Connect with us

Art and Culture

ከደብረ ሊባኖስ ገዳም የ“ውሻ ገደል” መንደር ከ2ሺ በላይ ነዋሪዎች ይነሣሉ

Published

on

ከደብረ ሊባኖስ ገዳም የ“ውሻ ገደል” መንደር ከ2ሺ በላይ ነዋሪዎች ይነሣሉ

• ከ60 እስከ 70 ሚሊየን ብር ካሳ፣ በቤተ ክርስቲያኒቱ ይፈጸማል
• የገዳሙ ታሪካዊና መንፈሳዊ ህልውና አደጋ ላይ ወድቋል ተባለ
• መካነ ቅርሱን በዩኔስኮ ለማስመዝገብ እየታሰበ ነው – ክልሉ

ከአንድ ሺሕ ዓመት በላይ ዕድሜ ባስቆጠረው ደብረ ሊባኖስ ገዳም አካባቢ የተቆረቆረው መንደር ወደ ከተማነት በመለወጡ፣ የገዳሙ ታሪካዊና መንፈሳዊ ህልውና አደጋ ላይ መውደቁ በጥናት የተረጋገጠ ሲሆን መንግሥት፣ ነዋሪዎቹ ከቦታው የሚነሡበትን ሁኔታ እንደሚያመቻች አስታወቀ፡፡

ማኅበረ መነኰሳቱ “ፍኖተ ጽድቅ” በሚሉትና በተለምዶ “ውሻ ገደል” እየተባለ በሚጠራው የደብረ ሊባኖስ ገዳም መግቢያ አካባቢ በሚገኘው መንደር፣ በነዋሪዎችና በገዳሙ መካከል ስላለው ግንኙነት፣ ስምንት አባላት ያሉት አጥኚ ቡድን ያካሔደው የዳሰሳ ጥናት፤ የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት አፈ ጉባኤ አቶ አባዱላ ገመዳና የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትሯ ዶ/ር ኂሩት ወልደ ማርያም ባሉበት ለፌዴራልና ለክልሉ መንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት መቅረቡ ታውቋል፡፡

“የነዋሪዎቹ መበራከት ለገዳሙ ህልውና አስጊ ሆኗል፤ ጉዳዩ እልባት ይሰጠው፤” የሚል አቤቱታ፣ የገዳሙ አስተዳደር ማቅረባቸውን ተከትሎ፣ ላለፉት አራት ወራት ከተለያዩ ተቋማት በተውጣጡ ምሁራን፤ መንደሩ፥ ከገዳሙ ሥርዓት፣ ከአስተዳደርና ሰብአዊ መብት፣ ከጸጥታና ከብዝኃ ሕይወት ጥበቃና ክብካቤ አንጻር የፈጠረው ችግር ተጠንቶ መቅረቡን፣ በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት፣ የቅርስ ጥበቃ ቤተ መጻሕፍት ወመዘክርና ቱሪዝም መምሪያ ዋና ሓላፊ፣ መጋቤ ሰላም ቀሲስ ሰሎሞን ቶልቻ አስረድተዋል፡፡

መንደሩ፣ በገዳሙ ጥንታዊ ይዞታ መሀል መስፋፋቱ ችግር መፍጠር የጀመረው ከ50 ዓመት በፊት ሲሆን የገዳሙ አቤቱታ ከ17 ዓመታት በላይ ሲቀርብ እንደቆየ ያወሱት መጋቤ ሰላም ሰሎሞን፤ በካሳና በምትክ ቦታ አሰጣጥ ጉዳይ ላይ ከሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ጋራ መግባባት ሳይቻል ቀርቶ፣ እስከ አሁን ተግባራዊ ሳይደረግ መዘግየቱን ጠቁመዋል፡፡

READ  በድርቅ አካባቢዎቸ እንስሳትን በመሸጥ ወደ ገንዘብ መለወጥ ይገባል ተባለ

“ከቤተ ክርስቲያኒቱ ታላላቅ ታሪካዊና ተፈጥሯዊ መካነ ቅርሶች አንዱ የደብረ ሊባኖስ ገዳም ነው፤” የሚሉት ዋና ሓላፊው፤ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር አቤቱታውን ተቀብሎ፥ ከሚኒስቴሩ የጥናትና ምርምር ዳይሬክቶሬት፣ ከቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን፣ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲና ከመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት የተውጣጣ የምሁራን ኮሚቴ ተቋቁሞ፣ ካለፈው ሚያዝያ አንሥቶ፣ሙሉ ጊዜ በመውሰድ፣ የችግሩን ሥር መሠረት ማጥናቱን ገልጸዋል፡፡

በጥናቱ ከተጠቆሙት ችግሮች መካከል፥ በንግሥ በዓላት ወቅትና ምእመናን ሱባኤ በሚይዙባቸው ጊዜያት ዝርፊያ፣ ድብደባና አስገድዶ መድፈር መፈጸም፤ ከገዳሙ መንፈሳዊ አገልግሎት ጋር የሚቃረኑ የመጠጥ ቤቶችና ሆቴሎች መስፋፋት፤ የሴተኛ አዳሪነትና የሕገ ወጥ ቪድዮ ቤቶች መበራከት ይገኙባቸዋል፡፡ በገዳሙ የሚገኙ የቆሎ ተማሪዎችንና መናንያንን በከተማ ባህሎች በማማለልና በማላመድ ከትምህርታቸውና ከገዳማዊ አኗኗር ተለይተው በመንደሩ እንዲውሉ ተደርገዋል፤ ይላል ጥናቱ፡፡

በአካባቢው፣ ከመንፈሳዊነት ጋራ ተቃርኖ ያላቸው እንደ ሲጋራ ማጨስ፣ ጫት መቃም፣ በጾም ወቅት እርድ መፈጸምና ኳስ ጨዋታዎችንና ያልተገቡ ፊልሞችን ማሳየት፣ በስፋት እየተለመደና የአካባቢውም ዋነኛ ችግር እየሆነ መምጣቱም ተጠቁሟል፡፡ በመናንያንና በቱሪስቶች ላይ ወከባና ስርቆት ይፈጸማል፤ ሕገ ወጥ የጦር መሣሪያ ግዢና ሽያጭም ይከናወናል የሚለው ጥናታዊ ሪፖርቱ፤የገዳሙን ጥበቃዎች እስከ መደብደብና መሣሪያ እስከ መቀማት የደረሱ የከፉ ችግሮች መኖራቸውን ይገልጻል፡፡

“የገዳሙ አጠቃላይ መልክአ ምድር በራሱ፣ ሥፍራው ለምናኔ እንጂ ለዓለማውያን ሰዎች መኖሪያ እንደማይሆን ማረጋገጫ ነው፤” ያለው ጥናቱ፣ መንደሩ፥ ለዓለማዊ ሕይወት የሚያስፈልጉ መሠረተ ልማቶችንና ተቋማትን ለማሟላት አመቺ እንዳልሆነ ያብራራል፡፡ የፍሳሽ ማስወገጃና መጸዳጃ ቤት ባለመኖሩ፣ አካባቢው ለበሽታና ወረርሽኝ እንደተጋለጠም ይጠቁማል፡፡ መንደሩ በፕላን ያልተሠራ፣ አብዛኞቹ ቤቶችም ወደ ገዳሙ በሚወስደው የአስፋልት መንገድ ዳርቻ በእጅጉ ተጠግተው የተሰሩ በመሆናቸው ለትራፊክ አደጋ የተጋለጡ ናቸው፤ ብሏል፡፡

READ  የብቃት ማረጋገጫ ፈተናን ከወሰዱ መምህራን ማለፍ ያቻሉት 19 በመቶዎቹ ብቻ ናቸው

በአጠቃላይ መንደሩ በሒደት ተስፋፍቶ ወደ ከተማነት እየተለወጠ መምጣቱ፣ የገዳማውያኑን መንፈሳዊ አኗኗርና ተግባራት ከማወኩም በላይ የገዳሙን ቀጣይ ህልውና አደጋ ውስጥ እንደከተተው ጥናቱ አመላክቷል፡፡

መንደሩ በፀበልተኞች ማረፊያነት እንደተቆረቆረ መረጃዎች የሚያመለክቱ ሲሆን፤ በ1968 ዓ.ም በዕድገት በኅብረት መርሐ ግብር ወደ አካባቢው የዘመቱ ወጣቶች፣ የሠሯቸው በርካታ ቤቶች፣ ለመንደሩ መስፋፋት ቁልፍ አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን ጥናቱ ጠቅሷል፡፡ በመንደሩ ከነበረው የቀበሌ መዋቅር፣ ገዳሙ በ1980 ዓ.ም. ከተረከባቸው በተጨማሪ በርካታ የግል ቤቶች እንደተገነቡና በገዳም የሚተዳደሩት ቤቶች ቁጥር እያነሱ እንደመጡ ተጠቅሷል፡፡ በመንደሩ የቦታና የቤት ሽያጭ እንደሚካሔድና የግንባታ ፈቃድ የሚሰጠውም፣ በፍኖተ ጽድቅ በተቋቋመው ጊዜያዊ ኮሚቴ እንደሆነ የተገለጸ ሲሆን ገዳሙ የሚገኝበት የደብረ ጽጌ ወረዳ አስተዳደር፣ በመንደሩ ምንም መንግሥታዊ ሚና እንደሌለውና ከባለይዞታዎች የቦታና የቤት ግብር እንደማይሰበስብም የጥናቱ ሪፖርት አረጋግጧል፡፡

በጥናቱ ማጠቃለያ በተደረገው የቤቶች ቆጠራ፣ መንደሩ በአሁኑ ወቅት 602 ያህል ቤቶች እንደተገነቡበት የታወቀ ሲሆን ከእኒህም መካከል 315 ቤቶች በግል የተያዙ፣ 277 በገዳሙ ባለቤትነት በኪራይ የሚተዳደሩ፣ የተቀሩት 10ሩ ደግሞ ልዩ ልዩ የማኅበራዊ አገልግሎት መስጫዎች እንደሆኑ ተገልጿል፡፡ በአጠቃላይ በመንደሩ አባወራዎችን ጨምሮ 2ሺ263 ነዋሪዎች እንዳሉና ከቋሚ ነዋሪዎች መካከል፥ መንደሩን ያቀኑ ነባር ባለይዞታዎች፣ ፀበልተኞች፣ በገዳሙ በጉልበት ሥራ የሚያገለግሉ፣ ጡረተኞች፣ መናንያን፣ የመንግሥት ሠራተኞችና በግብርና የሚተዳደሩ እንደሚገኙበት ተጠቅሷል፡፡

የ“ፍኖተ ጽድቅ” መንደር ነዋሪዎች፣ ተገቢው ካሣ ከተሰጣቸው ለገዳሙ ክብር ሲሉ አካባቢውን ሙሉ በሙሉ ለቀው ለመውጣት ተነሣሽነት ማሳየታቸው፤ የዞንና ወረዳ መስተዳድሩም፣ በአካባቢው ለተነሺዎች ቦታ ለማዘጋጀት መፍቀዱ፤ የተነሽዎች ቤትና ንብረት የዋጋ ግምት ተደርጐ ከነመጓጓዣቸው የሚያስፈልጋቸውን ከ64 ሚሊዮን ብር በላይ ካሣ ክፍያ ለማመቻቸትና ወደ ገዳሙም መጠቃለል የሚፈልጉትን ለማቀፍ ደግሞ የገዳሙ አስተዳደር መወሰኑ፣ “መልካም አጋጣሚዎች ናቸው፤” ብሏል ጥናቱ፡፡

READ  አቡነ ዮሴፍ የኢትዮጵያ ህዋ ሳይንስ መጻኢ መቼት

ጥናቱ ባለፈው ዓርብ ለቋሚ ሲኖዶሱ እንደቀረበና ለተነሺዎች የሚከፈለው ከ60 እስከ 70 ሚሊዮን ብር የካሣ ክፍያ በቤተ ክርስቲያኒቱ እንዲፈጸም ይኹንታ መገኘቱን መጋቤ ሰላም ቀሲስ ሰሎሞን ገልጸዋል። “በምክረ ሐሳቡ መሠረት ለሚወሰነው ውሳኔና የአፈጻጸም ተግባራዊነት ቤተ ክርስቲያኒቱ የምትተባበር መሆኑን ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ አረጋግጠዋል፤” ብሏል ጥናቱ፡፡ ምትክ ቦታ የማዘጋጀቱ ተግባር በክልሉ ሥራና ከተማ ልማት ቢሮ በኩል ተፈፃሚ ይሆናል ተብሎ እንደሚጠበቅ ዋና ኃላፊው አስታውቀዋል፡፡

ገዳሙ በክልሉ ብቻ ሳይሆን ከሀገሪቱ የጥንታውያንና ታሪካውያን ቅርሶች መገኛ ከሆኑ ስፍራዎች አንዱና ዋነኛው እንደሆነ የተናገሩት፣ የኦሮሚያ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ሓላፊ፣ ገዳማዊ ሥርዓቱን በጠበቀ መልኩ የቱሪስት መስሕብነቱ እንዲቀጥል ከማድረግ አኳያ በቢሮው ልዩ ትኩረት እንደሚሰጠው ጠቁመው፣ መካነ ቅርሱን በዩኔስኮ ለማስመዝገብ እየታሰበ እንደሆነም ለአጥኚ ቡድኑ ገልጸዋል፡፡
የ“ፍኖተ ጽድቅ”(ውሻ ገደል) መንደር ነዋሪዎች ከተነሡና ችግሩ መፍትሔ ካገኘ በኋላ፣ የአካባቢው መንግሥታዊ አካል ለገዳሙ ሙሉ ይዞታ የተረጋገጠለት የባለቤትነት ካርታ እንደሚሰጥ ተገልጿል፡፡

በተከለለው የገዳሙ ይዞታ፣ ሥርዓቱ በሚፈቅደው አግባብ፣ ደንብና መመሪያ በማዘጋጀት፣ መንፈሳዊ አገልግሎቱንና ቱሪዝሙን በተጣጣመ መልኩ ለማስቀጠል የታቀደ ሲሆን የመንፈሳዊና የቱሪስት አገልግሎት መስጫ ተቋማት መሠረተ ልማት ሥራን ብቻ ለማከናወንና የግል ወይም የኪራይ ቤቶች ይዞታ በቦታው ላይ እንዳይቀጥል ለማድረግ ገዳሙ ግዴታ እንደሚገባም ለማወቅ ተችሏል። addisadmassnews

Continue Reading

Art and Culture

ወደ ዳንጉር ተራራ፤ ከማንቡክ እስከ ጉብላክ

Published

on

ወደ ዳንጉር ተራራ፤ ከማንቡክ እስከ ጉብላክ

ወደ ዳንጉር ተራራ፤ ከማንቡክ እስከ ጉብላክ | ተጓዡ ጋዜጠኛ ሄኖክ ስዩም ወደ ዳንጉር ተራራ ይዞን ሊወጣ መተከል ዞን ገብቷል፡፡ በማንቡክ የነበረውን ቆይታ የጉብላክ ከተማን ድባብ እየተረከ ዳገቱን ይዞን ይወጣል፡፡ ስውሩ የተፈጥሮ መስህብ እስከ ዛሬስ የት ነበር? ብሎ ይጠይቃል፡፡ ቋንቋ አብሮ ለመኖር እንቅፋት የማይሆንበትን አኗኗርን እንዲህ ያስጎበኘናል፡፡ | ሄኖክ ስዩም በድሬ ቲዩብ

ማንቦጓ የሚለው ቃል የመጣው ከጉምዝኛ ነው፡፡ መዋቢያ ማለት ነው ትርጉሙ፡፡ ማንቦጓ የሚለው ቃል ደግሞ ማንቡክን ወለደ፡፡ እኔ ማንቡክ ነኝ፡፡

በአሶሳ በኩል ነው የመጣሁት 379 ኪሎ ሜትሮችን ተጉዤ እዚህ ደርሻለሁ፡፡ ያለሁባት ከተማ ስያሜዋን ያገኘችው ከማንቡክ ወንዝ ነው፡፡

የጉምዝ ሴቶች ወደ ወንዙ እየወረዱ ከሚዋቡበት፤ እናም ወንዙን ማንቦጓ ሲሉ መዋቢያ አሉት፡፡ ማንቡክ ከዚህ ቃል ተገኘ፡፡

ዳንጉር ነኝ፡፡ መተከል ገብቻለሁ፡፡ እዚህ ብዙ ተሸሽጎ የኖረ መስህብ አለ፡፡ እዚህ ምንም ያልተነገረለት ተአምር ተቆጥሮ አያልቅም፡፡ የጠንካራ ገበሬዎች ከተማ በጠዋት ትነቃለች፡፡ ሲያቅላላ የታረደው በሬ ጸሐይ ስትወጣ ትዝታውም አይተርፍ፡፡ እንዲህ ናቸው ስጋ ቤቶቿ፤ ብዙው ሱቅ ከግብርና የተቆራኘ ነው፡፡ ብዙ ሰው የሚያወጋችሁ ምድር ምን ያህል ፍሬ እንደሰጠችው ነው፡፡ ብዙ ቋንቋ የሚሰማባት ከተማ ናት፡፡

የሰው ልጆች ከተማ፤ 838700 ሄክታር ቆዳ ስፋት ካለው ዳንጉር ወረዳ ብዙው ቆላማ ነው፡፡ ሦስት እጁ ቆላማ በሆነበት ምድር ደግሞ ሃያ በመቶ የሚሆን አስደናቂ ደጋ ምድር አለ፡፡ ማንቡክ ግን ሞቃታማ ናት፡፡

በ1962 ዓ.ም. ነበር ከተማ ሆና የተቆረቆረችው፡፡ ከከተማዋ ታሪክ ጋር ባለውለታ ሆነው ፊታውራሪ ኢያሱ ዘለቀ እና አቶ ተፈራ ሆሬ ስማቸው ጎልቶ ይነሳል፡፡ ማንቡክን በጠዋት ለቅቄ መንገድ ጀመርኩ፡፡ ቀጥዬ የምንደረደርባት ከተማ ጉብላክ ነች፡፡

READ  ግብጽና ኢትዮጵያ አንዳቸው በሌላቸው ላይ እንደማያሴሩ ተናገሩ

ጉብላክ ከማንቡክ በበለጠ ለግብርና ሕይወት ትቀርባለች፡፡ ሁለ ተገሯ ከምድር ፍሬ ጋር የተገናኘ ነው፡፡ እዚህም እዚያም ሰሊጥ በቆሎ ማሽላ ነው ጨዋታው፡፡ ትራክተሮች ማየት ብርቅ አይደለም፡፡ የማሳ ላይ ውሎ አላደርስ ብሏቸው የነተበ ልብሳቸውን አላወልቅ ያሉ ብርቱዎች ወዛም ያደረጓት ከተማ ናት፡፡

ጉብላክ ሰባ በመቶ ምድሩ ሜዳማ ለሆነው ዳንጉር አንድ ማሳያ ናት፡፡ ሩቅ ድረስ በተዘረጉ የእርሻ ማሳዎች ተከባለች፡፡ ከጉብላክ እስከ ድባጉያ እጓዛለሁ፡፡ ከዚያ በኋላ ግን በእግር ነው፡፡

ለብዙ ሰዓታት በእግር መጓዝ፤ ወደ ዳንጉር ተራራ አናት መውጣት፤ ከዳንጉር አናት ሆኖ ትይዩውን በላያን ማየት፤ እድሜ ጠገቡን ገዳም መጎብኘት፤ የደገኛውን ምድር እስክጠግበው መቆየት፡፡ ወደዚያው ለመሄድ መንገድ ላይ ነኝ፡፡ DireTube

Continue Reading

Art and Culture

“ህዳር ሲታጣን” በዚህ ዘመን….

Published

on

“ህዳር ሲታጣን” በዚህ ዘመን….

ከ100 ዓመታት በፊት በአገራችን በህዳር ወር ተከስቶ የበረው የኢንፍሉዌንዛ በሽታ ስፍር ቁጥር የሌለው የሰው ህይወት እንዳጠፋ የታሪክ መዛግብት ያስረዳሉ።

በዘመኑ የነበሩት ነግስታት የበሽታውን ስያሜ “የህዳር በሽታ” ብለው በሽታው በቀላሉ ሊስፋፋ የሚችለው ደግሞ ከጽዳት ጉድለት መሆኑን ለህዝብ በማስገንዘብ ነዋሪዎች የመንደራቸውን ቆሻሻ እያሰባሰቡ በማቃጠል በሽታውን ለመከላከል እንዲዘምት በአዋጅ አዘዙ።

ይህ የቆሻሻ ማቃጠልና በጭስ የማጠኑ ልምድ በጊዜው የነበረውን በሽታ በማጥፋት ከፍተኛ ሚና የተጫወተ ቢሆንም አሁን የምናቃጥላቸው ፌስታልና የተለያዩ ኬሚካል ያላቸው ቁሶች የከባቢ ሙቀት መጨመርን የሚያባብስ መሆኑን የዘርፉ ባለሙያዎች ይገልጻሉ፡፡

በዘንድሮው ህዳር 12 ማለዳም አዲስ አበባ በግራጫማ ጭስ ታፍና ተስተውላለች፡፡

በጉዳዩ ላይ ያለዎት ሀሳብ አስተያየት ያካፍሉን!!  ebc

READ  Roza Shiferaw, Ethiopian Airlines Crew, Returned $10,000 to Passenger
Continue Reading

Art and Culture

የዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ ከፊት መምጣት

Published

on

የዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ ከፊት መምጣት

የዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ ከፊት መምጣት፤ የኦቦ ለማ መገርሳ ካቢኔ ሩቅ አሳቢነት እና የኦሮሞ ባህል ጥላቻን የመጥላት እሴት | ከስናፍቅሽ አዲስ በድሬቲዩብ

ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ የኦዳ ትራንስፖርት የብስራት ጉባኤ ላይ ከፊት ታይተዋል፡፡ ጎናቸው ያሉት ያሳደጓቸው የፖለቲካ ልጆች ናቸው፡፡ በርሃ ሳሉ አይተዋወቁም፡፡ የበርሃ ጓዱን ለእግዜሃር ሰላምታ ዓይኑን አያሳየኝ በሚል የፖለቲካ ሜዳ ሌላ ዓይነት ጨዋታ ማየታችን አጃኢብ አስብሎን ከርሟል፡፡

እውነቱ ግን ኦሮሚያን የሚመሯት የኦሮሞ ልጆች መሆናቸው ነው፡፡ አንድ መሪ የሚመራው ሕዝብ አብራክ ክፋይ ሲሆን ባህሉን ያከብራል፡፡ እንደ ባህሉ ይኖራል፡፡ ከሀገር ወግ አያፈነግጥም፡፡

እኔ በኦዳ ትራንስፖርት ጉባኤ ላይ ነጋሶን ከነ ለማ ጋር አብሬ ሳያቸው የገባኝ የገዳ ሥርዓት እሴት ምን ያህል ታላቅ መሆኑን ነው፡፡ በሀሳብ ልትለያይ ትችላለህ ግን ጠላት አይደለህም፡፡

ኦሮሚያን በመምራት በኩል የኦሮሞን ባህል አውቆ እንደ ኦሮሞ በመምራት ረገድ የተሳካላቸው መሪ አባዱላ ነበሩ፡፡ ግን እሳቸው በዚያን ወቅት ብቻቸውን ናቸው፡፡ ዛሬ ድፍን ካቢኔው ሊባል በሚችል መልኩ የአባቶቹን ወግ ጠንቅቆ ያውቃል፡፡ የአባቶቹ ወግ ደግሞ ጥላቻን ይጠላል፡፡

እናም እንደ ገዳ ባህል ወንድም ወንድሙን አይጠላም፡፡ ሀሳቡን ስለ ጠላ ወንድሙን አያሳድም፡፡ የዶክተር ነጋሶ ከፊት መምጣት ምስጢሩ ይሄ ይመስለኛል፡፡ ያም ሆኖ በጥላቻ ፖለቲካ መጠጥ የሰከርን ስለሆነ በሆነው ነገር ደንግጠናል፡፡ ተገርመን አላበቃንም፤ አሰላስለን አልጨረስንም፡፡

ዶክተሩ በምን አግባብ ዳግም በኦሮሞ ህዝብ ጉዳይ እንደ አንድ ኦሮሞ በጉባኤ እንግዳ ሆነው ይታደማሉ ብለን እናስብ ነበር፡፡ አዲስ ትውልድ መጣና አደረገው፡፡ በዶክተሩ ቋንቋ ስንጠቀም፤ መንግስቱ ሃይለማርያምን የማይመስል አዲስ ትውልድ፡፡ ይሄ ሌሎቹም ጋር ቢለመድ መልካም ነበር፡፡ ግን ውሃ መውቀጥ ስለሆነ አልናፍቀውም፡፡ ኦሮሚያ ይቀጥል ዘንድ ግን እመኛለሁ፡፡

READ  አቡነ ዮሴፍ የኢትዮጵያ ህዋ ሳይንስ መጻኢ መቼት

ኢትዮጵያ ዲሞክራሲን ብዙ ዓመታት ቀድማ የጀመረች ሀገር ናት ብለን ስንሟገት ማስረጃችን ገዳ ነው፡፡ ሀሳብ እንጂ ሰው እንደማይገፋ ማሳያ የሆነው ይህ ባህል የገዳ ስርዓት እሴት የፈጠረው ነው፡፡ እናም ደስ ያሰኛል፡፡

ኦህዴድ ቀጥሎ ስለ ዶክተሩ ህልውና ያስብበት፡፡ ተገፍተዋል፡፡ እንደ አንድ ተራ ሀገር ዘራፊ ካድሬ እንኳን የሚታዩ አይደሉም፡፡ ርዕሰ ብሔሩ በብዙ ችግሮች ውስጥ ናቸው፡፡

ትናንትናቸውን ማሰብ ባይቻል እንኳን ጀርመንን ከመሰለች ሀገር ከሞቀ ህይወት የሰው ሀገር ሰው ጭምር ይዘው ሀገር አለኝ ብለው የመጡት የኦሮሞን ህዝብ ለማገልገል እንጂ የጀመሩት ትምህርት አላልቅ ብሏቸው አሊያም፤ ከዚች ሀገር ስራ ፍለጋ አይደለምና፤ አርቀን በማሰብ ትውልድ የሚኮራበት ስራ እንስራ፡፡ DireTube

Continue Reading

Trending

news.et Mobile App!

It's Faster!

By continuing to use the site, you agree to the use of cookies. more information

The cookie settings on this website are set to "allow cookies" to give you the best browsing experience possible. If you continue to use this website without changing your cookie settings or you click "Accept" below then you are consenting to this.

Close