Connect with us

Art and Culture

ጥቁር በግ

Published

on

ጥቁር በግ

ጥቁር በግ | በያሬድ ነጋሽ

ሴትየዋ አዲስ ሆቴል ትከፍትና ገበያ የማብዛት አንዳች ምትሀታዊ ድግምት አለው ወደ ተባለው ግለሰብ ዘንድ ትሄዳለች ፡፡ ግለሰቡ ወዳለበት ቦታ በእርሶ መጃን ብላ በእንብርክክ ደረሰች፡፡ አዲስ ሆቴል መክፈቷ እና ቤቷ በገበያ እንዲጥለቀለቅ እንዲያደርግላት ፈልጋ እርሱ ድረስ እንደመጣች ነገረችው፡፡

አዋቂውም ጉዳዩን እያጤነ በመምሰል በዝምታ ቆየ፡፡ ትንሽ ቆይቶም ዶቃ እና ጨሌውን ምራቁን እንፍ እያለ አሻሽቶ መሬቱ ላይ ጣለው ፡፡ ቀጥሎም ጨሌውና ዶቃው አመላከቱኝ የሚለውን ለመናገር እተዘጋጀ ከዛ በፊት ግን 100,000 ብር ፊት ለፊት ባለው ሙዳይ ላይ እንድታስቀምጥ ያዛታል ፡፡ እሷም “ገበያዬ ይብዛ እንጂ አረ እኔ ምን ገዶኝ” በማለት የ100,000 ቼክ ፅፋ አስቀመጠችለት፡፡አዋቂው ትዛዝና ትንቢቱን ደባልቆ ይነግራት ጀመር ፡፡ ጥቁር በግ ገዝታ ቆዳውን በግቢዋ አትክልት ስፍራ ውስጥ እንድትቀብረው እና ስጋውን ደግሞ ዱለት እያደረች ለተጠቃዎች ቁርስ ላይ እንድትሰጣቸው ነገሯት ይህንን ነገር ለአራት ጊዜ እንድትሞክረው ያዛታል፡፡ ይህንንም ካደረገች ቤቷ በገበያ እንደሞላ ገልፆላት ተለያዩ፡፡

ባለሆቴሏም አዋቂው እንዳላት አንዳች ሳታጎድል ለማድረግ እንቅስቃሴ ጀመረች፡፡ ለአራት ጊዜ የሚሆኗትን ጥቋቁር በጎች ገዛች ፡፡ በመጀመሪያውም ዙር አንዱን በግ አርዳ ቆዳውን በአትክልቱ ሥፍራ ውስጥ ቀበረች ፡፡ ዱለቱንም ቁርስ ላይ በነፃ ለተመጋቢዎች ሰጠች፡፡ አዋቂው አልተሳሳተም ነበር፡፡ ቤቷ ከቁርስ እስከ እራት በሰዎች ተጨናነቀ፡፡ ነገሮች እንዲሁ እንደቀጠሉ ነው፡፡ በሆቴሏም አራቱንም ዙር ሳታቋርጥ በጎቹን እያረደች ቆዳውን እየቀበረች ዱለቱን ቁርስ ላይ ለሰዎች እየሰጠች ቤቷም በሰዎች እንደተጥለቀለቀ ነው ፡፡ አዋቂው አራት ጊዜ እንድታደርግ ያዘጋት ድግምት ካለቀ በኋላ ግን የደንበኛው ቁጥር እየቀነሰ ሄዶ በኋላም ዝም ጭጭ ማለት ጀመረ ፡፡ይህም ጉዳይ ባለሆቴሏን ክፉኛ አስጨነቃት፡፡ በድጋሚም አዋቂው ዘንድ ሄዳ በእርሶ መጀን ምን አጉድዬ ይሆን ብላ ለመለማመን ለመሄድ ተነሳች፡፡

ያሄ ምኑ ነው ድግምት ? እንዲመስል ግን ጥቁር በግ አርደሽ ቆዳውን መሬት ቀብረሽ … … … እግዜር ያሳያቹ አንድ ሆቴል በነጻ ዱለት ካበላ ለምን በሰው አይጨናነቅም ? በነጻ የሚያበላውን ዱለት ሲቀር ደግሞ እንዴት ሰው ሁሉ አይቀርም ? ባለሆቴሏን ግን ይበላት ብዬ ወደ ዋና ጉዳዬ ልግባ፡፡

አለማችን በመምሰል ተውጣለች፡፡ እኛም ለእውነታው ሳይሆን እውነት ለሚመስለን ጉዳይ ቀልባችንን ሰጥተን እንኖራለን፡፡ ወደ ግለሰቦች እና ወደ ተቋማት ለአንዳንድ ጉዳያችን መፍትሄ ፍለጋ ተጉዘን ይሆናል ፡፡ መፍትሄ ሰጪውም እጃችን ላይ ያሉ መፍትሄዎችን የተለያዩ የስነ-ልቦና ጥበቦችን (psychological makeup) በመጠቀም ከእጃችን ወስደው እራሱኑ መልሰው ለእጃችን ይሰጡናል ፡፡ በተለያዩ የስነ-ልቦና ጥበቦች የመታለል ሰለባ የሚሆኑ ሰዎች ደግሞ በተሳሳተ መረጃ የታጨቀ ግንዛቤ ያላቸው እና እነሱ ባይረዱትም የተሳሳተ ግንዛቤያቸው ለአታላዩችና ለአሳሳቾች ገጦ መታት በመቻሉ ነው ፡፡

አንድ አሜሪካዊ ነጭ ወደ ኢትዩጵያ ይመጣና ከበርቻቻ አብዝቶ የያዘው ብር ኒል ይገባና ምግብ ለመብላት እንኳን እስኪያቅተው ድረስ አጣ መነጣ፡፡ ይህንን ችግሩን ለመፍታት በከተማችን በሚገኝ አንድ የግል ትምህርት ቤት ውስጥ የእንግሊዘኛ ንግግር (spoken English) መምህር ሆኖ ይቀጠራል፡፡ በት/ቤቱ ውስጥም ከሁሉ ጋር ጓደኝነትን ያበጃል፡፡ መሀከል ላይ ግን ኢትዩጵያዊ ጓደኞቹ ከዚህ ሰው ጋር አንድ ቀላል ፤ ነገር ግን ብዙ ብር የሚያሳፍሳቸውን የንግድ እቅድ ያወጣሉ፡፡

የእቅዳቸው ገበያ ጥናት ያልተወጣበት ያልተወረደበት ሲሆን ነገር ግን የብዙዎቻችን በተሳሳተ መረጃ የታጨቀ ግንዛቤ መነሻ ያደረገ ነበር፡፡ ይህም የሀገር ሰውን እና የሀገር ውስጥ ምርትን አንኳሶ የማየት አባዜአችን ነበር፡፡ ለዚህ አባዜአችን ማረጋገጫ የሆናቸው ደግሞ የሆስፒታላቸውን ፈዋሽነት ፣ የትምህርት ቤታቸውን መላቅ እና የምርታቸውን ጥራት ለህዝብ ለማሳመን ከጀርመን ሀገር በመጡ ሀኪሞች ፣ ከአሜሪካ በመጡ መምህራን እና ከጣሊያን ባስመጣነው ማሽን በሚል ማስታወቂያ የሚስነግሩ ድርጅቶች መብዛታቸው እና እኛም ትልቅነትን ፣ መላቅና እና ጥራትን በዚሁ መለካትና ማመን መጀመራችን ነበር፡፡ ነገሩን በዝርዝር እንመልከተው፡፡

ነገሩ እንዲህ ነው፡፡ ከፊት ለፊታቸው የፋሲካ በአል ሊደርስ ወራቶች ቀርተዋል፡፡ በአዲስ አበባ ኤግዝቢሽን ማዕከል ውስጥ በሚደረገው የፋሲካ ኤግዚብሽንና ባዛር ላይ ለመነገድ የሚያስችለውን ምዝገባ አደረጉ፡፡ በመንደራቸው በቅርብ ከሚያገኟቸው ፈሳሽ ሳሙና አምራቾች ጋር ውል ይዋዋሉና እነሱ በሚፈልጉት ሌብል በማሻሸግ ምርቶቻቸውን ተረክበዋቸው የኤግዚብሽንና ባዛር ዝግጅቱ ውስጥ ተሳታፊ ለመሆን ይጠብቁ ጀመር ፡፡ ኤግዚብሽንና ባዛር ዝግጅቱም ተጀመረና ባነር ፣ ብሮሸሮች … የአሜሪካን ስም ደጋግሞ በማውሳት አሳተሙ፡፡ ያኛው ያጣና የመነጣ አሜሪካዊ ጓደኛቸውን ሱፍና መነፀር በማድረግ በድንኳኑ ውስጥ ቁጭ ብሎ ሞባይሉን የመነካካት ውለታ ብቻ እንዲውልላቸው ጠይቀውት ተስማማ፡፡ ሁሉ ነገር ባቀዱት መሠረት ተጓዘ፡፡ የሀገራችንን ትላልቅ ሳሙና አምራቾችን ባስከነዳ ሁኔታ ያስገቡት የገፍ ፈሳሽ ሳሙና በፈለጉት ዋጋ ጨርሰው ወጡ፡፡ ይህ ፈሳሽ ሳሙና ግን ድንገት ማምረቻው እቤታችን ጎን ሆኖ ዞር ብለን ያላየነው ይሆናል፡፡

አንድ ሀብታም ቤተሰብ የእነሱን ክብር ለሚመጥን ትልቅ ፍጥረት ሴት ልጃቸውን ለማዳር ይነሳሉ፡፡ ቀን ከሌሊት ብርሃኑ ሳይጠፋ የሚኖር ፀሀይ ነው በተባሉት መሠረት ፀሀይን ከፍጥረት ትልቅ በመሆንህ ሴት ልጃችንን ልንድርልህ መጥተናል ይሉታል፡፡ ፀሀይም እንደተሳሳቱ ነገራቸው ብርሃኔ ዘልቆ እንዳይሄድ ማገድ የሚችል ደመና ለተባለ ትልቅ ፍጥረት ልጃቸውን እንዲድሩ መክሮ ሸኛቸው ፡፡

ቤተሰቡ ለዳመናም እንደዛ አሉ፡፡ እሱም ወዳሻው ቦታ ገፍቶ መውለድ የሚችል ነፋስ ለተባለ ትልቅ ፍጥረት ልጃቸው እንዲድሩ ይመክራቸዋል፡፡ ቤተሰቡም ንፋስ ጋርም እንዲህ አሉ፡፡ ነፋስም ወደ ፈለኩት እንዳልሄድ ማገድ የሚቻለው ተራራ የሚባል ፍጥረት ትልቅ ነውና ለእሱ ዳሩለት ይላቸዋል፡፡ ተራራንም እንዲሁ ጠየቁ፡፡ እሱም ከስሩ በስቶ ከላዩ መውጣት የሚቻለው አይጥ የተባለ ታላቅ ፍጥረት ስላለ ከእሱም በላይ ታላቅ እንደማያገኙ አሳምኖ ሰደዳቸው፡፡ ቤተሰቡም እጅግ አዘነ ለዘመናት በቤታቸው ኮርኒስ ውስጥ ሆኖ ሰላም የነሳቸው አይጥ ትልቁ ፍጥረት መሆኑን ሳይረዱ ያባከኑት ጊዜና ያወጡት ወጪ ነደዳቸው፡፡ ካሉትም አይጦች መሀከል መልከመልካሙን መርጠው ለልጃቸው ዳሩለት ይባላል፡፡

አንሳሳት !! .. .. .. እጃችንና አካባቢያችን ላይ ለችግራችን የሚሆኑ ብዙ መፍትሄዎች አሉ፡፡ ግለሰቦችን ከቆዳ ቀለማቸው ፣ ከነተበው እና ካደፈው ልብሳቸው ፣ ካልተመቸው ገጻቸው እና ከደሳሳ ጎጆአቸው በላይ ተሻግሮ የሚያይ መረዳት ካለን ከመፍትሄም በላይ የህይወትን ቁልፍ ሊያስጨብጡን ይችላሉ፡፡ እንዲህ ካሰብን ደግሞ እውነት በማስመሰል በሚዘጋጅ የስነልቦና ተውኔት ሳንታለል እውነታውንና መፍትሄውን በቅርባችን አንዳች ወጪ ሳናወጣ ማግኘት ይቻለናል እላለሁ፡፡ DIRETUBE

 

Trending

By continuing to use the site, you agree to the use of cookies. more information

The cookie settings on this website are set to "allow cookies" to give you the best browsing experience possible. If you continue to use this website without changing your cookie settings or you click "Accept" below then you are consenting to this.

Close