በመናኸሪያዎች ለተጓዦች የጉዞ መረጃ ማቅረብ የሚያስችል አሰራር ሊዘረጋ ነው

0
80

በሁሉም የሃገሪቱ መናኸሪያዎች ለተጓዦች ሙሉ የጉዞ መረጃ ማቅረብ የሚያስችል የአሰራር ሥርዓት ሊዘረጋ ነው።

የፌደራል ትራንስፖርት ባለሥልጣን ለኢዜአ እንዳስታወቀው፥ በቴክኖሎጂ የሚታገዘው ይህ አሰራር የመንገደኞችን ጊዜና ወጪ የሚቆጥብ ነው።

የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ ካሳሁን ኃይለማርያም እንዳሉት፥ ነባሩ አሰራር አድካሚና ለወጪ የሚዳርግ ከመሆኑ ባሻገር ተጓዦችን ለአዳጋ የሚያጋልጥበት ሁኔታ ተስተውሏል።

አዲሱ አሰራር ተገልጋዮች የትኬት መቁረጫ ቦታ፣ የተሽከርካሪ ሰሌዳ ቁጥርና መቆሚያ እንዲሁም የመነሻና መድረሻ ሰዓታቸውን በቀላሉ ለይተው ማወቅ እንደሚያስችል ተናግረዋል።

መረጃው ተሽከርካሪዎች ከመናኸሪያ ከመውጣታቸው በፊት የቆሙበትን ቦታ በግልጽ የሚያመላክት እንደሆነም አስረድተዋል።

በጉዳዩ ዙሪያ ከክልል የትራንስፖርት ባለሥልጣን መስሪያ ቤቶችና ከባለድርሻ አካላት ጋር ምክክር የተደረገ ሲሆን፥ በዚህ ዓመትም ተግባራዊ ይደረጋል ብለዋል።

አሰራሩ መንገደኞች የሚፈልጉት ተሽከርካሪ ያለበትን ቦታ መናኸሪያ ከመግባታቸው በፊት እንዲያወቁት የሚያደርግ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ የታገዘ ይሆናልም ነው ያሉት።

ለአሰራሩ እንዲያመችም ነባር መናኸሪያዎችን የማደስና አዳዲስ የሚገነቡትን ደግም ለቴክኖሎጂው ምቹ እንዲሆኑ የማድረግ ሥራ እንደሚሰራም ገልጸዋል።

ለተሽከርካሪዎች መስፈርት በማውጣትና ለባለሃብቶች በመስፈርቱ መሰረት ከሚዘረጋው አገልግሎት ጋር የተጣጣመ ቴክኖሎጂ የተገጠመላቸው ተሽከርካሪዎች እንዲያቀርቡ ይደረጋልም ነው የተባለው።FBC

READ  አሸተን ማርያም-የነአኩቶ ለአብ ድንቅ ስራ

NO COMMENTS