ሚስቱን ከገደለ በኋላ ራሱን ከ6ኛ ፎቅ የወረወረው ግለሰብ በ19 አመት ፅኑ እስራት ተቀጣ

0
ሚስቱን ከገደለ በኋላ ራሱን ከ6ኛ ፎቅ የወረወረው ግለሰብ በ19 አመት ፅኑ እስራት ተቀጣ
ተከሳሹ ፍርድ ቤት ቀርቦ “ሚስቴን የደበደብኳት በስካር መንፈስ ነው፤ አስቤበት አልገደልኳትም፤ በዚህ ድርጊቴ ተፀፅቼም ከፎቅ ተወርውሬ ራሴን ለማጥፋት ሞክሬ ነበር” ሲል አስረድቷል።

በስካር መንፈስ ሚስቱን ደብድቦ ከገደለ በኋላ ራሱን ከ6ኛ ፎቅ የወረወረው ግለሰብ በ19 አመት ፅኑ እስራት ተቀጣ።

የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ 4ኛ የወንጀል ችሎት ነው የቅጣት ውሳኔውን ያሳለፈው።

የጠቅላይ አቃቤ ህግ ክስ እንደሚያመለክተው፥ ተከሳሽ አክሊሉ መላኩ በሰኔ 20 2007 ዓ.ም በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 7 ተከራይቶ በሚኖርበት መኖሪያ ቤት ውስጥ ሚስቱን ደብድቧል።

በእለቱ ከቀኑ 10 ስአት ጀምሮ ከባለቤቱ በእምነት ገረመው ጋር ሲዝናኑ አምሽተው ሁለቱም በስካር መንፈስ ላይ እንደነበሩ በክሱ ተጠቅሷል።

በወቅቱ በስካር መንፈስ በተፈጠረው አለመግባባት ሚስቱን የደበደበው ተከሳሹ ለሞት መቃረቧን ሲያረጋግጥ ቤቱን ጥሎ ወጥቶ ወደ ሰሜን ሆቴል ያመራል። ከሆቴሉ 6ኛ ፎቅ ላይ በመውጣትም ራሱን መወርወሩን የአቃቤ ህግ ክስ ያስረዳል።

የአካባቢው ሰዎች በአቅራቢያው ወደሚገኝ የህክምና ጣቢያ ወስደውት ህክምና አግኝቶ ህይወቱ በመትረፉም አቃቤ ህግ በግድያ ወንጀል ክስ መስርቶበታል።

ተከሳሹ ፍርድ ቤት ቀርቦ “ሚስቴን የደበደብኳት በስካር መንፈስ ነው፤ አስቤበት አልገደልኳትም፤ በዚህ ድርጊቴ ተፀፅቼም ከፎቅ ተወርውሬ ራሴን ለማጥፋት ሞክሬ ነበር” ሲል አስረድቷል።

የግድያ ወንጀሉን አስቦበት ሳይሆን በስካር መንፈስ መፈጸሙም በማቅለያነት እንዲያዝለት ጠይቋል።

ክሱን የተመለከተው የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ 4ኛ የወንጀል ችሎትም ተከሳሹ ድርጊቱን የፈፀመው በስካር መንፈስ መሆኑን በማቅለያነት በመያዝ በ19 አመት ፅኑ እስራት እንዲቀጣ ወስኗል።

fanabc

READ  ድርቅ በደቡብ ኦሞ ዞን

NO COMMENTS