Connect with us

Art and Culture

ወራጅ አለ!

Published

on

ወራጅ አለ!

ወራጅ አለ! ሚካኤል አስጨናቂ ፥ በድሬ ቲዩብ)| Michael Aschenaki

<< ቆይ ግን ፥ ለመኪና ወያሎች ቡኒው የፀጉር ሂና በነፃ ነው እንዴ የሚታደላቸው? >>

እኔማ አንዳንዴ ግራ ግብት ይለኛል ፥ የመኪና ባለቤቶች ረዳት ሊቀጥሩ ሰፈልጉ ፀጉሩን ቡኒ ቀለም የሚቀባ ብለው እንደ መስፈርት ያወጡ ይሆን? ወይስ ማንም ሰው ወያላ ሲሆን ‘አራት ኪሎ ፥ ካሳንቺስ ፥ መገናኛ’ እያለ ሲለፍፍ የጉሮሮውን መድረቅ ተከትሎ ፀጉራቸውም አብሮ ይደርቅ ይሆንን?

እንደውም አንድ ነገር ትዝ አለኝ ፥ በባለፈው ሳምንት መጨረሻ ላይ አጎቴ ከክፍለ ሀገር ሊመጣ ነው አላልኳችሁም ነበር? ትዝ አላችሁ አይደል? መጣ እኮ ፤ በግራ እጁ አስር ኪሎ በሶ በቀኝ እጁ ደግሞ አስራ አምስት ኪሎ ቦሎቄ ይዞ መጣ!
እኔማ መጀመርያ ላይ “ጎተራውን ሁሉ ሳይቀር በጀርባው አዝሎ ይሆን እንዴ የመጣው?” ብዬ ጀርባውን አተኩሬ ሳየው ፥
“አንተ ጀርባዬን የምታጠናው ሽብርተኛ ሀይል እመስልሀለሁ እንዴ?” ብሎ ኩም አደረገኝ ፤ አስቡት ኦገኖቼ ይሄ ጀርባ ማጥናት የሚባለው ነገር ለካ ኢትዮጲያ ሬዲዮ እንኳ በቅጡ የማይሰራበት የሀገራችን ገጠራማው ክፍል ሁሉ ደርሷል!

”አጎቴ ጀርባ ማጥናት ነው ያልከኝ ፥ ኧረ ይህን ቃል ከወዴት ሰማኅው?” አልኩት መገረሜን አንገቴን ከታች ላይ በማወዛወዝ እየገለፅኩለት

“ ይሄማ አንዳንድ ፀረ ልማት እና ኪራይ ሰብሳቢ ሀይሎች የብሄር ብሄረሰቦች አሻራ ያረፈበትን ህገ መንግስት በሀይል ለመናድ እየተመሳጠሩ እና እያሴሩ ሲገኙ እኛ የገጠር ቀበሌ አስተዳዳሪና ካቢኔዎች የኋላ ታሪካቸውን ለማጥናት የምንጠቀምበት ንግግር ነው” ብሎ በቅንፍ ውስጥ የገጠር ካቢኔ መሆኑንም አያይዞ ሹክ አለኝ። አዎ ከዚህ በላይ እኔም ከቀበጣጠርኩ ቀጣዩ የሚጠናው ጀርባ የኔ ሊሆን ይችላል በሚል ስጋት እያጣፈፍኩና እያስካለብኩት ወደ ሰፈሬ የሚወስደው ታክሲ ውስጥ ይዤው ገባሁ።
አጎቴ ቆፍጠን ብሎ ፥ ወያላው ላይ ትክ ብሎ ካፈጠጠበት በኋላ

“አንተ ወፈፌ! ፥ የማንን ኮበሌ ጭድ ለጭድ ስታላፋ ነው ፥ ፀጉርህ እንዲህ እብቅ በ እብቅ የሆነው ” አለው ።
“ ጀለስካ ” አለኝ ረዳቱ ወደኔ ዞር ብሎ “ምንሼ ነው እኒህን አብረው የመጡት ፋያሽ የፀጉር ቀለም አያርፉም እንዴ?ቆይ እኒህ ሰውዬ ከገዳም ነው ወይንስ ከክልል ነው የመጡት?” አለኝ አራድኛ ቋንቋ በተቀላቀለበት ንግግሩ ጥያቄውን እያዥጎደጎደ፤
አጠገቤ ተቀምጣ የነበረችው ልጅ ፈገግ አለች ! አቤት እኒያ ሀጫ በረዶ የመሰሉ ጥርሶቿ ስስ የሆነው ከናፍሯን ተሻግረው ብቅ ሲሉና ከፈገግታዋ ጋር ከተፍ የሚሉት ስርጉዶቿ እንዴት የውበት ጣራ ላይ እንደሰቀሏት አጠይቁኝ ፥ ታክሲ ውስጥ ከተሳፈርኩበት ሰዓት አንስቶ እርሷን ለማናገር ስንት ጊዜ ይሄ ቂጣ የቀደደው አፌን ከፍቼ እንደዘጋሁ እኔ ነኝ የማውቀው? ድንገት የአጎቴን ገድ ማን ያውቃል? የግራ ጎኔን ክፋይ ላገኛት ነው መሰል? ቁርጥ እኔ የምፈልጋት አይነት ሴት ነች።

በቃ ያበጠው ይፈንዳ እንጂ አሁን ስሟን ጠይቄ ልተዋወቃት ይገባል!
“ የኔ ስም ሚኪ ይባላል ፥ ያንቺን ትነግሪኝ ቆንጆ?” አልኳት የእጆቼን መዳፍ በሰላምታ መልክ እየሰደድሁላት
“ ኧህ የኔ ………………….” አላልኩም ስሟን ልትነግረኝ ነው። እኔ ድሮውንስ እጣ ፈንታዬን መች አጣኋትና
“ ወራጅ አለ !” አለች ቀጥላ በሚስረቀረቀው ቀጭን ድምጿ ንግግሯን ከፍ አድርጋ
ውይ ደግሞ ታክሲው ለክፋቱ እንዴት ፈጥኖ እንደቆመ ፥ ወሽመጤ ቁርጥ ሲል ታወቀኝ።

”ምፅ! አወይ ድህነት ክፉ ፥ አሁን ይቺ የወረደችው ልጅ ምናለ ቤተሰቦቿ ትንሽ ጨመር አድርገው ከጉልበቷ በታች ያልተቀደደ ሙሉ ቀሚስ ቢገዙላት ፥ እንዴት ያለችውን መልከመልካም ሸጋ ልጅ አጠፏት መሰለህ!?“ አለኝ አጎቴ የልጅቷን አጭር ቀሚስ አይቶ ካበቃ በኋላ እኔ ወደተቀመጥኩበት ቦታ አንገቱን ሶስት መቶ ስልሳ ዲግሪ አጠማዞ ፥ በዕውነቱ አጎቴ በሰዓቱ ስሜታዊ ሆኖ ነበር ለማለት ይቻላል ።

“ አንቺ ፋያሽ እርጥብ ተሸላሚ አርሶአደር ነገር ናቸው ” ብሎ ወያላው በዚያ የመለቁሴ ፎጣ በመሰሉ ጥርሶቹ ፈገግ ሲል እኔ ደግሞ በተራዬ ፊቴን እንደ ርጥም ብርድልብስ ዘፍዝፌው ስኮሳተር ነበር ፥ ይሁንና ግን ተቃጠል ሲለኝ ሁሉም ተሳፋሪ የወያላው ቀፋፊ ሳቅን ተከትለው አሽካኩ ፥ ። እኔኮ ግርም የሚሉኝ ነገር ሲናገር እንኳ ስርዓት ያልተሞላበት ና አፉ ላይ የመጣለትን ያለ ለከት የሚዘባርቅ ሰውን በመንቀፍ እና አደብ በማስያዝ ፈንታ ፥ ክፉ ንግግሩን ተከትለው የሚያሽካኩት በርታ ባይ አጃቢዎች ናቸው።

አዎን የብዙዎቻችን ችግር ከዚህ ይጀምራል ፥ እንደ ቀልድ እና እንደ ዋዛ እሰይ እሰይ እያልን የምናበረታታቸው ክፉ ልማዶች ጭራሽ ይባስ ብለው አሁን ደግሞ የባህላችንም አካሎች እየሆኑ የመምጣታቸውን ነገር እያሰቡ ማስተዋል ያሻል።
ለዛም ነው ወያላው በተናገረው ቅጥ አምባሩ በጠፋበት አማርኛ ሲያስካኩ የነበሩ ተሳፋሪዎች ከልቤ ያበገኑኝ።
እናም ከወያላው ፈገግታ ጋር አንድ ነገር ታሰበኝ ፥ አበስኩ ገበርኩ! ያን ሀጫ በረዶ የመሰለ ጥርስ ባየ አይኔ የሰፈራችህ ሴትዮ የሆኑት እትዬ ማዘንጊያሽ ያሰጡትን የባቄላ ክክ የመሰለ ጥርስ ያሳየኝ!? ዕውነት ፥ ዕውነት አጎቴ ገደቢስ ካድሬ ነው ።

DIRETUBE

Trending

By continuing to use the site, you agree to the use of cookies. more information

The cookie settings on this website are set to "allow cookies" to give you the best browsing experience possible. If you continue to use this website without changing your cookie settings or you click "Accept" below then you are consenting to this.

Close