Connect with us

Ethiopia

መንታ መንገድ ላይ የቆመው ፋሲል ከነማ

Published

on

መንታ መንገድ ላይ የቆመው ፋሲል ከነማ

መንታ መንገድ ላይ የቆመው ፋሲል ከነማ፤

ከስናፍቅሽ አዲስ፤

ሰሞኑን የቡናን ጨዋታ ለመመልከት አንጋፋውን ክለባችንን አጅበን ወደ ጎንደር ተጉዘን ነበር፡፡ ጎንደር በግርግሩ ምክንያት ከገባችበት ድብርት ውስጥ እንዳልወጣች ብዙ ምልክቶችን አይቻለሁ፡፡ ያም ሆኖ ድንገት ፋሲል ከነማ ከቡና መጫወቱ ከተማዋን ከገባችበት ድብርት መንጥቆ ያወጣት ክስተት ሆኗል፡፡

ቅዳሜ እና እሁድን የተለየ ድባብ ነበራት፡፡ ፋሲል ከነማ በርካታ ደጋፊዎች ያሉት ህዝባዊ ክለብ ነው፡፡ እንደ ወላይታ ዴቻ ሁሉ መሠረቱን ህዝብ አድርጎ ወደ ፕሪምየር ሊግ የመጣ ክለብ ነው፡፡ እኛ እኮ የዐፄዎቹ ደጋፊዎች ነን የሚሉት የፋሲል ከነማ ደጋፊዎች የዐፄ ቴዎድሮስን ጃኖ የሚወክል ነው በሚሉት በቀይ የተጌጠ ነጭ ጃኖ አምሳል መለያ ባንዲራቸው ያሸበርቃሉ፡፡ ዜማቸው ሀገርኛ ነው፡፡ ስታዲየማቸው ከሰዓቱ ቀድሞ የሚሞላ፤ ውስጥ እድል አግኝቶ ከሚገባው ይልቅ ቦታ ሞላ ተብሎ በየተራራው እና በየዛፉ እየተንጠለጠለ ክለቡን የሚደግፈው ብዙ ነው፡፡

ቡና ከፋሲል ጋር በሜዳው ያደረገው ጨዋታ እጅግ ደማቅ ነበር፡፡ ዐፄዎቹ በለስ ባይቀናቸውም ጨዋታውን ለማስተናገድ ያደረጉት ዝግጅት ግን እጅግ የሚያስመሰግን ነው፡፡ በዳኛ ላይ ተፈጥሮብናል ባሉት ቅሬታ ሳቢያ የተወሰኑ የፋሲል ከነማ ደጋፊዎች በቁጣ ጨዋታውን ለማስቆም ያስገደደ እርምጃ ቢወስዱም ችግሩ በርዶ ሙሉ ጨዋታውን ተቋርጦም ቢሆን ቀጥሎ ሊጠናቀቅ ችሏል፡፡

ፋሲል ከነማን ዳሽን ቢራ ስፖንሰር አድርጎታል የሚለው ዜና ግን ሁሉን እኩል ያስፈነደቀ አልነበረም፡፡ ይልቁንም ብዙዎች አሁን ገና ክለቡ መንታ መንገድ ላይ ቆመ ሲሉ አድምጫለሁ፡፡ እኔ በነበርኩበት አካባቢ ስታዲየም ውስጥ የዳሽን አርማ ያለበት ማለያ የለበሱ የፋሲል ደጋፊዎች በወጣቱ ቁጣ ሲገጥማቸው ተመልክቻለሁ፡፡ ፋሲል ከነማ ህዝባዊ ክለብ ቢሆንም የበጀት ችግር እየገጠመው እንደሆነ ጭምጭምታዎች ይሰማሉ፡፡

የዳሽን ቢራ የከተማዬ ስፖርት ክለብ ነው በሚል ክለቡን ለአምስት አመት የዋና ስፖንሰርነት ስምምነት ለመውሰድ ያቀረበው ጥያቄ ገንዘቡ ይጨምር አይጨምር በሚል ክርክር ውስጥ ገብቶ ነበር፡፡ በኋላም ለአምስት አመት 75 ሚሊዮን ብር በሚጠጋ ገንዘብ አጋር ስፖንሰር ሆኖ ስምምነት ላይ መደረሱ መደበኛ ባልሆነ መንገድ መወራት ጀምሯል፡፡

በቡና እና ፋሲል ጨዋታዎች ከኤርፖርት ጀምሮ በጎዳናዋ አደባባዮች እና በስታዲየሙ ዙሪያ ዳሽን ዋና የክለቡ አጋር መሆኑን የሚገልጹ ባነሮች ተሰቅለው ነበር፡፡ በተመሳሳይ የዳሽንን አርማ የያዙ ማሊያዎችም ተሰራጭተው ነበር፡፡ አንዳንዶች ቅሬታችን ጀመረ የሚሉት እዚህ ላይ ነው፡፡ የምንደግፈውን ክለብ ስፖንሰር እንደ ተቃራኒ ቡድን ሰርፕራይዝ ተደርገናል በሚል አንድ ብለው ይጀምራሉ፡፡

ክለቡ በቂ የፋይናንስ ምንጭ የለውም ዳሽን ደግሞ ከከተማዋ የንግድ እንቅስቃሴ ቀጥተኛ ተጠቃሚ ነው ስለሆነም ክለቡን በስፖንሰር መደገፉ ትክክለኛ ነው የሚል እምነት ያላቸው አሉ፡፡ በተቃራኒው ፋሲል ከነማ እዚህ የደረሰው በጎንደር ልጅ የተባባረ ክንድ እንጂ በሌላ አካል አይደለም፡፡ ዳሽንም ቢሆን በአንድ ከተማ ሁለት ቡድን ፈጥሮ የነበረ ተፎካካሪያችን የነበረበትን ጊዜ መርሳቱ ያስተዛዝባል የሚሉም አሉ፡፡ ሌሎች ደግሞ የቅሬታቸው መነሾ ከግል ፍላጎት የመነጨ እንደሆነ ነው የሚነገረው፡፡

ለምሳሌ ፋሲል እዚህ እንዲደርስ አስተዋጽኦ ካበረከቱ አካላት መካከል የቅዱስ ጊዮርጊስ ቢራ ፕሮሞተሮች የአንበሳውን ድርሻ ይይዛሉ፡፡ እነኚህ ወገኖች ለክለቡ ማደግ እና እዚህ መድረስ ገንዘባቸውንም ጊዜያቸውንም የሰው ናቸው፡፡ የእኛ ያሉት ክለብ የሌላ ሆነ ስለተባለ ቅሬታ ውስጥ ገብተዋል፡፡

ያለ ጨረታ ለምን ለዳሽን ተሰጠ የሚሉም አሉ፡፡ በርካታ ሙስሊም ጎንደሬዎች የሚዘምሩለት ፋሲል ከነማ ከቢራ ከተጋባ የእኛ ልንለው እንችላለን በሚል ሃይማኖትን መሰረት ያደረገ አጣብቂኝ ውስጥም የገቡ አሉ፡፡ ፖለቲካውም ስፍራ አለው፡፡ በጎንደር ተነስቶ ከነበረው ተቃውሞ ጋር ተያይዞ ዳሽን ላይ ያለመጠቀም አድማ ተቀስቅሶ ነበር፡፡

ስለሆነም በዳሽን ከነማው ስፖንሰር መደረጉ ዳሽን የጥረት ንብረት ከመሆኑ ጋር በተገናኘ መንግስትን እንደማስደሰት የሚቆጥሩት ብዙ ናቸው፡፡ አሁን ይሄ አንጋፋ ክለብ አጣብቂኝ ውስጥ ነው፡፡ የትኛውን መንገድ እንደሚመርጥ በእርግጠኝነት ለማናገር ይከብድ ይሆናል፡፡ የብዙዎች ምኞት ግን ፋሲል ከነማ አሁንም የፕሪምየር ሊጉ ጌጥ ሆኖ ከእነኚህ የኳስ ፍቅር ካሳበዳቸው ደጋፊዎቹ ጋር አብሮን ይዘልቅ ዘንድ ምኞቴ ነው፡፡

DIRETUBE

Trending

By continuing to use the site, you agree to the use of cookies. more information

The cookie settings on this website are set to "allow cookies" to give you the best browsing experience possible. If you continue to use this website without changing your cookie settings or you click "Accept" below then you are consenting to this.

Close