Connect with us

Art and Culture

ሃይ ጋይስ! እንዴት ናችሁ? አሳዬ ደርቤ

Published

on

ሃይ ጋይስ! እንዴት ናችሁ? አሳዬ ደርቤ

እንኳን ከዘመነ-ምንትስ ወደ ዘመነ-ሐዲስ (ቴዲ-አፍሮ መዳበሉ ሳይረሳ) በሰላም አሸጋገራችሁ፡፡

በአዲሱ ዓመት መንግስት ከቴዲ አፍሮ አናት ላይ ተንሸራቶ… በጥብስ ፈንታ ጮማ፣ ጮማ ርዕስ እንዲሰጠንና ቴዲ አፍሮም ጣፋጭ ስራዎቹን በዓላት ጋር ባልተዳበለ መልኩ እየለቀቀ ከአዘቦት ድብርታችን እንዲታደገን እመኛለሁ፡፡

ሆኖም ግን ይሄ ምኞቴ በእናንተም በኩል ሆነ በባለቤቶቹ ዘንድ ተቀባይነትን የማያገኝ ከሆነ… እንደተለመደው ሁላ ‹ሰለቸኝና ደከመኝ› ሳልል መንግስትን የሚነቅፉ፣ ቴዲ-አፍሮን የሚደግፉ ጽሁፎቼን በግፌስቡክ ድግዳዬ ላይ ከመለጠፍም ባለፈ… እስካሁን በዚህ ጉዳይ ላይ በ365 ቀናት የጻፍኳቸውን 365 ጽሑፎች በማሰባሰብ ‹‹መንግስት ሲምስ- ቴዲ አፍሮ አፈር ሲያለብስ›› በሚል መጠሪያ መጽሐፍ ለማሳተም የምገደድ መሆኔን ተናግሬና አንገቴን ቀብሬ ወደ ቀጣዩ ሃሳቤ ልግባ!
.
ትናንት የሆነች የኢቢሲ ጋዜጠኛ ወደ ቤተ-መንግስት አምርታ ጠቅላያችን ጋር ያደረገችውን ኢንተርቪው አያችሁት? የጋዜጠኛዋን ነጻነትና ድፍረት’ስ ስታዩ ምን ተሰማችሁ? ‹‹መለስ ያላየው ጉድ!›› አላላችሁም?

ከቤተ- መንግስት ወደ እኔ ቤት ስወስዳችሁ ጓዳዬ ውስጥ ለሚቀጥለው በዓል የተቀመጡ ስድስት የአውራ-ዶሮ ብልቶች ልክ እንደ ኮቴ በጥንቃቄ ተሰቅለው ማየታችሁ አይቀርም፡፡ (ወደ ፊት ደግሞ አራጁ በገመድ መሰቀሉን የምትሰሙበት አውደ-ዓመት ይኖር ይሆናል፡፡)
‹‹ከመቼ ወዲህ ነው የዶሮ ስጋ ቋንጣ መሆን የጀመረው?›› የሚል ጥያቄ ለምታነሱ ሰዎች የምሰጠው ደም ፍላታም መልስ ‹‹ከመቼ ወዲህ ነው ዶሮ’ስ ስድስት መቶ ብር መሸጥ የጀመረው?›› የሚል ይሆናል፡፡

እንደውም ድሮ አባቶቻችን ትልቅ በግና ፍየል ሲያርዱ ቆዳውን አጎዛ በማድረግ ሳሎናቸው ግድግዳ ላይ በመስቀል ታላቅነታቸውን እንደሚገልጹት ሁላ… እኔም የዶሮዬን ቆዳ ከዩኒቨርስቲ መመረቄን የሚገልጽ ፎቶዬን ሳስቀምጥበት በነበረው ፍሬም ውስጥ በማኖር ሳሎኔ ውስጥ ሰቅዬዋለሁ፡፡ (መቼም የአባቴ የበግ አጎዛ የእኔን የዶሮ አጎዛ በጸጉር እንጂ በብር ሊበልጠው አይችልም፡፡)

ከአጎዛው ወደ ስጋው ስመልሳችሁ በስድስት መቶ ብር የተገዛን ዶሮ በአንድ አውዳመትና በአንድ ድስት አቁላልቶ መብላቱ ‹‹ጡር›› የሚያመጣ ስለመሰለኝ ስድስቱን ብልት ከስድስት ኪሎ ሽንኩርት ጋር የሚቁላለበትን አዲስ አሰራር ተግባራዊ በማድረግ ዘመን መለወጫን በደማቅ ሁኔታ ላሳልፈው ችያለሁ፡፡

መቼስ አዲስ ዓመት በመጣ ቁጥር… ሰውነት እየኮሰመነ፣ እንስሳነት እየገዘፈ የሚመጣ ከሆነ፤ ልጆች ካሉት ሰው ይልቅ በጎች ያሉት ሰው ‹‹‹አንቱ›› የሚባል ከሆነ፤ እንስሳውን የሚያደልብ፣ እረኛውን የሚያስርብ ዘመን ከፊታችን በተደቀነ ቁጥር…. ከወቅቱ ጋር ራሳችንን ለማቆየት አሰራራችን ካላሻሻልን፣ ፍላጎታችንን ካልገደልን በሕይወት መሰንበት የሚቻል አልሆነም፡፡ (ወይም ደግሞ እንስሳትን በሸኮናቸው ሳይሆን በስጋቸው የሚመዝን ቻይና-ሰራሽ መነጽር ዓይናችን ላይ ማስገጠም ይኖርብናል፡፡)

ሆኖም ግን ‹መንግስት›  በእያንዳንዱ ዘመን ሰውነታችንን ከማራከስም አልፎ….
‹‹ስድስት ወር ለሞላው ብላቴና ህጻን፣
ፈጭተው ይመግቡት ስጋና እንቁላሉን›› እያለ ከአውሮፓ መድረክ ላይ የኮረጀውን የሸክስፒር ቀልድ በቴሌቪዥናችን መቀባጠሩን የማያቆም ከሆነ የአዲሱ ዓመት

እቅዳችን የመነመኑ ብላቴናዎቻችንን ከእነአጥሚታቸው ወደ አደባባይ በመውጣት ተቃውሟችንንና ቁጣችንን መግለጽ ይሆናል፡፡

እስከዚያው ግን በበዓሉ ምሽት ሽንኩርቴን በልቼና ጆሊ-ጁሴን ጠጥቼ በጻፍኳት የድሮ-ስርዓት ናፋቂ ግጥሜ ልሰናበታችሁ፡፡
የድሮዉን እርጎ ያለፈ ቀን ቋንጣ፤
በልቼ፣ ጠጥቼ ጎኔ ቢያጠረቃ፤
ሰዉ ችቦ ለኩሶ…
ለቅዱስ ዮሃንስ- ለአዲስ ቀን ሲወጣ፤
እባክህ ጌታዬ….
ለኔ ለብቻዬ- አሮጌ ቀን አምጣ!

DIRETUBE

Trending

By continuing to use the site, you agree to the use of cookies. more information

The cookie settings on this website are set to "allow cookies" to give you the best browsing experience possible. If you continue to use this website without changing your cookie settings or you click "Accept" below then you are consenting to this.

Close