Connect with us

Art and Culture

ሰው ሀገር የሞተው | በያሬድ ነጋሽ

Published

on

ሰው ሀገር የሞተው  

ሰው ሀገር የሞተው  | በያሬድ ነጋሽ

ከአዲስ አበባ 110 ኪ.ሜ ላይ እርቃ በምትገኘው ወሊሶ መግቢያ ላይ በሚገኘው የጨፎ ቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስቲያን አውደ ምህረቱ ፊት ለፊት በሁለተኛው የጣልያን ወረራ ወቅት ለእናት ሀገር በጥብቅ የጀግንነት ዘብ ከቆሙ ኢትዩጵያውያን አርበኞች መካከል አንደኛው ለሆነው ደጅአዝማች ገረሱ ዱኪ መታሰቢያነት በግርማ በቆመለት ሀውልት ስር ስለ ጀግናው ህይወት የሚተርክ በእምነበረድ የታተመ ጽሁፍ በማንበብ ላይ ነበርኩ ፡፡ ጽሁፉን በማንበብ ላይ ሳለሁ ግን አንድ ዘግይተው የመጡ አዛውንት ድርጊት ቀልበን ገዛው፡፡ አዛውንቱ ወደ ጀግናው ሀውልት በመጠጋት ሀውቱ ላይ ከዛፎች ተራግፈው ያረፉትን ቅጠሎች በማንሳት ተጠምደው ነበር፡፡

እኔም ቀደም ብዬ ያላደረኩትን የምንተ እፍረቴን አንድ ሁለት ቅጠል ጎንበስ ብዬ አነሳው፡፡በዛውም ግን ስለጀግው ሀውልቱ ስር በእምነበረድ ከተጻፈው ጽሁፍ በተጨማሪ እንዲነግሩኝ ለመጠየቅ መግቢያ የሚሆነኝን ሰላምታ ሰጠኋቸው፡፡እሳቸውም ሰላምታዬን በትህትና መለሱልኝ ፡፡ወደ ቤተክርስቲያኒቱ የገባሁት በአጋጣሚ እንደሆነ ነግሬ ፤ ባለችኝ አጭር ጊዜ ስለ ጀግናው ተጨማሪ ማብራሪያ ካላቸው እንዲሰጡኝ ጠየኳቸው እና ወደ አንድ ጥላ ስር ይዘውኝ ሄዱ ፡፡አዛውንቱን እንዲነግሩኝ ለጠየኳቸው ጥያቄ በእብነበረዱ ከተጻው በላይ ከእናቱ ፣ ከአባቱ ወይንም ከሰፈርና ከትግል ጓደኞቹ እየሰማሁ እስኪመስለኝ ድረስ ተረኩልኝ፡፡ የወሬያቸው ማገባደጅ ግን እንባ እንዲያቀሩ ያስገደዳቸው ነበር፡፡

“ይሄውልህ ልጄ ቀደም ሲል የውጪ ወራሪ ባህል ፣ ወግ እና ሀይማኖት ሊያጠፋ መጥቷል በተባለ ጊዜ በሰሜን መጥቶ እንደሆን አፍንጫ ሲመታ አይን እንደሚያለቅስ ሁሉ ከደቡቡም፣ ከምእራቡም እና ከምስራቁም ፤ በምዕራብ መጣ ሲባል ጸጉርህን እሳት ነክቶህ እንደው እጅህ በውሀ እንደሚያበርድልህ ሁሉ ከሰሜኑም ከደቡቡም እና ከምስራቁም ፤ በምስራቅ መጣ ሲባል አንድ ሰው በአይምሮው ሀሳብ አሰላስሎ መናገር የፈለገ እነደሆን አንደበቱ እንደሚታዘዘው ሁሉ ከምእራቡም ፣ ከሰሜንና ከደቡቡም ፤ በደቡብ መጣ ሲባል አንድ ገበሬ ዛፍ መቁረጥ አስቦ እግሩ ዛፉ ድረስ ካልወሰደው ፤ ቢወስደው እንኳን እጁ መጥረቢያ ካልጫበጠለት እንደማይሆነው ሁላ ከሰሜን ፣ ከምእራብ እና ከምስራቅ መላው የኢትዩጵያ ህዝብ ማቄን ጨርቄን ሳይል ለእናት ሀገሩ ዘብ ለመቆም የጀግና ሞትን ሞቷል፡፡

በአደዋ እና በማይጨው ጦርነት የጠላት ጦር በትግራይ በኩል ነበር የመጣው፡፡ ይሄ ችግር ግን የትግራይ ህዝብ ብቻ አልነበረም፡፡ የእናት ሀገር እንጂ ፡፡ለዚህም ነው መላ የኢትዩጵያ ህዝብ ደሙን ከፍሎ እቺን ሀገር ለዛሬ ያሰነበተልን፡፡ የግብጽ ጦር በጉራ በኩል ሲመጣ ችግሩ የኤርትራና የአከባቢው ህዝብ ብቻ ችግር አልነበረም ፡፡ለዛም ነው መላ የኢትዩጵያ ህዝብ በአጼ ዩሀንስ ጦር ውስጥ ተካቶ ህይወቱን የሰጠው፡፡ በምስራቅ በኩል እስከ ሀረርጌ ድረስ ወረራውን በማስፋፋት ወደ ሀገራችን የገባው የሲያድባሬ ጦር አመጣጡ በሱማሌ እና በኦሮሚያ በኩል ነበር፡፡ ይሄም ችግር ግን የሶማሌውና የኦሮሞ ህዝብ ብቻ አልነበረም ፡፡የእናት ሀገር እንጂ፡፡በዚህም ምክንያት በርካታ የኢትዩጵያ ህዝብ ህይወቱን ለሀገሩ ገብሯል፡፡አየህ ኢትዩጵውያን አንዳችን በአንዳችን የደም ውለታ ላንለያይ ተሳስረናል፡፡

ልጄ አሁን ላይ ግን ኢትዩጵያ ከምትዋሰናቸው ጎረቤት ሀገራት ድንበር በተጨማሪ ለጓዳ ጎድጓዳዋ ሁሉ ድንበር አበጅታለች አሉ፡፡አረ እንደውም ጓዳዎቿም የአንተ ሀገር ወዲያ የእኔ ሀገር ወዲህ ብለው ጦር ሰብቀዋ አሉ ፤ የዚህ አከባቢ ሰውና የዚህ አከባቢን ቋንቋ ካልተናገርክ ስራም የሚቀጥርህ የለም ሲሉም ሰማሁ፡፡ልጄ በአደዋ በማይጨው ፣ በሀረርጌው እና በሌሉቹም የሀገሪቷ ክልሎች ላይ ከውጪ ወራሪ ጋር በተደረጉ ጦርነቶች ወቅት ወረራው የተፈጸመበት ቦታ የትውልድ መንደራቸው ባይሆንም እናት ሀገሬ ብለው ህይወታቸውን የሰጡ ጀግኖች እናት ዛሬ ላይ ብትኖር ምን ብላ እንደምታለቅስ ታውቃለህ?” ብለው ጠየቁኝ ፡፡ እኔም እኔ እንጃ የሚል ምላሽ በጭንቅላቴ ሰጧቸው፡፡ “ሰው ሀገር የሞተው እያለች ታለቅስ ነበር ፡፡ምክንያቱም ዛሬ ላይ ሀገሩ የትውልድ መንደሩ ነበራ”፡፡ “አሁን ይሄ ጀግና” አሉኝ ወደ ደጅአዝማች ገረሱ ዱኪ ሀውልት እየጠቆሙኝ ∷ “ጦሩን ማንሳት የነበረበት የጠላት ጦር ትግራይን አጋይቶ ፣ ወሎን አፈራርሶ እና ሸዋን አንድዶ ወሊሶ የገባ እለት ነበር፡፡ምክንያቱም ሀገሩ የትውልድ ስፍራው ስለነበር” እያሉኝ አይናቸው በእናባ ሞላ፡፡ እኔም የእኚህን አዛውንት እንባ ለሀገሪቷ የራሄልን እንባ ያድርግላት እያልኩ አንድ ትውስታ በአይምሮዬ ተከሰተ፡፡

በእኔ እድሜ ሀገራችን የገጠማት ጦርነት የኢትዩ-ኤርትራ ጦርነት ብቸኛው ነበር፡፡የመጨረሻዋም እንዲሆን እመኛለሁ‼፡፡ በዚህ ጦርነት ወቅት በተወለድኩበት አዲስ አበባ . . . ልደታ አከባቢ በቅጽል ስሙ ሞሮኮ ተብሎ የሚጠራ የሰፈሬ ልጅ ሀገር ተወሮ እጅ እግሬን አጣጥፌ አልቀመጥም ብሎ በመዝመት ውድ ህይወቱን በጀግንነት እንደከፈለ አውቃለሁ፡፡እንደ አዛውቱ ገለጻ የሰፈሬ ልጅ ሞሮኮ ከመዝመቱ በፊት የጠላት ጦር የአዲስ አበባ መግቢያ የሆነችው አያት አከባቢ እስኪደርስ ሊታገስ ሲገባው ሰው ሀገር እንደሞተ ተሰማኝ፡፡ነብስ ይማር‼!

አዛውንቱን ከተለየው በኋላ ግን አንድ ስጋት ውስጤ ተጫረ ፡፡ይሄውም አሁን ላይ የጠላት ጦረ በሰሜን ወይንም በደቡብ ወይንም በምስራቅ ወይንም ደግሞ በምዕራብ መጣ ቢባል ከአከባቢው ውጪ ያለን የሀገሪቷ ልጆች ይበለው የሚል ምላሽ እንዳንሰጥ ፍርሀት ነገሰብኝ፡፡ DIRETUBE

Trending

By continuing to use the site, you agree to the use of cookies. more information

The cookie settings on this website are set to "allow cookies" to give you the best browsing experience possible. If you continue to use this website without changing your cookie settings or you click "Accept" below then you are consenting to this.

Close