“የኛ” በወጣት ሴቶች ዙሪያ በኢትዮጵያ የአስተሳሰብ ለውጥ ለማምጣት የሚሠራውን ስራ አጠናክሮ ይቀጥላል

0
1238
“የኛ” በወጣት ሴቶች ዙሪያ
“የኛ” በወጣት ሴቶች ዙሪያ በኢትዮጵያ የአስተሳሰብ ለውጥ ለማምጣት የሚሠራውን ስራ አጠናክሮ ይቀጥላል

Press release:

“የኛ” በወጣት ሴቶች ዙሪያ የአስተሳሰብ ለውጥ ማምጣትን ግቡ ያደረገ በኢትዮጵያ ፈር ቀዲጅ የሆነ የሚዲያ ስራ ነው፡፡ ስራችን መሠረቱን በኢትዮጵያ ባህል ላይ ያደረገ፤ በኢትዮጵያውያን ለኢትዮጵያውያን የሚሠራ ነው፡፡

“የኛ” በወጣት ሴቶች ዙሪያ ያሉ አመለካከቶች፣ እምነቶችና ምግባሮች ላይ ሃሳቦች እንዲንሸራሸሩና በበጎ መልኩም እንዲዳብሩ፤ ብሎም ወጣት ሴቶች ለማህበረሰባቸው አወንታዊ አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ ማስቻል ነው፡፡

“የኛ” ፤ በአማራ ክልልና በአዲስ አበባ ብቻ ከስምንት ሚሊዮን በላይ አድማጮች ያሉት ሳምንታዊ የሬድዮ ድራማ ፣ ቶክ ሾው እና የሙዚቃ ቡድን ነው፡፡ በተለያዩ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች የተላለፈው የ“የኛ” ፊልም በአገር አቀፍ ደረጃ ብዙ ሚሊዮን ተመልካቾች አግኝቷል፡፡ በተጨማሪም በሬድዮ የምናንሸራሽራቸው ሃሳቦች በማህበረሰቡ ዘንድ እንዲሰርጹ በትምህርት ቤቶች የየኛ ክበቦች ተመስርተዋል፡፡

በ“የኛ” ድራማ የሚነሱት ታሪኮች በአገራችን በወጣት ሴቶች ዙሪያ ያሉ እውነታዎችን እንዲያንፀባርቁ በማሰብ ይዘታቸው የሚዳብረው ወጣት ሴቶችን፣ ቤተሰቦቻቸውንና ማህበረሰቡን ባሣተፈ መንገድ ነው፡፡

“ባለፈው ዓርብ ይፋ እንደሆነው፣ ከአጋሮቻችን አንዱ ከሆነው የእንግሊዝ ዓለም ዓቀፍ የልማት ድርጅት ወይም DFI D ጋር የነበረን ትብብር ተቋርጧል፡፡ DFI D ስራውን ስንጀምር ከነበሩት ዋና አጋሮቻችን መካከል እንዱ ነበር፡፡

ለአራት ዓመታት አብረን በሰራንበት ጊዜም ከምርምር፣ ክትትልና ድጋፍ ስራቸው ብዙ ተጠቃሚ መሆን ችለናል፡፡ አሁን ግን ስራችን አዋጭና ዘላቂ በሆነ መንገድ በራሳችን ሁለት እግር ቆመን ወደምናስኬድበት ምዕራፍ ተሸጋግረናል” ሲሉ የ“የኛ” ማኔጂንግ ዳይሬክተር ወ/ሮ ሰሎሜ ታደሰ ተናግረዋል፡፡

ይህ የDFI D ውሳኔ “የኛ” በሦስት ዓመታት ያሳለፈውን ስኬታማ ጉዞና ያስመዘገበውን ውጤት በማናቸውም መልኩ የሚያመላክት አይደለም፡፡ ይልቁንም ባለፉት ተከታታይ ሦስት ዓመታት በDFI D ዓመታዊ ሪፖርቶች “የኛ” የA ደረጃን ማግኘት ችሏል፡፡

READ  East Africans behind Dr. Adhanom WHO’s Campaign

በዚህም ምክንያት የኢትዮጵያውያን ወጣት ሴቶች ህይወትን በማጎልበት ደረጃ ውጤታማ መሆን ችለናል፡፡ የ“የኛ” መደበኛ አድማጭ ከሆኑት ውስጥ 76 በመቶ የሚሆኑ ወጣት ሴቶች “የኛ” ትምህርታቸውን እንዲቀጥሉ እንዳነሳሳቸው ይገልፃሉ፤ 95 በመቶ የሚሆኑ ወጣት ወንድ አድማጮች ደግሞ ሴቶች ያለፍቃዳቸው ለትዳር ቢዳረጉ የዳር ተመልካች እንደማይሆኑ ይናገራሉ፡፡

“የኛ” ለወጣት ሴቶች የሚያደርገውን ድጋፍና ለአገራችን ማህበራዊ ማንሰራራት የሚሰጠውን አስተዋፅኦ ስለምናውቅ ኢትዮጵያዊ መሠረቱን አስጠብቆ ፈር ቀዳጅ በሆነ መንገድ የሚሰራውን ስራ ይቀጥላል፡፡ በቀጣይም የሚሠሩ በርካታ ስራዎች ያለምንም መስተጓጎል ይቀጥላሉ፡፡ ለዚህም ተመሳሳይ አመለካከት ካላቸው የአገር ውስጥና ዓለም ዓቀፍ አጋሮች ጋር አብረን እንሠራለን፡፡

በቅርቡም “የኛ”ን አገር ዓቀፍ ሽፋን ወዳለው ፕሮግራም በማሸጋገር፣ በመላው አገሪቱ የሚገኙ ወጣት ሴቶችን፣ የዕድሜ አቻዎቻቸውንና ቤተሰቦቻቸውን እንደርሳለን፡፡

“ሁሌም እንደማምነው “የኛ” ኢትዮጵያዊ ክስተት ነው፡፡ አሁንም ቢሆን በስራችን እየጎለበትን በሄድን ቁጥር የኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት ድጋፍ እንደማይለየን ሙሉ እምነት አለኝ” ሲሉ ወ/ሮ ሰሎሜ አክለዋል፡፡  Press Release

NO COMMENTS