Connect with us

Entertainment

አማሮ ነኝ-ከኮሬዎች ምድር

Published

on

አማሮ ነኝ-ከኮሬዎች ምድር

አማሮ ነኝ-ከኮሬዎች ምድር | ተጓዡ ጋዜጠኛ ሄኖክ ስዩም አማሮ ነው፡፡ አማሮ በደቡብ ክልል ተወዳጁ ቡና የሚመረትበት የኮሬ ብሔረሰብ ወረዳ ነው፡፡ ከሰንሰለታማዎቹ ተራሮች ስር ሆኜ ይሄንን አየሁ ሲል ሄኖክ ስዩም የተመለከተውን እንዲህ ይነግረናል፡፡ (ሔኖክ ስዮም በድሬትዩብ)

አማሮ ገባሁ፡፡ የገላና ሸለቆ ጠንጣሎ በተራራ ከታገደበት ምድር፡፡ አማሮ የኮሬዎች ምድር ነው፡፡

ደቡብ ነኝ፡፡ የአባያና ጫሞ ሐይቆችን አየር ቁልቁል ወደ ነገሌ እንዳይከንፉ ካገዱት ሰንሰለታማ ተራሮች ስር፡፡ አሁን ያለሁባት ከተማ ኬሌ ትባላለች፡፡ ከዚህ ሀዋሳ 210 ኪሎ ሜትር ይርቃል፡፡ ኬሌ ጠዋት ማታ ተራራ የምታይ ከተማ ናት፡፡ የአማሮ ሰንሰለታማ ተራሮች ዓይናቸውን ከኬሌ ላይ ነቅለው አያውቁም፡፡

ኬሌ የዕርቅ ምድር ናት፡፡ ተፈጥሮ ይታረቅባታል፡፡ በዚያ የገላና ሸለቆ እስኪበቃው ተኝቶ ወበቅ ይተፋል፡፡ በዚህ የአማሮ ተራሮች ጉም ያስመልሳሉ፡፡ በመሀል እኔ ያለሁባት የኮሬዎች መዲና ኬሌ ተዘርግታለች፡፡ እንዲህ የታደሉ ከተሞች ትንሽ ናቸው፡፡

እዚህ ደራሲና ጋዜጠኛ ተሾመ ገብረ ስላሴ ደጋግሞ የተረካቸው የአማሮ ደጋማ ቀበሌዎች መዲና ውስጥ ሆኜ ሽቅብ ህይወት አያለሁ፡፡ እንደ በርሊን ግንብ ተራራ አንድን ህዝብ ሁለት ቦታ ከፍሎ ቆለኛና ደገኛ ሲያደርግ መሀል ሆኖ መመልከት እድል ነው፡፡ ተራራ ለአማሮ ብርቅ አይደለም፡፡ የአማሮ ተራሮች ባለ አረንጓዴ ካባ ናቸው፡፡ ልብሰ ተክህኖን ከፈጣሪ የታደሉ፡፡ ደሎ የአማሮ ትልቁ ተራራ ነው፡፡

 

በደቡብ ከሚገኙ አንጋፋ ተራሮች አንዱ ሲሆን ከጉጌ ቀጥሎ ወደ ሰማይ በመጠጋት የክልሉ ሁለተኛው ረዥሙ ተራራ ነው፡፡ አሁን ግን ኬሌ ከተማ ከሚገኘው ተራራ ስር ነኝ፡፡ ከዚህ ተራራ ንጹህ የምንጭ ውሃ ወንዝ ሆኖ ቁልቁል ይወርዳል፡፡

ቤዋይ ወንዝ ኬሌን ከአማሮ ተራሮች ጋር የሚያቆራኝ ነው፡፡ የሽቅብን ውበት ቁልቁል ሰዶ ተፈጥሮን ከሰው ልጅ ሲያስታርቅ የሚኖር የፈጣሪ ስጦታ ነው፡፡ ማለዳ ተነሳሁ፡፡ ተራሮቹ በጉም ተሸፍነዋል፡፡ እንደ መንገደኛ ቁልቁል ቀስ እያለ የሚንደረደረው ጉም ሲመሽ ጉዞውን ጀምሮ ሲያቅላላ ኬሌ ከተማ አናት ደርሷል፡፡ ኬሌዎች አሁን ወደ ቤዋይ ወንዝ እየወረዱ ነው፡፡ ቤዋይ ከተራሮቹ አናት ጉዞውን ጀምሮ ያለሁበት ደርሷል፡፡

በጠዋት በዚህ ወንዝ መታጠብ የመንጻት ሥነ-ሥርዓትን ያክል ብዙ ትርጉም ያለው የተለየ ክንዋኔ ነው፡፡ ጦጣዎቹ ከዛፍ ሳይወርዱ፣ ወፎች ከጎጆአቸው ሳይወጡ ሰዎች እዚህ ፌት እንደ መስታወት የሚያሳይ ወንዝ ውስጥ እየገቡ መታጠብ ጀምረዋል፡፡ በየቀኑ እንዲህ ያለ ነገር ለዘመናት ኖሯል፡፡

ኬሌ እንኳን በእድሜዋ ለተከታታይ ሰባ አምስት ዓመታት ይሄንን ትዕይንት አይታለች፡፡ ከዚህ የወንዝ ውስጥ መለቃለቅ በኋላ ቀኑ ብሩህ ነው፡፡ ማልዶ ወንዙ ጋር የደረሰ ታጥቦ ሲጭርስ ጸሐይ ከተራሮች አናት ቁልቁል ትወርዳለች፡፡ አሁን ጉሙ ወደ መጣበት መልሶ መውጣት ጀምሯል፡፡ ወፎች እንሰት በከበባቸው ደኖች ውስጥ ተሸሽገው ማዜም ጀምረዋል፡፡

ኬሌ የምትናፍቀው ቀን መጥቶ በግርግር ልትታመስ በደስታ ቀኑን ጀምራዋለች፡፡ ሁሌም ማክሰኞና ቅዳሜ እንዲህ ነው፡፡ እነኚህ ሁለት ቀናት ይህቺ የአማሮዎች ከተማ ይበልጥ የምትደምቅበት ቀን ነው፡፡ ይህ ቀን ከቀሩት አምስት ቀናት ሁሉ በበለጠ ሩቅ ያሉት ኮሬዎች የሚቀርቡበት የገበያ ቀን ነው፡፡ ወደ ማክሰኞ ገበያ ለመሄድ ቁርስ መብላት ይኖርብኛል፡፡ ከኮሬዎች ጋር ገበያ መዋልን የመሰለ ነገር የለም፡፡ DIRETUBE

Trending

By continuing to use the site, you agree to the use of cookies. more information

The cookie settings on this website are set to "allow cookies" to give you the best browsing experience possible. If you continue to use this website without changing your cookie settings or you click "Accept" below then you are consenting to this.

Close