Connect with us

Entertainment

ከቡና ወደ በለስ

Published

on

ከቡና ወደ በለስ

ከቡና ወደ በለስ | አሳዬ ደርቤ በድሬ ትዩብ

ዘወትር ከምሳ በኋላ ለቡና መጠጫ የመደብኩትን ወርሃዊ በጀት ከኮዱ ላይ ገንጥዬ በማንሳት ወደ ‹‹በለስ›› ካዛወርኩት ሁለት ሳምንት አለፈኝ፡፡

ይሄን ውሳኔ የወሰንኩት ባለፈው ቪኦኤ ስለ ሀገራችን የቡና ምርት ስጋት ላይ መውደቅ ሲዘግብ ከሰማሁ በኋላ ነው፡፡ ቪኦኤ ያቀረበው ዘገባ በውጭ አጥኚዎች የተጠና ሲሆን… ጥናቱ የሃገራችን የቡና ምርት በሚቀጥሉት አመታት አሁን ካለበት በግማሽ እንደሚቀንስ የሚገልጽ ነው፡፡

ለነገሩ ጥናቱን ባያቀርቡትም የሐረር ገበሬ ቡናውን እየመነጠረ በጫት እየተካው መሆኑን በዐይኔ በብረቱ አይቼ አረጋግጫለሁ፡፡
ስለዚህ እየጠፋ ያለውን ማስወገድ፣ እየተስፋፋ ያለውን መላመድ አስፈላጊ በመሆኑ የቡና ሱሴን በበለስ ለመተካት መሞከሬ አግባብነት ያለው ይመስለኛል፡፡

እንዳልኳችሁ ከአንጀት የማይደርስ ምሳዬን ለኮፍ ለኮፍ ካደረኩ በኋላ ወደ በለስ ደንበኛዬ ጋር በመሄድ አንድ ሶስት በለስ ጣል ሳደርግበት ሆዴ ብቻ ሳይሆን መንገድ ላይ ካልሾለኩኝ እያለ የሚታገለኝ ቦላሌዬም ባለበት ይረጋል፡፡

ባለፈው ታዲያ ባጋጣሚ ምሳዬን የበላሁት ከአንዲት የስራ ባልደረባዬ ጋር ስለነበር የዘወትር ተግባሬን ለመፈጸም አልቻልኩም ነበር፡፡ እናም በባልደረባዬ ትከሻ ተከልዬ የበለስ ደንበኛዬን ባላዬ ሙድ ላሽ ልለው ስል ‹‹አባው›› እያለ ይጠራኝ ጀመር፡፡

እንዳልሰማ ሰው ሆኜ ለማለፍ ስሞክር ጭራሽ ከኋላዬ ተክትሎ ‹‹ዋይ አይተን አደለም እንዴ የምጣራው›› አይለኝም!
‹‹እኔን ነው?›› አልኩት የጨመደደኝን እጁን ከሸሚዜ ላይ እያነሳሁና እየተቆጣሁ፡፡

‹‹ዋይ እኔን ነው አትበለኝ እንጂ! ለደንበኛዬ ብዬ ሙርጥ በለስ አስቀምጨልህ እንጂ ለምን አባክ የፈለኩህ መስሎህ ነው?›› በማለት በቁጣ ሲናገረኝ… ብስጭቱ ከአንድ ደህንነት እንጂ ከአንድ የበለስ ነጋዴ የማይጠበቅ ስለሆነብኝ ድምጼን እያለሰለስኩና ጉንጩን እየደባበስኩ ‹‹ለዛሬ ይቅርብኝ ብዬ ነው›› በማለት አልፌው ሄድኩኝ፡፡

ያም ሆኖ ደንበኛዬን እንጂ በማንጎ ዋጋ በለሴን እየገዛሁ መመገቤን አልተውኩም፡፡

ችግሩ ግን በቡና ፈንታ ወደ በለስ ተጠቃሚነት ከተዛወርኩበት ጊዜ አንስቶ ወገቤ መግረር፣ እንብርቴ መጠጠር ከመጀመሩም በላይ የመጸዳጃ ቤት ቆይታዬም ረዥም ሁኗል፡፡ መጸዳጃ ቤት ውስጥ የማየው ፍዳ ልጇን ለመገላገል ወደ ሆስፒታል ከገባች እናት ጋር ሲነጻጸር በማማጥም ይሁን በመንቆራጠጥ የእኔው ሳያይል አይቀርም፡፡ ልዩነቱ ከእኔ ምጥ የሚጠበቅ ‹‹ቁስ-አካል›› አለመኖሩ ነው፡፡

ባለፈው እንደውም ከአንድ ሆቴል መጸዳጃ ቤት ገብቼ ‹‹እእእእእእህህህ›› የሚል ቅላጼ ያለው ረዥም ምጥ እያማጥኩ እንዳለ አንድ ድምጹን እንጂ መልኩን ያላየሁት ሰውዬ በትዕግስት ሆኖ መጸዳጃ ቤቱን እንዲለቅለት ሲጠብቀኝ ከቆዬ በኋላ ‹‹ምን በልተህ ነው እንዲህ ሆድህ የደረቀው?›› በማለት ጠየቀኝ፡፡
‹‹በለስስስስስ››
‹‹ውይ እሱን በልተህ ከገባህማ በቃላሉ አትወጣም››
‹‹አልወጣልኝ ብሎ ነው እንጂ መውጣቴስ አይቀርም›› አልኩት፡፡
‹‹አትወጣም ስልህ!››
‹‹ለምን አልወጣም?››
‹‹እሱን ቤተ-መንግስት ሂዲና ጠይቃቸው! እኔ የማውቀው ከዛሬ ነገ ይወጣሉ እያልኩኝ ሃያ አምስት ዓመት መጠበቄን ብቻ ነው›› ብሎኝ በራሱ ንግግር እየሳቀ ጥሎኝ ሄደ፡፡
.
የሰውዬውን አሉባልታ ችላ ብለን ወደ ምጡ ስንመለስ… ምንም እንኳን የበለስ ጣዕም የተመቸኝ ቢሆንም በሌላ መልኩ ግን የሚያስከትለውን ድርቀት መቋቋም አልቻልኩም፡፡ እንደውም አንዳንድ ጊዜ በምጤ መሃከል ትንሽ እረፍት ወሰድ አድርጌ ሳስበው ‹‹ጣና ሐይቅንም እንደ እኔ ሆድ የድርቀት ስጋት ያመጣበት ‹ጣና-በለስ› የሚባል ፕሮጀክት ይሆን?›› የሚል ስያሜን መሰረት ያደረገ ጥያቄ አንስቼ ወደ ምጤ እመለሳለሁ፡፡
‹‹እእእእእእእህህ››
በነገራችን ላይ ከበለስ ጋር ያስተዋወቀኝ አንድ ጓደኛዬ ሲሆን መፍትሔውንም ቢጠቁመኝ ብዬ ቀኑን ሙሉ ስልኩ ላይ ስደውልለት ከዋልኩ በኋላ አመሻሽ ላይ ስልኬን አንስቶ ሽግሬን ከጠየቀኝ በኋላ ‹‹ምን ብጠጣበት ይሻለኝ ይሆን?›› ብዬ ለጠየኩት ጥያቄ የመለሰልኝ መልስ እንዲህ የሚል ነበር፡፡
‹‹ምን አባክ ሞቶ ሃምሳ ጊዜ ድርቀት፣ ድርቀት እያልክ ታደርቀኛለህ? ሎምን ጡይት ጠጥተህ ባንድ ፊቱ ዱፍት አትልም››

DIRETUBE

 

Trending

By continuing to use the site, you agree to the use of cookies. more information

The cookie settings on this website are set to "allow cookies" to give you the best browsing experience possible. If you continue to use this website without changing your cookie settings or you click "Accept" below then you are consenting to this.

Close