Connect with us

Art and Culture

የሚበረታታው የኢትዮጲያ የሙዚቃ ኢንዱስትሪ!

Published

on

የሚበረታታው የኢትዮጲያ የሙዚቃ ኢንዱስትሪ!

የሚበረታታው የኢትዮጲያ የሙዚቃ ኢንዱስትሪ! | ሚካኤል አስጨናቂ ፥ በድሬ ቲዩብ

እንደ መግቢያ → { የደራሲውን ተጨማሪ ስራዎች ለምትፈልጉ አንባቢያን “Michael Aschenaki” ብላችሁ ፌስቡክ ላይ በመፈለግ መከታተል ትችላላችሁ }

ሰላም ለእናንተ ይሁን ተወዳጆች! ሳምንቱ እንዴት አለፈ? ለነገሩ እናንተ ምን ትሆናላችሁ ?! ይብላኝ እንጂ ለኔ ለታካች ሚስኪኑ! ምፅ…
ወገን አሁን እኔ አገባሁ የምለው ሚስት ነው ወይስ ሚጥሚጣ!
ቆይታ መጣች ፥ ዝም አልኩ ! አምሽታ መጣች ፥ ዝም አልኩ! አድራ መጣች ፥ ዝም አላልኩም…….
“ ሴትዮ ይሄ ነገር አልበዛም? “ የምትለዋን አጭር ጥያቄ በቁጣ ሳይሆን ተለሳልሼ ጠየቅሁ ፤ የጠበቀኝ ምላሽ ግን በዕውነቱ ጠንከር ያለ ነበር

“ እኔን ሴትዮ!” ብላ አንባረቀች ፤ በዕውነቱ በሰዓቱ የማስታውሰው ነገር ቢኖር የእንቁላል መጥበሻውን ስታነሳ ማየቴን ብቻ ነበር ፤ አንዳች ነገር “ኪው” የሚል ድምፅ አውጥቶ አናቴን ከበረቀሰኝ በኋላ የሆነ ነገር ብልጭ ብሎብኝ ከመሬት ተዘረርሁ! ከተጋደምኩበት ከሁለት ሰዓታት በኋላ ስባንን ግን ሚስቴ ፊት ለፊቴ አልነበረችም! “ኡፍ ተመስገን ጌታዬ !“ ብዬ ገና ከመተንፈሴ ወደ ጀርባዬ ዞር ስል ደህና ባለ እንጨቱን የቤት መጥረጊያ አነጣጥራ እየጠበቀችኝ ነበር።
ከቀድሞው በባሰና አሳዛኝ በሆነ ቅላፄ

” የኔ ፍቅር በዕውነቱ ሴትዮ የሚለውን ቃል በመናገሬ ፥ ዱንዝዝ ድንጋይ ራስ መሆኔ ስለገባኝ ይቅርታሽን ጠይቄያለሁ! ግን እንደሁ ተወዳጁ ድሬ ቲዩብ ላይ አንድ የማነሳት ቁም ነገር አለችና መጥረጊያሽን ቁጭ አድርገሽ ዕድሉን ትሰጪኝ ዘንድ በማክበር እጠይቃለሁ “ እንዳልኳት ፥ ትንሽ እንደማንገራገር ብላ
” ሰውዬ በድሬ ቲዩብ አትምጣብኝ ፥ የሆንክ አስኮናኝ!“ ብላ መጥረጊያውን ወደቦታው መለሰችው።
ተጀመረ ……………………………….
ጥሩ ጅማሮ ነው!

ሙዚቃ ከ ሰው ልጅ መፈጠር ጀምሮ የነበረ ፣ ያለ እና የሚኖር ስሜት ቀስቃሽ ሚስጥራዊ ሀይል ነው። ሙዚቃ ከሰው ልጆች ባሻገር እንስሳትን እና ዕፅዋትን ሁሉ ስሜት የሚሰጥ ጥበብ መሆኑን ብዙ የሳይንስ ጥናቶች ያመላክታሉ።

ሀገራችንም በዚህ የሙዚቃ ኢንዱስትሪ ውስጥ በተለያዩ ጊዜዎች ውስጥ ሲዋዥቅ የነበረ እሽክርክሮሽ ውስጥ አሳልፋለች ፥ ብዙ ወርቃማ ጊዜያት እንደነበሩ ሁላ ”አይይ ሙዚቃ እቴ !? የ እብድ ዘመን መጣ!“ ያስባሉ ታሪኮችንም ማንሳት እንችላለን።
በተለይ ወርቃማ ከሆኑት የአስራ ዘጠኝ መቶ ስልሳ ጊዜያት አንስቶ የነበረው ድንቅ የሙዚቃ ጊዜያት በ አስራ ዘጠኝ መቶ ዘጠናዎቹ መጀመርያ ላይ ወደነበረው የዘመናዊ ሙዚቃ ጥንስስ ወቅት ላይ ደርሶ በነበረበት ሰዓት ከባድ የሚባሉ ተግዳሮቶች የገጠሙት ሲሆን በሂደት ደግሞ የተሻሉ ነገሮችንም ሰምተን እንድናጣጥምም ሆነናል። እነዚህ የዘመናዊ ሙዚቃ ጅማሮች ላይም ተወዳጁ አርቲስት ቴዲ አፍሮ ፥ ጎሳዬ ተስፋዬ እና አሌክሶ የተጫወቱትን የጎላ ሚና ለማንሳት እንወዳለን።

እነዚህ አርቲስቶች የአስራ ዘጠኝ ዘጠናዎቹ የዘመናዊ ሙዚቃ ፈርጦች ናቸው ብንል ማጋነን አይሆንብንም።
የሚሊኒየምን አዲስ ብስራት ተከትሎ በነበሩት ጥቂት ወቅቶች ላይ ይህ ጅማሮ ከሽፎ ፥ ሙዚቃዎቻችን ከሀገራዊ ለዛ ወተው የውጪውንም ቃና በቅጡ ሳይዙ መሀል ቤት ላይ ተንጨባርቀው እኛንም ጆሮዎቻችንን መቀለጃ አድርገውበት የነበረበት ክስተት የተፈጠረ ሲሆን አሁን አሁን ደግሞ ባህላችንን ከዘመናዊ ሙዚቃ ጋር አማክለው እየወጡ ያሉ ስራዎች ተስፋችን ተመልሶ እንዲያገግም አድርገውናል። በዚህም ላይ እነ ሚኪያስ ቸርነት ፣ ወንዲማክ ፣ መስፍን በቀለ ፥ የእነ አቢዮት የጭፈራ ጥምረት ፣ያሬድ ነጉ ፣ አለምዬ ፣ አስጌ ባሌ ሮቤ እና የመሳሰሉትን ለማመስገን እንወዳለን።

ይሁንና እነዚህ ድንቅ ባህልን ከዘመናዊ ስራ ጋር የማጣመር ስራዎች እንዳሉ ሆነው ፥ መሰረታዊ በሆኑት የግጥም ስራዎች ፣ የቀረፃ እና ቅንብር ፥ በክሊፕ ስራዎች ላይም ከፍተኛ ክፍተቶች መስተዋላቸው አልቀረም። ተደጋጋሚ የሆኑና ተመሳሳይ ክሊፖችን ማየት አሰልቺ ከመሆኑም ባሻገር ሀገሬ ፥ ሀገሬ እያሉ በአውሮፓ ና አሜሪካ ጎዳናዎች ላይ እስክስታ ማውረድ የሀገርን ፍቅር ተዓማኒነትም አጠራጣሪ ያደርገዋል። የማይኖሩትን ዓለም አስመስሎ እንደመቅረብ አሳፋሪ የህሊና ዝቅጠት ያለ አይመስለኝም።

ከዚህ መለስ ባለውና ቀድሞ ከበላይ በጠቀስነው ባህልን ከዘመናዊ ሙዚቃ ጋር የማጣመር ጥሩ የሚበረታታ ጅማሮ መሰረቱን ሳይለቅ ባህላዊውን የሀገራችንን የ አኗኗር ዘይቤ ከዘመናዊ ሙዚቃዎች ጋር አጣምሮ ፥ ከዚህ ቀደም በህንድ እና በቻይና አዘውትረን ያየናቸውን አይነት ከምዕራብያውያን ተፅዕኖ የተላቀቀ የራሳችን ቀለም እና አሻራዎች ያረፈባቸው ስራዎችንም በተከታታይ እንደሚያስገኝልን ተስፋ እናደርጋለን።
መልካም ይሁን በያላችሁበት! DIRETUBE

Trending

By continuing to use the site, you agree to the use of cookies. more information

The cookie settings on this website are set to "allow cookies" to give you the best browsing experience possible. If you continue to use this website without changing your cookie settings or you click "Accept" below then you are consenting to this.

Close