Connect with us

Business

አንበሳ ሲያረጅ…… አንበሳ አውቶቢስን ከአዲስ አበቤዎች ልብ ማውጣት ይቻል ይሆን?

Published

on

አንበሳ አውቶቡስ

ከአዲስ አበባ ቢሸፍቱ ሲሰራ ያልከሰረው እንዴት የቢሸፍቱ ባስ ሲያስገባ ተራቆተ?
አንበሳ አውቶቢስን ከአዲስ አበቤዎች ልብ ማውጣት ይቻል ይሆን? (ከስናፍቅሽ አዲስ)

ማንንም የአዲስ አበቤ ሰው አንበሳ አውቶቢስ ምንህ ነው ብትሉት ንብረቱ እንደሆነ ይነግራችኋል፡፡ የዛሬ 73 ዓመት ገደማ ንጉሣዊው ቤተሰብ እንደ ግል ንብረት ሊጠቀምበት የመሰረተው ኢንቨስትመንት መሆኑን ዛሬ ማንም ትዝ ብሎት አያውቅም፤ እንደስሙ አንበሳ ኾኖ ሰባት አስርት ዓመታትን ከአዲስ አበቤዎች ጎን የቆመ አንጋፋ እና ባለውለታ ድርጅት ነው፡፡

ዛሬ የአዲስ አበባን ጎዳናዎች ተሸማቆ የሚጎተትባቸው የአንበሳ አውቶቢስ የዛሬን አያድርገው እና ያኔ እንዲህ እንደአሁኑ ሺ አውቶቢስ አለኝ ሳይል በጣት በሚቆጠሩ አውቶቢሶች አዲስ አበባን ተርመስምሶባት ነበር፡፡

ዛሬ ከ850 በላይ አውቶቢሶች ኖረውት ግማሹን በአግባቡ ለአዲስ አበቤዎች ማድረስ አቅቶት በተገኘው አውቶቢስ ሁሉ ሲታገዝ ይውላል፡፡ አንዳንዴ አንበሳ አረጀ እንዴ? ብዬ እጠይቃለሁ፡፡ ሰሞኑን ደግሞ የምሰማው ነገር አንበሳ ሲያረጅ እንድል አስገድዶኛል፡፡ 900 ሚሊዮን ብር የወጣባቸው የቢሾፍቱ የከተማ አውቶቡሶች አንበሳ አውቶብስን ለከፍተኛ ወጪ ዳርጎታል የሚለው ዜና ዳር እስከ ዳር እየደረሰ ነው፡፡

አንበሳ አደጋ የገጠመው ስሙን ሰላሳ መልኩን አስር ቁመቱን ብዙ ያደረገ ሲመስለኝ ነው፡፡ አሁን ደግሞ ዳፍ ያንቀጠቀጠው የአዲስ አበቤ የገበጣ መንገድ በሀገር ልጅ በተገጣጠመ መኪና ልክ ይገባል ተብሎ በመከላከያ ኢንጂነሪንግ የተሰሩትን የቢሸፍቱ አውቶቢሶች እንዲገዛ የተደረገው አንበሳ ከለገሀር ቢሸፍቱ በሁለት ብር ሰው ሲያመላልስ ኖሮ ያልከሰረውን በሀገር ልጅ ምርት ከጥቅም ውጪ ሆነ የሚለው ዜና ናኝቷል፡፡ በእርግጥ የቢሸፍቱ አውቶቢስ መገጣጠሚያ እንደ ሀገር ጅምሩ የሚያኮራን ነው፡፡ ችግሩንም ጥራቱንም ልንቋቋመው የምንችለው ከዜሮ ጀምረን እያደግን ስንሄድ ነው፡፡ ኪሳራው ስኬት ሆኖ ካስፈነጠዘን ግን እድገቱም ቁልቁለት ይሆንና አንበሳ አውቶቢስ ላይ የገጠመው ችግር እየገዘፈ ይመጣል፡፡

መረጃዎች አንበሳ 550 አውቶቡሶች ከቢሸፍቱ ገዝቶ ግማሾቹ ከጥቅም ውጪ መሆናቸውን ያሳያሉ፡፡ አንዱ አንበሳ ሞቶ ሌላው ቆሞ እንዲሄድ አንዱን እያረዱ ለሌላው መለዋወጫ ማድረጉም እንደ አማራጭ ገንግኗል፡፡ እኛ አዲስ አበቤዎች ይሄንን ለመረዳት በአንድ ደመወዝ ሁለት አውቶቢስ የሚነዱ የድርጅቱን ሹፌሮች ማነጋገር አይጠበቅብንም፡፡ የከተማችን ጎዳና ላይ ቆመን የምናየው በቂ ነው፡፡

አምስት ዓመት ያልሞላው አኮርዲዮን መሳይ አውቶቢስ መጋጠሚያው እንደ ደሃ ልብስ ተቦጫጭቆ እያየነው ነው፡፡ ለሃያ ዓመት ይሰራሉ የተባሉ አውቶቢሶች ስድስት ወር ላይ ወገቤን ሲሉ ጉዳዮን በመመርመር ፈንታ የአውቶቢሱን ቁጥር በየቀኑ እንደ አሸን እያፈሉ በሞተው ምትክ አዲስ መውለድ ሀገርንም ለኪሳር የሚዳርግ አሰራር ነው፡፡

ስድስት ወር ያልሰራ አውቶቢስ ሞተሩ እየወረደ ነው የሚሉ ሹፌሮችን ሰሚ ጆሮ ያስፈልጋል፡፡ በአመት ከአንድ መቶ በላይ አውቶቢስ ከጥቅም ውጪ እያደረግን ሰባ አምስት ዓመታትን የኖረ የህዝብ ትራንስፖርት ድርጅት በወር አንድ ሚሊዮን ብር ደጉመን በአመት ሰባ ሚሊዮን ብር አክስሮን ለእሱ አውቶቢስ የሚሸጠውን ድርጅት አትረፈ፣ ገነነ፣ ሀገሪቱ ራሷን ቻለች ማለት የእብድ ቀልድ ይመስለኛል፡፡

አንበሳ አሁን የአዲስ አበባን ህዝብ ከሚያገለግለው ይልቅ መለዋወጫ አቅራቢዎችን የሚጠቅም ተቋም እየሆነ ሲመጣ ቆም ብሎ መምከር የሚመለከታቸው ሰዎች ሃላፊነት ይመስለኛል፡፡ በተለይም የአዲስ አበባ ከተማ የስራ ሃላፊዎችን ከተጠያቂነት አያድንም፡፡ የድርጅቱ ሰራተኞች የጉዳዩን ግዝፈት ፊርማ በማሰባሰብ አቤት እስከማለት ደርሰው ዝም ማለት ወንጀልም ይመስለኛል፡፡ 550 አውቶቢሶችን ከመከላከያ ኢንጂነሪንግ ሲገዛ 900 ሚሊዮን ብር ወጪ ያወጣው ትርፍና ኪሳራውን በገበያ ህግ ሳያጠና መሆኑን ውጤቱ ምስክር ነው፡፡

አውቶቢሶች ሃያ ዓመት ድረስ ያገለግላሉ ከተባለ ለደረሰባቸው ችግር ተጠያቂው አምራቹ ነው፡፡ ይሄ የዓለም የገበያ ህግ ነው፡፡ ይሄን ጥሶ እንደ ጃፓን ለመሆን እንደ ቻይና ራሳችንን ለመቻል መንገድ ላይ ነን የሚለው ቀልድም ይመስለኛል፡፡ አሁን አንድ ቦታ ልጠቁማችሁ አምቼ ሂዱ፤ ከፈለጋችሁ መካኒሳ ብቻ የቆመውን አውቶቢስ ብዛት እዩት፣ የበቀለበት ሳር ተመልከቱ እናም ትርፋማ እና ስኬታማ ነን በሚል የአንድ ተቋም ሰዎች ለሹመት ለሽልማት እንዲበቁ የሌላ ተቋም ሰራተኞችን እስከ መበተን የሚያደርስ፣ በእጅ አዙር በግዙፍ በጀት በሚደጎም የህዝብ ትራንስፖርት ሙድ መያዝ ይመስለኛል፡፡

የአንበሳ አውቶቢስ አንድ የስራ ሃላፊ በአዲስ ዘመን ጋዜጣ የአውቶብሶቹ ችግር የጥራት እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡ የጥራት ችግር ባይርባቸው ኖሮማ እንዴት ከ15 እስከ 20 ዓመት ሊያገለግሉ የተሠሩ አውቶቡሶች በአራት ዓመት ዉስጥ ይህን ያህል ይበላሻሉ ሲሉም ጠይቀዋል፡፡ መከላከያ ኢንጂነሪንግ ደግሞ ከአገልግሎት አሰጣጡ እና ከአጠቃቀሙ ጋር በተያያዘ የተከሰተ መሆኑን ነው የተናገረው፤ እኔ ደግሞ አዘንኩ አንድ ቢሊዮን ብር በሚጠጋ ገንዘብ እከሌ እከሌ ነው እያለ አለቃ የሌላቸው ይመስል ጉዳዪን መንግስት በዝምታ ማለፉ አሳስቦኛል፡፡

የጊዜ ጉዳይ ነው እንጂ እንደ ህጋችን ያጠፋም ጥፋት የደበቀም ተጠያቂ ናቸው፡፡ በምንንም ሁኔታ ውስጥ ግን አንበሳን ከአዲስ አበቤዎች ልብ ማውጣት አይቻልም፡፡ DIRETUBE NEWS

Trending

By continuing to use the site, you agree to the use of cookies. more information

The cookie settings on this website are set to "allow cookies" to give you the best browsing experience possible. If you continue to use this website without changing your cookie settings or you click "Accept" below then you are consenting to this.

Close