Connect with us

Art and Culture

በዚህ እለት፤ በዚህ ጊዜ፤ በዚህ ቦታ

Published

on

በዚህ እለት፤ በዚህ ጊዜ፤ በዚህ ቦታ

እንዴት ያለ ራዕይ ወይም ህልም ተልመን ይሆን ? ህልማችንንስ የትስ ቦታ ለማሳካት አቅደን ይሆን ? በየትኛውስ ወቅት እውን እንዲሆን እንፈልግ ይሆን ? ብቻ የትኛውም አይነት ህልም ይኑረን ፤ በየትኛውም ቦታ ለመተግባር እናቅድ ፤ በየትኛው ጊዜ እውን እንዲሆን ብንፈልግም የህላማችንን ግዝፈትና ለማሳሳካት የሚኖረውን ውጣ ውረድ በማሰብ እንዴት እና በምን አይነት መንገድ ህልሜን ማሳካት ይቻለኝ ይሆን የሚል ጥያቄ ለብዙዎቻችን ከፊታችን የተጋረጠ ጥያቄ ይሆንብናል ፡፡ በሌላ በኩል በእየ እለት ተዕለት ኑሮዋችን ደጋግመን በመከወናችን ሳቢያ የተላመድናቸውና እጅጉን ቀላል የሚመስሉን ጉዳዮች ደግሞ በርካታ ናቸው ፡፡ ህልሜን እንዴት ማሳካት ይቻለኛል የሚል ጥያቄ ከተጋረጠብን ሰዎች መሀከል የአንድን ወጣት ጥያቄ ለናሙና እንውሰድና ነገሩን ለማየት እንሞክር፡፡

ወጣቱ አንድ እንዲሆንለት የሚሻው የወደፊት ህልም አለው፡፡ ህልሙም ቢሳካ የእርሱን ህይወት ከመቀየር አልፎ ተርፎ የቤተሰቡን ብሎም የማህበረሰቡን ኑሮ መቀየር እንደሚያስችለው ይገባዋል፡፡ ሆኖም ግን እንዴት የሚል ጥያቄ ከፊቱ ተጋርጦበታል፡፡ ከዚህም በዘለለ የገዛ አይምሮው የህልም እንጀራ ነው እያለ ሊያሳምነው ይሞግተው ይዟል፡፡በሌላ በኩል ደግሞ እጅግ ቀላል እንደሆነ ያመነበትን ጉዳይ ለማሳካት አንድ ምሽት ላይ እቅድ አወጣ፡፡ነገሩ እንዲህ ነው፡፡

አንድ ቀን ምሽት ላይ ለአንድ ጓደኟው ይደውልና ለብርቱ ጉዳይ በጥብቅ ስለሚፈለገው እዛው ጓደኛው የሚኖርበት ሰፈር በሆነው ሸጎሌ በምትገኝ አንዲት ካፍቴሪያ ውስጥ ከጠዋቱ 3፡30 ላይ ሳያረፍዱ እንዲገናኙ ይቀጥረውና ስልኩን ይዘጋዋል፡፡ ቀጥሎም ጠዋት የሚለብሰውን ልብስና ጫማ አዘጋጅቶ ይተኛል ፡፡ ማልዶም ይነሳና ቁርሱን በልቶ፤ ከሚኖርበት ሰበታ ታክሲ ተሳፍሮ እንዳለውም አንዲትም ሽራፊ ሰከንድ ሳትዘነፍ በቀጠሮው ቦታ የተባባሉት ካፌ ውስጥ ከጓደኛው ጋር ተገናኘ፡፡

ወጣቱ እንዴት ይቻለኛል ያለው ግዙፉ ህልሙ እና ቀላል እንደሆነ ያመነበት በጠዋት ጓደኛውን ቀጠሮ ማግኘት እኩል ነበሩ፡፡ ምክንያቱን እንመልከት፡፡

ወጣቱ ጓደኛውን ቀጠሮ አሲዞ በተኛበት ለሊት ፤ ሌቱ ላይነጋለትና ከእንቅልፉ ሳይነቃ በዛው የሚቀርባቸው ከአንድ ሺ በላይ ምክንያቶች ነበሩ፡፡ ከጎኑ ባለው ቸልተኛ ጎረቤቱ ሳይጠፋ በተረሳ ሻማ የተነሳ እሳት ወደ እርሱም ቤት ተጋብቶ እሱን ከፍራሹ ለመለየት በቸገረ ሁኔታ አንድዶት ቢያደርስ ? በአንድ ወቅት በወላይታ ሶዶና የሻሸመኔ መውጫና መግቢያ በሮች ላይ የተከሰተው የመሬት መሰንጠቅ የሱን ቤት መሀል ለመሀል አካፍሎ ያለፈ የነበረ ቢሆንስ ? እኩለ ለሊት ላይ ከመጠን በላይ ጠጥቶ መኪና በማሽከርከር ወደ ቤቱ ይገባ የነበረ ጎረቤቱ ከወጣቱ ደጃፍ የነበረውን ስልክ እንጨት ገጭቶ በመጣል በቀጥታ ወደ ወጣቱ መኝታ ቤት ላይ ወድቆ መሀል አናቱን ነርቶ ገድሎት ቢሆንስ ? ብቻ አይድረስ እንጂ የምራቅ ትንታስ በዛው ይዛው ሄዳ ቢሆንስ ? ነገር ግን ይህ ሁሉ ሳይሆን ቀረና ነጋለት፡፡

ከነጋም በኋላ ቢሆን በትራንስፖርት ተሳትፎ ወደ ጓደኛው ሰፈር የማይደርስባቸው ከአንድ ሺ አንድ በላይ በርካታ ምክንያቶች ነበሩ፡፡ የተሳፈረበት ታክሲ ሹፌር በሀንጎቨር ነበርና መኪናዋን የሚዘውረው፤ ባጋጠመው የእንቅልፍ ሽልብታ መስመር ስቶ በመንገዱ ዳር ባሉ ድልድዮች በአንዱ ገብቶ የነበረ ቢሆንስ ? ሹፌሩ ሰላም ቢሆን እንኳን የተሳፈረበት ታክሲ ከኦሪት ጀምሮ መነዳት የጀመረች ከርካሳ ነበረችና ፍሬን በጥሳ ከአንድ ቋጥኝ ጋር አላትማቸው የነበረ ቢሆንስ ? ሹፌሩም መኪናዋም ጤነኛ ነበሩ እንበል ፤ ነገር ግን እንደ አውሎ ንፋስ ይከንፍ የነበረ የዘመኑ ሞገደኛ የሲኖ ትራክ ሹፌር ታክሲዋ ላይ ወጥቶ ከአስፓልቱ ጋር ለጥፏቸው የነበረ ቢሆንስ ? ብቻ ይህም ሳይሆን አለፈና ከጓደኛው ጋር በቀጠሮው ሰዓት ተገኝቷል፡፡

ይህ ወጣት ቀጠሮው ቦታው ለመገኘት ያደርገው የነበረው አስተዋፅኦ ማታ ላይ የጠዋት ልብስና ጫማውን ማዘጋጀት፣ ጠዋት ቁርሱን መብላት፣ እራሱን ታክሲ ድረስ ማድረስ፣ የታክሲ ሂሳብ መክፈል እና የቀጠሮው ቦታ ወደ ሆነው ካፌ እራሱን ማድረስን ብቻ ነበር፡፡ ይህ ደግሞ ሊደርስበት ቢችል ኖሮ ብለን ካልናቸው ነገሮች ጋር ሲነፃፀር 1% ላትሞላ ትችላለች ፡፡

ስለዚህ ይህ ወጣት ቀጠሮው ቦታ ለመድረስ ካደረገው እንቅስቃሴ በላይ ተስፋውን ከልበ ሙሉነት በመነጨ እምነት በማጀቡ እውነትን ለማየት በመቻሉ ነበር፡፡

ይህ ወጣት እንዴት ይቻለኛል ለሚለው ግዙፍ ህልሙ መሳካት የሚሻ ከሆነ ህልሙን እንደሚያሳካው ከልብ ሙሉነት የመነጨ እምነትና ለቀጠሮው እለት እንዳዘጋጀው ጫማና ልብስ እንደ ከፈለው የታክሲ ብር ያሉ የአቅሙ ልክ ጥረት ማድረግ ብቻ ይገባዋል፡፡ ድንገት ግዙፍ ነው ከሚለው እምነቱ ይልቅ ጓደኛውን ቀጥሮ ማግኘት ከባድ ሊሆን ሁሉ ይችል ይሆናል፡፡ ስለዚህ ወጣቱ ካንተ የሚጠበቁ ጥረቶችን እያደረክ በእዚህ እለት፣ በዚህ ጊዜ እና በዚህ ቦታ ብለህ ግዙፉን ህልምህን ቅጠረው፡፡

DIRETUBE

Trending

By continuing to use the site, you agree to the use of cookies. more information

The cookie settings on this website are set to "allow cookies" to give you the best browsing experience possible. If you continue to use this website without changing your cookie settings or you click "Accept" below then you are consenting to this.

Close