቴልአቪቭ የተዘረጋውን ኦፕሬሽን እየመሩ ነው፡፡በመካከላቸው አንድ ኢትዮጵያዊ አለ፡፡ሰክሯል፡፡አሁንም እየጠጣ ነው፡፡ጢንብራው ግን ዞሯል፡፡‹‹እኔ ሕይወቴ ከእስራኤል ሕዝብ ጋር ነው፤ይህ ኦፕሬሽን እንዲሳካ ቁልፍ ሚና የነበረኝ እኔ ነኝ›› እያለ በስካር አንደበቱ እየተናገረ ነው፡፡በርግጥ ሰውየው ሚናው ትንሽ አልነበረም፡፡ይህንን እነ ኡሪ ሉብራኒም አይክዱም፡፡

በእስራኤል ሒብሩ ዩኒቨርሲቲ ሶሻል ወርክ የተማረው ይህ ሰው የሂብሩ ቋንቋን ያቀላጥፋል፡፡ለኢትዮጵያው መሪ ቅርበትና የስጋ ዝምድና እንዳለው የሚነገርለት ይህ ሰው ጠንቃቃ ዲፕሎማት እንደሆነ እስራኤሎቹ ያውቃሉ፡፡ከመነሻውም ይህንን ኦፕሬሽን ለማካሔድ ከኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት የተመረጠው እርሱ ነው፡፡ለኦፕሬሽኑ ተመልምሎ ዘለግ ላሉ ጊዜያት አድካሚውን ሥራ ሰርቷል፡፡ለዚህ ውለታውም ጠቀም ያለ ጉርሻ ተሰጥቶታል፡፡

ቀጣይ እጣፈንታው አሳስቦታል፡፡ተስፋ በቆረጠ ሥሜት ውስጥ እየጠጣ ነው፡፡በአማጽያኑ በተከበበችው ከተማ ውስጥ እየኖረ ነገን ማለም አቅቶታል፡፡አስቀድሞ ከነኡሪ ሉብራኒ ጋር ባደረገው ስምምነት ቤተሰቡን ወደ እስራኤል አሽሽቷል፡፡ግራ የገባው የእርሱ ጉዳይ ነው፡፡በሁሉም ኬላዎች ላይ ማንም እንዳይወጣና እንዳይገባ እየተደረገ ያለው ቁጥጥር ለመኮብለል አላስቻለውም፡፡ምርጫው እስራኤሎቹን የሙጥኝ ማለት ሆነ!! ይህ ታዋቂ ኢትዮጵያዊ ዲፕሎማት ተናገረ፤‹‹ኡሪ ሉብራኒ፣ ከአማጽያኑ መንጋጋ አስጥልሃለሁ ብለህ የገባህልኝን ቃል እንደማታፈርስ ተስፋ አለኝ››፡፡ኡሪ ሉብራኒም መለሰ፡፡ቃል የእምነት እዳ ነው!

ኦፕሬሽኑ ተጠናቀቀ፡፡በሺህ የሚቆጠሩ ቤተእስራኤላዊያን ወደ ቅድመ-አያቶቻቸው አገር ሔደዋል፡፡ሌሊቱን ሲከናወን ያደረው ኦፕሬሽን ሰለሞን በስኬት ተጠናቅቋል፡፡የኦፕሬሽኑን መሪዎች ለመጫን c-130 ሄርኩለስ አውሮፕላን ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ጣቢያ አርፏል፡፡በሂልተን ሆቴል፣በእስራኤል ኤምባሲና በቦሌው ድንኳን ውስጥ የነበሩት እስራኤላዊያን ኮማንዶዎችና ዲፕሎማቶችም ወደ አውሮፕላኑ ወስጥ እየገቡ ናቸው፡፡

ድንገት ከኋላ ቃሬዛ የጫነ መኪና ሳይረኑን እያጮኸ መጣ፡፡ኡሪ ሉብራኒ መኪናው ወደ ውስጥ እንዲገባ ፈቀደ፡፡በኤርፖርቱ ውስጥ ለነበሩት የኢትዮጵያ የጸጥታ ኃይሎችም ስለቃሬዛው ማብራሪያ ሰጠ፡፡ታምመው ሆስፒታል የከረሙ ቤተእስራኤላዊያን እንደሆኑና ከመሞታቸው በፊት ወደ አያቶቻው አገር እንዲሄዱ የተፈለጉ ፈላሻዎች መሆናቸውን ነገራቸው፡፡ኡሪ ሉብራኒን የጸጥታ ኃይሎቹ አመኑት፡፡ቃሬዛዎቹ ገቡ፡፡

ይሁን እንጂ በሽተኛ ቤተእስራኤላዊያን የተባሉት ሰዎች እንደተባለው ፈላሻዎቸ አይደሉም፡፡በበርካታ ኬላዎችና በአውሮፕላኖች እንዳይወጡ ከታገዱ በርካታ የደርግ መንግሥት ባለሥልጣናት መካከል ሁለቱ ናቸው፡፡የደህንነቱ ምክትል ሚኒስትር ኮሎኔል መርሻ ቀጸላ እና ዲፕሎማቱ ካሳ ከበደ!! ኡሪ ሉብራኒ ቃሉን አከበረ፡፡ሁለቱንም ሹማምንት ወደ እስራኤል ወስዶ አስቀድሞ ካሸሹአቸው ቤተሰቦቻቸው ጋር ቀላቀላቸው፡፡

በ1983 ከግንቦት 18-20 ሌሊት በተካሄደውና በሺህ የሚቆጠሩ ቤተእስራኤላዊያንን ከኢትዮጵያ ባስወጣው ኦፕሬሽን ሰለሞን ወቅት፣ በቃሬዛ ያመለጡት የደርግ ሹማምንት ካሳ ከበደ (የከበደ ተሰማ ልጅ) እና የደህንነት ሚኒስትሩ ኮሎኔል ተስፋዬ ወ/ሥላሴ ምክትል የነበረው፣ ኮሎኔል መርሻ ቀጸላ ናቸው!!

DIRETUBE

Trending

By continuing to use the site, you agree to the use of cookies. more information

The cookie settings on this website are set to "allow cookies" to give you the best browsing experience possible. If you continue to use this website without changing your cookie settings or you click "Accept" below then you are consenting to this.

Close