Connect with us

Business

ኢሕአዴጎች ሆይ እመኑኝ የኤርትራ ፖሊሲያችሁ አክስሮናል፤ ኑ ሒሳብ እናወራርድ!!

Published

on

ኢሕአዴጎች ሆይ እመኑኝ የኤርትራ ፖሊሲያችሁ አክስሮናል፤ ኑ ሒሳብ እናወራርድ!!

ኢሕአዴጎች ሆይ እመኑኝ የኤርትራ ፖሊሲያችሁ አክስሮናል፤ ኑ ሒሳብ እናወራርድ!! | መላዕክነሽ ሽመልስ በድሬቲዩብ

 የ200 ሚሊዮን ዩሮው ፖለቲካ

 ኢሳያስና ሱዛን ራይስ

 የትራምፕ መንግሥትና ኢሳያስ አፈወርቂ

 ኃይለማርያም ደሳለኝና ወዲ አፎም

 50ዎቹ ጋዜጠኞችና ኢሳያስ አፈወርቂ

 የአስመራው ጉባኤና ቀጣይዋ ኤርትራ

አረቦቹ በየመን ለሚያደርጉት ውጊያ የጦር ሰፈር ከመመስረት አልፈው፣የኤርትራን ወደቦች በሊዝ ተከራይተዋል፡፡

ማርቲን ፕላውት ‹‹Understanding Eritrea›› በተሰኘው መጽሐፍ እንደተረከው የአረብ ነገሥታት (ምንም እንኳ ካታር ከኤርትራ ምድር ጓዟን ነቅላ ብትወጣም) የኤርትራን ባሕርና የብስ እንዳሻቸው እንዲፈነጩበት አቶ ኢሳያስ አፈወርቂ ይሁንታ ሰጥተዋቸዋል፡፡ወዲ አፎም ለዚህ ውለታቸውም ገንዘብና ነዳጅ በነጻ እያገኙ ናቸው፡፡

ኤርትራ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አፍሪካዊቷ ሰሜን ኮሪያ የሚለውን ስሟን በሚያሻሽል ሁኔታ ራሷን ክፍት እያደረገች ነው፡፡ባሳለፍነው ዓመት ለደቡብ ሱዳን ሕዝብ ለሚቀርብ ርዳታ ወደቧን ፈቀደች፤ በዚያው ዓመት ከ15 ዓመት ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ የአካዳሚክ ሰዎች ያደረጉት ጉባዔ ተካሔደ፡፡

በዚያ ጉባዔ ላይ በኤርትራ ምድር ባልተለመደ ሁኔታ ከፍ ያሉ ሃሳቦች የተደመጡበት (ከሰብዓዊ መብት እስከ ውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ጉዳዮችን ያስተናገደ) ነጻ ውይይት ተካሂዷል፡፡

በዚህ የዴሞክራሲን ትወራ ባቀነቀነው ጉባዔ ላይ የተሳተፉት የጆርጅ ታውን ዩኒቨርሲቲው ረዳት ፕሮፌሰር ሃሪ ቬርሆቨን እንደሚሉት አስመራ ከ15 ዓመታት ወዲህ ዓይታው የማታውቀውን ምሁራዊ ውይይት /Intellectual  Discourses/ አስተናግዳለች፡፡

ለመገናኛ ብዙሃንና ለገለልተኛ ወገኖች ዝግ የነበረችው ኤርትራ በ2015 እ.ኤ.አ. ብቻ 50 ጋዜጠኞች እንዲጎበኟት ፈቅዳለች፡፡ እንዲህ ያለው ይሁንታዋ ፣ከተገለለችበት ዓለም ጋር መልሳ ለመታረቅ ለምታደርገው ጉዞ መግቢያ በር መሆኑ አያጠራጥርም፡፡

የአስመራው አስተዳደር ባለፉት ሁለትና ሦስት ዓመታት ከምዕራቡ ዓለም ከመንግሥታት ጋር መልካም ግንኙነት ለመፍጠር ባደረገው ግንኙነት የተሻለ መስመር ውስጥ እየገባ ይመስላል፡፡ምንም እንኳ ከወራት በፊት አቶ ኢሳያስ አሜሪካን ኮንነው ለዓለም መንግሥታት ደብዳቤ ቢጽፉም ከአውሮፓ ሃገራት በኩል የይሁንታ ‹ፈቃድ› (Green Light) ዓይተዋል፡፡

በ2015 እ.ኤ.አ. የአውሮፓ ሕብረት ሁለት መቶ ሚሊዮን ዩሮ ለኤርትራ እርዳታ ሰጥቷታል፡፡ይህ ገንዘብ የሚውለው በኤርትራ ውስጥ ያለውን ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ለመከላከል ለሚሰሩ የደኅንነትና የጸጥታ ተቋማት ነው፡፡

በሌላ ቋንቋ፣የኤርትራ የደኅንነትና የመከላከያ ተቋም ራሱን የሚያደረጅበት የውጭ ምንዛሬ ከነጮቹ በእጅ አዙር አገኘ ማለት ነው፡፡ከሕብረቱ በተጨማሪ የተለያዩ አባል አገራትና የአውሮፓ የሰብዓዊ መብት ኤጀንሲዎች ከኤርትራ መንግሥት ጋር ለመተባበር ፍንጭ እያሳዩ ነው፡፡

የብሪታኒያ ዓለም አቀፍ የልማት ድርጅት (Britain Department for International Development)  የተሰኘው ግብረሰናይ ተቋም በኤርትራ ቢሮ ሊከፍት ዕቅድ እንዳለው ይፋ አድርጓል፤የጀርመን መንግሥትም ከላይ እንደተጠቀሰው ላሉ ድርጅቶች የቴክኒክ ድጋፎችን ለማድረግ ተስማምቷል፡፡

የስደተኞች ጉዳይ ጭንቅ ለሆነበት የአንጌላ መርክል አስተዳደር ብዙ ስደተኞች ለሚመጡባት ኤርትራ ከዚህም በላይ ድጋፍ ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

እነዚህ ነገሮች የሚያመለክቱት ኢትዮጵያ ኤርትራን ለማግለል የተከተለችው ፖሊሲ እየከሰመ መምጣቱን ነው፡፡‹ተመጣጣኝ ርምጃ› የሚለው ወታደራዊ አማራጭም እስካሁን ምንም ለውጥ ሳያመጣ ቀጥሏል፡፡

እናም መንግሥትን ውጤታማ አላደረገውም፡፡ይልቁንም የሰላምም ጦርነትም የለም ፖለቲካ (No War No Peace Status Quo) ለአቶ ኢሳያስ የተመቻቸው ይመስላል፡፡

አገራቸው በጦርነት ዋዜማ ላይ የምትገኝና ከኢትዮጵያም ሆነ ከሌሎች ጎረቤቶቻቸው የመወረር ሥጋት ያደረባት አድርገው የሚነገሩትን የኤርትራ ወጣት ለውትድርና እንዲመለመል ሆኖላቸዋል፡፡

ከአሜሪካ መንግሥት ጋርም የርዕዮተ-ዓለም ሽኩቻ ውስጥ የገቡ አስመስለው ስለሚተርኩና ‹‹የዋሽግተን ፖለቲከኞች ዓላማ በኢትዮጵያ መንግሥት መዳፍ ምሥራቅ አፍሪካን መቆጣጠር ነው›› የሚለውን ትወራ በየማለዳው ስለሚናገሩ ቁጥሩ ከጥቂት በላይ የሆነ የአገሬው ሰው አምኗቸው እየኖረ ነው፡፡

በዲፕሎማሲው መስክ ከኤርትራ ጋር በተያያዘ ከኢትዮጵያ ጎን በመቆም የምትታወቀው አሜሪካ አሁን አሁን ለዘብተኛ እየሆነች ይመስላል፡፡ለዚህ የተለያዩ ምክንያቶችን መዘርዘር ይቻላል፡፡

በውጭ ጉዳይና በድሃ መንግሥታት ጉዳይ ቸልተኛ የሆኑት ሪፐብሊካን ሥልጣን መያዛቸው፤ከሁሉም በላይ ለአፍሪካ ጉዳይ ዳተኛ የሆኑት ዶናልድ ትራምፕ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት መሆናቸው የኢትዮ-ኤርትራ ጉዳይ ከልዕለ ኃያሏ አገር ትኩረት እየራቀው ለመሆኑ ማሳያ ነው፡፡

በተለይ የሁለቱን አገራት ውዝግብ ከሥር መሠረቱ አንስተው የሚያውቁትና የኢሕአዴግ መንግሥትና ባለሥልጣናት ወዳጅ መሆናቸው የሚነገርላቸው ሱዛን ራይስ ከትራምፕ አሥተዳደራዊ ሥርዓት ውጭ መደረጋቸው ጉዳዩን የእርሳቸውን ያህል በኃላፊነት (With Passion) የሚይዘው ሰው ይኖራል ተብሎ አይጠበቅም፡፡

በ1990ዎቹ የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ሲካሄድ ከአሜሪካ በኩል ጉዳዩ በሽምግልና እንዲፈታ ጥረት ሲደረግ አደራዳሪ ሆነው ይሰሩ የነበሩት ቶኒ ሌክ የተባሉ ግለሰብ ነበሩ፡፡ወዲያው ግን ሱዛን ራይስ ተተክተው ጉዳዩን በትኩረት ያዙት፡፡በኋላም በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት ሚኒስትር ሆነው ከኢትዮጵያ መንግሥትና ባለሥልጣናቱ ጋር በቅርበት ሲሰሩ ቆዩ፡፡በዚህ ሒደት ውስጥ ኤርትራዊያን እንደ ራይስ የሚጠሉት አሜሪካዊ ያለ አይመስልም፡፡

የአስመራ ሰዎች ራይስ ገለልተኛ ነበሩ ብለው አያምኑም፡፡ኢትዮጵያ በኤርትራ ላይ ማዕቀብ እንዲጣል የምታደርገውን ጥረት ራይስ ተቀብለው አስተጋብተዋል የሚል ነው የኢሳያስ ልሂቃን መከራከሪያ፡፡የሆነው ሆኖ ኢትዮጵያ በኤርትራ ላይ የምትከተለው ዲፕሎማሲ ልክ እንደ ወታደራዊው አማራጭ ሁሉ  ውጤታማ አልሆነም፡፡

አረቦቹ ለኤርትራ መንግሥት ዶላር፣ነዳጅ፣የመሠረተልማት ግንባታ፣የጦርመሣሪያ ርዳታ፣ወታደራዊ ሥልጠና ወዘተ እየሰጡ ነው፡፡ማዕቀቦች በተጣሉባት አገር እንዲህ ያለ ነገር ሲፈጸም የማዕቀብ ተቆጣጣሪው አካል ዝምታን መምረጡ ርምጃው ሊነሳ ወይም ቀለል ሊል የሚችልበት ዕድል እንዳለ የሚጠቁም ነው፡፡

ኤርትራ ላይ ዓለም አቀፋዊ ማዕቀብ እንዲጣል ምክንያት የሆነው አልሸባብን የመደገፏ ነገርም አሁን ማስረጃ እንዳልተገኘለት እየተነገረ ነው፡፡ስለዚህ ኤርትራን ለማግለል በኢትዮጵያ በኩል የተሔደበት መንገድ ከዚህ በላይ የሚያስጉዝ አይመስልም፡፡ DIRETUBE

Trending

By continuing to use the site, you agree to the use of cookies. more information

The cookie settings on this website are set to "allow cookies" to give you the best browsing experience possible. If you continue to use this website without changing your cookie settings or you click "Accept" below then you are consenting to this.

Close