Connect with us

History

ዝክረ ዓድዋ……. ከዕለት ወረት፤ ወደ ዘላቂ ለዓመታት

Published

on

ዝክረ ዓድዋ....... ከዕለት ወረት፤ ወደ ዘላቂ ለዓመታት

ዝክረ ዓድዋ……. ከዕለት ወረት፤ ወደ ዘላቂ ለዓመታት /ከትውልዱ የሚጠበቅ ዓቢይ ጉዳይ/
ካሣ አያሌው ካሣ…………… የካቲት 23/2009ዓ.ም

‹‹በ20ኛው ክፍለ ዘመን ዓለም ትኩረትና ፊቱን ኢትዮጵያ ላይ እንዲያደርግ ካስገደዱት ጥቂት ክስተቶች መካከል አንዱና ዋናው የዓድዋ ድል ነው›› በማለት ታዋቂው የታሪክ ሊቅ ባህሩ ዘውዴ ያስረዳሉ፡፡

ሄንዝ የተባለው ስመጥር እንግሊዛዊ የታሪክ ተንታኝ <<The History of Ethiopia>> በተሰኘው መፅሐፉ ‹‹በጣሊያንና በኢትዮጵያ መካከል በዓድዋ የተካሄደው ጦርነት በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ እጅግ ደማቁና አገሪቱ በዓለማቀፍ መድረክ በነበራት ቦታ ላይ ከፍተኛ የግንዛቤ ለውጥ ያመጣ የታሪክ ነፀብራቅ ነው›› ሲል በዓድዋ የተገኘውን ኢትዮጵያዊ ድል ገልፆታል፡፡

የዓድዋ ድል በዓለም ታሪክ ላይ በተለይም አውሮጳውያን አፍሪካን ለመቀራመት ተስማምተው በርካታ አገራትን በቅኝ ግዛት ስር ከትተው ሲመዘብሩ በከረሙባቸው በእነዚያ ዘመናት፤ በእንዲህ ያለ ክፉ ድርጊታቸው አንገታቸውን እንዲደፉ ያደረገ ሲሆን፤ ለመላዎቹ አፍሪካዊ ጥቁር ህዝቦች ደግሞ ካቀረቀሩበት የባርነት ጫና ቀና እንዲሉ ዕድል የፈጠረ ነው፡፡ ለዚህም ነው ‹‹የዓድዋ ድል የመላ ነፃነት ናፋቂ ጥቁር ህዝቦች ድል ነው›› የሚባለው፡፡

የአፍሮ ሴንተሪክ ታሪክ ተመራማሪ የሆነው ሞሌፍ አሳንቴ ይህንን አስተሳሰብ ‹‹ኢትዮጵያ በ 1996 ዓ.ም /እ.ኤ.አ/ በጣሊያን ላይ የተቀዳጀችው ድል ለመላ አፍሪካውያን አዲስ የነፃነት ጎዳናን ያመላከተ ነው፡፡ ይህንን ድል ተከትሎ በተለያዩ አፍሪካዊ ቅኝ ተገዢ አገራት የፀረ ቅኝ ግዛት ንቅናቄዎችና የነፃነት ፋኖዎች ሊፈጠሩ ችለዋል፡፡ ኢትዮጵያም በዚህ የዓድዋ ድል ምክንያት የመላ አፍሪካውያን ኩራትና ተስፋ ለመሆን በቅታለች፡፡ አውሮጳዊ የቅኝ ግዛት ተቅበዝባዦችም በአፍሪካውያን ላይ ያላቸውን ከንቀት የሚመነጭ አስተሳሰብ ቆም ብለው እንዲፈትሹ አስገድዷቸዋል›› በማለት አረጋግጧል፡፡

እንዲህ የሚዘከርለትና የሚነገርለት የዓድዋ ድል ባለቤቶች እኛ ኢትዮጵያውያን ነን፡፡ ለወቅቱ ንጉሳችን አፄ ምኒልክና በዙሪያቸው የነበሩ የጦር አዛዦች እንዲሁም ለመላው የዚያ ዘመን ጀግኖች አባቶቻችን ክብርና ሞገስ ይግባና፤ ደማቸውን አፍስሰውና አጥንታቸውን ከስክሰው እንደ ታፈረችና እንደተከበረች ይህችን ድንቅ አገር አውርሰውናል፡፡

እኛ የዚህ ዘመን ትውልዶች የወረስነው እንዲህ ያለ ታላቅና ደማቅ ታሪክ ገብቶናል ወይ? ብዬ ስጠይቅ ውስጤ የሚሰጠኝ ምላሽ ያስደነግጠኛል፡፡ እውን ገብቶን ከሆነ…… የታለ በኪነ-ጥበብ ስራችን ያወሳነው፡፡ ከየካቲት 23 በቀር መቼ ነው ሚዲያዎቻችን ከአውሮጳ ሊግ እግርኳስ ዝባዝንኬ በምትተርፈው ኩርማን ሰዓት እንኳን ድላችንን ነግረውን የሚያውቁት፡፡ የቱ ጋር ነው ህዝብና መንግስት ሁላችንም፤ በአገር ዓቀፍና ዓለማቀፍ አደባባይ ይህንን ታሪካዊ ድል የገፅታ ግንባታችን አንዱና ዋና ጉዳይ አድርገን የሸጥነው፡፡ አረ መቼስ ነው ድሉን ትውልድ ተሻጋሪ ለማድረግ በትምህርት ካሪኩለማችን ያካተትነውና በየምልዐተ ህዝቡ ዓውድ ላይ የሰበክነው፡፡ መቼና የቱ ጋርስ ነው ይህ ታላቅ የጥቁር ህዝቦች ድል የመላ አፍሪካውያን ድል ሆኖ እንዲዘከር ጫና ያሳረፍነው፡፡ …………. አረ ስንቱ……….

እነኝህ ሁሉ የቤት ስራዎቻችን አልተሰሩም፡፡ ስለዚህም የዓድዋ ድልን የካቲት 23 ከመዘከር በዘለለ ቋሚ የታሪክ ቅርስ አድርገን ማቆየት ካስፈለገ /ያስፈልጋልም/ ከዝክር ቀን ያለፈ ብዙ ስራ ይጠበቅብናል፡፡ የትውልድ ንቃተ ህሊና አስፈላጊነቱ እዚህ ላይ ነው፡፡ አልያ እንዲህ ያለ ታላቅ ድል እንደ ጨው ሟምቶና እንደ ወረት ፍቅር ደብዝዞ መጥፋቱ የሚያጠያይቅ አይደለም፡፡

DIRETUBE

Trending

By continuing to use the site, you agree to the use of cookies. more information

The cookie settings on this website are set to "allow cookies" to give you the best browsing experience possible. If you continue to use this website without changing your cookie settings or you click "Accept" below then you are consenting to this.

Close