የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽነር ለደቡብ አፍሪካ ፕሬዘዳንትነት በእጩነት ይቀርባሉ ተባለ

0
468
የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽነር ለደቡብ አፍሪካ ፕሬዘዳንትነት በእጩነት ይቀርባሉ ተባለ
ደቡብ አፍሪካዊቷ የፖለቲካ ሰው ከህብረቱ ከተሰናበቱ በኋላ በሀገራቸው ለፕሬዘዳንትነት እጩ ሆነው ይቀርባሉ ከወዲሁ እየተባለ ይገኛል፡፡

የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ኮሚሽነር ድላሚኒ ዙማ ዘንድሮ የህብረቱ አመራርነታቸውን ያስረክባሉ፡፡ ደቡብ አፍሪካዊቷ የፖለቲካ ሰው ከህብረቱ ከተሰናበቱ በኋላ በሀገራቸው ለፕሬዘዳንትነት እጩ ሆነው ይቀርባሉ ከወዲሁ እየተባለ ይገኛል፡፡ ትናንት በወጡ መረጃዎች ዙማ በኤኤንሲ የሴቶች ሊግ በኩል ለፕሬዘዳንትነት እጩ ሆነው እንዲቀርቡ ከፍተኛ ድጋፍ አግኝተዋል ብለዋል፡፡

ዙማ በእጪነት ቢቀርቡ ከሀገሪቱ ምክትል ፕሬዘዳንት ከሲሪል ራማፎሳ ጠንካራ ፉክክር ሊገጥማቸው ይችላል ተብሏል፡፡ ሆኖም በፓርቲው ጠንካራ ድጋፍ እያገኙ ያሉት ዙማ እስከአሁን ባሳለፉት የስራ ህይወት ያካበቱት የአመራርነት ልምድና ችሎታ ለፕሬዘዳንታዊ ስልጣን እንዲበቁ ያስችላቸዋል ነው የተባለው፡፡

በቅርቡ የተባበሩት መንግስታት ዋና ጸሀፊነትን የለቀቁት ደቡብ ኮሪያዊው ባን ኪ ሙን ለሀገራቸው በመሪነት ለመቅረብ ከጫፍ መድረሳቸው ሲዘገብ ነው የቆየው፡፡ አሁን ደግሞ ዙማ ከአህጉራዊ ድርጅት መሪነት ወደ ሀገር መሪነት ሊመጡ ይችላል ተብሎ ተገምቷል፡፡

ሰሞኑን 105ተኛ የምስረታ አመቱን ያከበረው ገዢው የደቡብ አፍሪካ ፖለቲካ ፓርቲ አፍሪካን ናሽናል ኮንግረስ ወይም ኤኤንሲ በአህጉሪቱ ጭምር እድሜ ጠገብ ከሆኑ የፖለቲካ ማህበራት አንዱ ነው፡፡

ፓርቲው እንደ ኔልሰን ማንዴላና ታቦ ምቤኪን የመሳሰሉ በአፓርታይድ አገዛዝ ትግል የሚታወቁ ጠንካራ ፖለቲከኞችን ያፈራ ድርጅትም ነው፡፡ የአሁኑ የሀገሪቱ ፕሬዘዳንት ጃኮብ ዙማም የዚሁ ፓርቲ ነባር አባል ናቸው፡፡

አሁን ላይ በጃኮብ ዙማ መሪነት ስር የሚገኘው ፓርቲው በቅርብ አመታት በሙስናና በስልጣን ብልግና እንዲሁም በደካማ የኢኮኖሚ አፈጻጸም ሲተች ቆይቷል፡፡ ድላሚኒ ዙማ ታዲያ ወደስልጣን መጥተው ይህን ሁሉ ያቃኑት ይሆን የሚለው ጥያቄ ወደፊት የሚመለስ ነው የሚሆነው፡፡africa

READ  ግብጾች የኢትዮጵያ ባለስልጣናት ሀገራቸውን መወንጀል እንዲያቆሙ ጠየቁ

NO COMMENTS