ዛምቢያ ሴቶች የወርአበባ ሲያዩ ፍቃድ እንዲሰጣቸው ህግ አወጣች

0
1705

አንዲት አፍሪካዊት ሀገር ሴቶች የወር አበባ በሚያዩበት ወቅት ለቀጣሪ ድርጅቶቻቸው ደውለው በማሳወቅ እረፍት መውሰድ እንደሚችሉ ደንግጋለች።

ደቡብ አፍሪካዊቷ ዛምቢያ ነች ይህን መብት ለሴቶች የፈቀደችው።

ይህ ልማድ “የእናቶች ቀን” እየተባለ የሚጠራ ሲሆን፥ በሀገሪቱ የሰራተኞች ህግ እንዲካተት መደረጉ ተገልጿል።

የወር አበባ (ፔሬድ) የሚለውን ቃል መጥራት በዛምቢያ እንደ ነውር የሚቆጠር በመሆኑ ነው ኡደቱ “የእናቶች ቀን” በሚል የተሰየመው።

የወር አበባ ሲያዩ ወደ ስራ ገበታ ማምራት ያልቻሉ እና ህመም የተሰማቸው ሴቶች ወደ አሰሪዎቻቸው ደውለው ፈቃድ በመውሰድ በስራ ገበታ ላይ አለመገኘት ይችላሉ ነው የተባለው።

ነገር ግን ሁሉም የወር አበባ ያዩ ሴቶች አይደሉም ከስራ ገበታቸው እንዲቀሩ የሚፈቀድላቸው፤ በዚህ ኡደት የተነሳ ህመም የሚሰማቸው ብቻ እንጅ።

በወርሃዊ ኡደቱ ምክንያት ህመም የተሰማቸው ሴቶች ፈቃድ ጠይቀው የከለከለ ድርጅትም በህግ ተጠያቂ ይሆናል ተብሏል።

ፈቃድ ሳይጠይቁ እና ህመም ሳይሰማቸው የሚቀሩ ሰራተኞችም በህጉ ተጠያቂ ይሆናሉ ብለዋል የሀገሪቱ የሰራተኛ ጉዳይ ሚኒስትር ኖንዴ ሲሙኮኮ።

ፈቃድ ጠይቀውና ከስራ ቀርተው ፀጉራቸውን ሊሰሩ ወጣ ያሉም ሆነ ለሸመታ ወደ ሱቅ ወጥተው የተገኙ ሴቶች እስከመባረር የሚደርስ ቅጣት ይጠብቃቸዋል ነው ያሉት ሚኒስትሩ።

“የእናቶች ቀን” ፈቃድ ተሰጥቷት በእርሻ ስራ ላይ ተሰማርታ የተገኘች ሴት ከስራ መሰናበቷንም ለአብነት አንስተዋል።

ህጉ መልካም ብስራት ነው የሚሉ በርካታ ሴቶች ቢኖሩም ምርታማነትን ይቀንሳል የሚል ስጋት ያላቸውም አልጠፉም።

በሀሰት አሞናል እያሉ ከስራ የሚቀሩ ሴቶችን መጠንም ይጨምራል የሚሉ አሉ።

ከዛምቢያ ባሻገር በቻይና ሶስት ግዛቶች (ሻንሺ፣ ሁቤይ እና ኒንግሺያ) በወር አበባ ምክንያት ለህመም የሚዳረጉ ሴቶች የአንድ ቀን እረፍት እንዲወስዱ ይደረጋል። ፈቃድ የሚከለክሉ ድርጅቶችም ቅጣት ይጠብቃቸዋል።

READ  ደሞዝ አልተከፈለኝም በሚል ሰበብ የአሰሪውን ሴት ልጅ አግቶ 218 ሺህ ብር የጠየቀው ምግብ አብሳይ በቁጥጥር ስር ውሏል

ጃፓን በ1947 ተመሳሳይ ህግ ያወጣች ሲሆን፥ ኢንዶኒዥያ፣ ደቡብ ኮሪያ እና ታይዋንም እንዲሁ ተመሳሳይ ህግ አላቸው።

የኢንዶኒዥያ ሴቶች ይህን መብት ብዙ ጊዜ አይጠቀሙበትም ተብሏል። ምክንያቱም ቀጣሪ ድርጅቶች ፈቃድ ጠያቂ ሴቶች በእርግጥም በወር አበባ የተነሳ ህመም እንደተሰማቸው ለማረጋገጥ ምርመራ እንዲያደርጉ ስለሚያስገድዷቸው ነው።

ይህን መሰሉ ህግ በምዕራባዊያኑ የተለመደ አይደለም።

ሩስያ በ2013 ነበር ሴቶች የወር አበባ ባዩበት ቀን እረፍት እንዲያደርጉ ያለመ እቅድ ለመጀመሪያ ጊዜ ይፋ ያደረገችው፤ ይሁንና ይህ እቅድ ወደ ህግነት አልተቀየረም።

NO COMMENTS