Connect with us

Ethiopia

ሙያዊ ሥነ-ምግባር – የሕዝብ አገልጋይነት… ???

Published

on

ሙያዊ ሥነ-ምግባር

ሙያዊ ሥነ-ምግባር – የሕዝብ አገልጋይነት… ???
(መላኩ አላምረው)

ለመወቃቀስ አይደለም፡፡ ግን ግልጽ እንነጋገር፡፡ ችግር ውስጥ ነን፡፡ መፍትሄ ያሻል!!!

ሰሞኑን አንድ የሸገር ኤፍ.ኤም. ጋዜጠኛ በአዲስ አበባ መንገዶች እተዘዋወረ የደንብ ልብስ ለብሰው ‹‹በሥራ ላይ ነን›› ያሉ ፖሊሶችን ስለ አንዳንድ በፖሊስ ሊታወቁ የሚገባቸው መረጃዎች እየጠየቃቸው ነበር፡፡ ያገኘው ምላሽ ግን ያስደነግጣል፡፡

ሌላውን ሁሉ ትተነው ‹‹የፖሊስ የአስቸኳይ (የአደጋ) ጊዜ ጥሪ ቁጥርን›› ያወቁት ከ53 ፖሊሶች 3ቱ ብቻ ናቸው፡፡ ሦስቱ ብቻ፡፡

(((፡ከዚህ ላይ ቁጥሩን ማወቅ በራሱ የብቁ ፖሊስነት መለኪያ ነው ወይም አለማወቅ ከፖሊስነት አያስመድብም እያልሁ እንዳልሆነ ይሰመርልኝ፡፡ ነገር ግን ‹‹ለአደጋ ጊዜ በአስቸኳይ ለመድረስ ዝግጁ ነኝ›› ብሎ መለያውን ለብሶ በሥራ ላይ ያለ ፖሊስ የሚጠራበትን ቁጥር (ለመረጃ ያህል እንኳን) አለማወቅ በምንም መስፈርት ትክክል የሚሆን አይመስለኝም፡፡)))

ይህንን የፖሊሶች ጉዳይ እንደአጋጣሚ ሰምቸው ስላስገረመኝ አነሳሁት እንጅ በሁሉም የሥራ ዓይነት የሙያዊ ሥነ-ምግባርና የአገልጋይነት (በሁሉም መንገድ ዝግጁ የመሆን) ጉዳይ በህመም ላይ ያለና የሚታደገውን ሐኪም ካላገኘም እየሞተ የሚሄድ ስለመሆኑ ብዙ መገለጫዎችን ማንሳት ይቻላል፡፡

በየትኛውም ቦታ ለሙያቸው ታማኝና በሥነ-ምግባራቸውም ምስጉን የሆኑ የሕዝብ አገልጋዮች (በጥቂት ቁጥርም ቢሆን) መኖራቸው ባይካድም…. በየሐኪም ቤቶች ያለው ሐኪሞችና ነርሶች ሕሙማንን የሚያስተናግዱበት መንገድ፣

በየኮሌጆችና ዩኒቨርሲቲዎች አልፎም በሃይስኩሎች አካባቢ የሚታየው የመምህራንና የተማሪዎች መስመር የማለፍ ነገር (ተማሪም መምህርም)፣ በየ‹‹ሲቪል ሰርቪስ›› ተቋማቱ (ከፌደራል እስከ ቀበሌ) ያለው የመንግሥት ሠራተኞች ሁለንተናዊ ቁመና (የአገልግሎት ዲሲፕሊን)፣ ወዘተ…. በደንብ ቢፈተሸ አስደንጋጭም አሳዛኝም ነው፡፡

አመንም አላመንም ከሙያዊ ሥነ-ምግባር አንጻር ሀገራችን ትልቅ ችግር ውስጥ ናት፡፡ በየሙያው ያልተሰላቸና የማያማርር ሠራተኛ በየትኛው ተቋም ይገኛል? የደመወዝንም ሆነ የሌላ ጥቅማጥቅምን መጓደል መሠረት አድርጎ ለሚያገለግለውን ሕዝብ ጀርባውን ያልሰጠስ? (ሕዝብ ከዚህ አንጻር ምንድነው ጥፋቱ? ግብር የመክፈል ግዴታውን እየተወጣ ተገቢውን አገልግሎት የማግኘት መብት የለውም? ይህንን አገልግሎትስ ማን ይስጠው? የአገልግሎት ቦታውን የያዝን አይደለንምን?
እንተማመን፡፡

በሀገራችን ያለው ሙያዊ ሥነ-ምግባር (Discipline) ወርዷል (እየጠፋ ነው)፡፡ በጣም ጥቂት ከሆኑ ምስጉኖች በስተቀር…. በማንኛውም የሥራ ዘርፍ ተመድበን ‹‹ለሙያችን ታማኝ፣ ቅን፣ ሐቀኛ፣ ኃላፊነታንን የምንወጣ…….. የሕዝብ አገልጋዮች ነን›› የምንልና 12ቱን የሥነ ምግባር እሴቶች በየቢሯችን የለጠፍን ሁሉ (በየቤታችንም የለጠፍን አንጠፋም) በተግባር ስንፈተሽ ባዶ ነን፡፡

በደመወዝ ማነስም ሆነ በጥቅማጥቅም የሚጎዳን ሌላ….. ተገቢውን አገልግሎት በመንፈግ የምናሰቃየው ሌላ፡፡

ሙያዊ ሥነ-ምግባር ማለት የደንብ ልብስ መልበስና ሰዓት ማክበር ብቻ የሚመስለን ስንቶቻችን ነን? ስለምንሰጠው አገልግሎት ጠንቅቀን የምናውቅና ምንም ዓይነት የመረጃ ክፍተት የሌለብንስ ስንት እንሆን ይሆን?

እንታረም፤ እንተራረም፡፡ መንግሥትም አገልጋዩን ይመልከት፡፡ ዋናው የቤት ሥራ የእርሱ መሆኑን ይወቅ፡፡ የሕዝብ አገልጋዩ የሚጎድለውን ያሟላ፡፡ በሥራው ልክ ይከፈለው፡፡ አገልጋዩም ሙያዊ ሥነ-ምግባሩን አክብሮ ያገልግል፡፡

ያለበለዚያ ይህች ‹‹ውድ ሀገራችን›› እያልን የምንመጻደቅባት ሀገር ለመጨው ትውልድ ሲኦል እየሆነች ነው፡፡ ሁላችንም፣ እያንዳንዳችንም ተጠያቂዎች ነን፡፡ DIRETUBE NEWS
—–//—–

Trending

By continuing to use the site, you agree to the use of cookies. more information

The cookie settings on this website are set to "allow cookies" to give you the best browsing experience possible. If you continue to use this website without changing your cookie settings or you click "Accept" below then you are consenting to this.

Close