Connect with us

Ethiopia

የአገር መከላከያ ሠራዊትን በመክዳት የተጠረጠሩ ወታደሮችና ግለሰቦች ተከሰሱ

Published

on

የአገር መከላከያ ሠራዊትን በመክዳት

የአገር መከላከያ ሠራዊትን በመክዳት የፀረ ሽብርተኝነት አዋጅን በመተላለፍ፣ የሽብር ተግባር ለመፈጸም ሲንቀሳቀሱ በቁጥጥር ሥር ውለዋል የተባሉ ወታደሮችና ግለሰቦች ክስ ተመሠረተባቸው፡፡

ተከሳሾቹ የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) እና የአርበኞች ግንቦት ሰባት አባል መሆናቸውን የሚገልጸው የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ክስ፣ ወደ ኤርትራ በመሄድ የድርጅቶቹን ወታደራዊና ፖለቲካዊ ሥልጠና መውሰዳቸውን ያስረዳል፡፡

አድራሻቸው ኤርትራ መሆኑ የተገለጸው ተከሳሾች አወል አባጊዲና ሰይድ መሐመድ የአገር መከላከያ ሠራዊት አባል እንደነበሩ ክሱ ይገልጻል፡፡ የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል፣ የኦሮሚያ ክልልና የሰሜን ሱዳን ነዋሪዎች መሆናቸውን የተገለጸው ተከሳሾች ሰይድ መሐመድ፣ አንዱዓለም ያሲንና ሰሚራ አማን የተባሉት ተከሳሾች ደግሞ፣ በኦነግና በግንቦት ሰባት አባላት የተመለመሉ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡

አወል የተባለው ተከሳሽ አሰብ አውሮፕላን ማረፊያ ደባዋና ኪሎማ በተባሉ አካባቢዎች የድርጅቶቹ ታጣቂ በመሆን፣ የገቢ ማስገኛ ሥራዎች ላይ ተሰማርቶ እንደበር ክሱ ይገልጻል፡፡ በኦነግ ማሠልጠኛ ከሚገኙ 500 የቡድኑ አባላት ጋር ወታደራዊና ፖለቲካዊ ሥልጠና ለሦስት ወራት ያህል ከሠለጠነና ካጠናቀቀ በኋላ፣ የቡድኑ ጦር መሪ በመሆን ሲሠራ ቆይቶ በግንቦት ወር 2008 ዓ.ም. የቡድኑ ጋንታ አዛዥ ሆኖ ታጣቂዎችን ሲመራ እንደነበር ክሱ ያብራራል፡፡

ተከሳሹ የመከላከያ ሠራዊት አባል ከነበረው ጓደኛው ሙሉጌታ ቂጤሳ ጋር በመሆን በሰሜን ሱዳን በኩል ወደ ኢትዮጵያ በመግባት ሕዝቡን ለአመፅ እንዲያነሳሱ፣ አባላትን እንዲመለምሉና እንዲያደራጁ እንዲሁም ለወታደራዊ ቤዝ የሚሆን ቦታ እንዲያጠኑ የሚረዳቸው ተልዕኮ ማስፈጸሚያ 600 የሱዳን ፓውንድ ተቀብለው ሲንቀሳቀሱ እንደነበር በክሱ ተጠቅሷል፡፡ ከሰሜን ሱዳን መታወቂያ ተሠርቶላቸውና ድንገት በኢትዮጵያ የፀጥታ ሠራተኞች ቢያዙ እንዴት ዋሽተው ማምለጥ እንደሚችሉ ሥልጠና ተሰጥቷቸው፣ በገላባት በኩል ወደ መተማና ባህር ዳር ከገቡ በኋላ፣ ወደ ቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል መሄዳቸውን ክሱ ያብራራል፡፡

በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ ዞን ነዋሪ መሆኑ የተገለጸው አንዱዓለም ያሲን የተባለው ተከሳሽ ደግሞ የአርበኞች ግንቦት ሰባት ድርጅት አባል መሆኑ፣ መአዛው ጌጡ ከተባለ የድርጅቱ አመራር ጋር ኡመሀጅር በተባለ ቦታ ተገናኝተው ወደ ሥልጠና ገብቶ ለሦስት ወራት ያህል በአደም ደሚቶ ማሠልጠኛ መሠልጠኑ ተገልጿል፡፡ ተከሳሹ የአሠልጣኝነት ሥልጠና ለአንድ ወር ከወሰደበትና የአርበኞች ግንቦት ሰባት ወታደራዊ አሠልጣኝ ሆኖ ሲሠራ ከቆየ በኋላ፣ ለአምስት ቀናት የደኅንነት አሠራር ሥልጠና በመውሰድ የመረጃና ደኅንነት ሠራተኛ ሆኖ መመደቡንም ክሱ ይገልጻል፡፡

ለአርበኞች ግንቦት ሰባት የአገር ውስጥ አባላት በተንቀሳቃሽ ስልክና በፌስቡክ በመጠቀም አዳዲስ አባላት እንዲመለምሉ መመርያ ሲሰጥ እንደነበርና በደብረ ዘይትና በተለያዩ ቦታዎች ለሚገኙ አባላት በተለይ የመከላከያ ሠራዊት አባላትን እንዲመለምሉ መመርያ ሲያስተላልፍ እንደነበር ተገልጿል፡፡

ተከሳሹ የአርበኞች ግንቦት ሰባት አባል ከሆነበት ወቅት አንስቶ ብዙ ነገሮች የሠራ ከመሆኑም በተጨማሪ፣ በተለያዩ መንገዶች የመረጃና ደኅንነት ሠራተኞች በሴል ሲያደራጅ እንደነበር ተገልጿል፡፡ ተከሳሹ በደብረ ዘይት የአየር ኃይል ደኅንነት ኃላፊን ለማስገደል ለሌሎች አባላት ተልዕኮ በመስጠት በመንቀሳቀስ ላይ እያለ በቁጥጥር ሥር መዋሉን ዓቃቤ ሕግ ያቀረበው ክስ ያብራራል፡፡ በአጠቃላይ ተከሳሾቹ የሽብር ተግባር ለመፈጸም በማቀድ፣ በመዘጋጀት፣ በአመራርነት መሳተፍና የማሴር ወንጀል የፀረ ሽብርተኝነት አዋጁ አንቀጽ 7(2)ን ጨምሮ በመተላለፍ ክስ ተመሥርቶባቸዋል፡፡ ethiopianreporter

Trending

By continuing to use the site, you agree to the use of cookies. more information

The cookie settings on this website are set to "allow cookies" to give you the best browsing experience possible. If you continue to use this website without changing your cookie settings or you click "Accept" below then you are consenting to this.

Close