በመልሶ ማልማት የተፈናቀሉ ነጋዴዎች ቃል የተገባልንን መሬት ማግኘት አልቻልንም አሉ

0
1139
በመልሶ ማልማት የተፈናቀሉ ነጋዴዎች
በመልሶ ማልማት የተፈናቀሉ ነጋዴዎች ቃል የተገባልንን መሬት ማግኘት አልቻልንም አሉ

ከመሀል አዲስ አበባ በመልሶ ማልማት ፕሮግራም የተፈናቀሉ ነጋዴዎች ግንባታ የሚያካሂዱበት ምትክ ቦታ እስካሁን ድረስ ስላልተሰጣቸው ለከፍተኛ ችግር መዳረጋቸውን፣ ለግንባታ ያዋጡት ገንዘብም ለዓመታት ያለሥራ መቀመጡን ገለጹ፡፡

ከአሥር በላይ በሚሆኑ አክሲዮን ማኅበራት ተደራጅተው የሚገኙ ከአንድ ሺሕ በላይ ነጋዴዎች፣ ጉዳያቸውን ለማስፈጸም ላለፉት ሦስት ዓመታት ቢመላለሱም ሰሚ ባለማግኘታቸው ምሬታቸውን እየገለጹ ነው፡፡

አቤቱታ እያቀረቡ የሚገኙት አክሲዮን ማኅበራት በልደታ ክፍለ ከተማ ሦስት፣ በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ስምንት፣ በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ሦስት ናቸው፡፡

በልደታ ክፍለ ከተማ ተክለሃይማኖት (ሰንጋ ተራ ቁጥር ሦስት) 33 ሔክታር መሬት ላይ ይኖሩ የነበሩ ሰዎች በልማት ምክንያት ተነስተዋል፡፡ ከዚህ ቦታ ላይ የተነሱ 122 ነጋዴዎች ‹‹ጥቁር አንበሳ አክሲዮን ማኅበር›› በሚባል ስያሜ የንግድ ድርጅት አቋቁመዋል፡፡
ነጋዴዎቹ የተነሱት በ2006 ዓ.ም ቢሆንም፣ የከተማ ቦታ በሊዝ ስለመያዝ የወጣው አዋጅ ቁጥር 721/2004 የሚፈቀድላቸውን ቦታ ማግኘት እንዳልቻሉ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

የጥቁር አንባሳ አክሲዮን ማኅበር ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ተስፋዬ አበበ ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ ይነግዱበት የነበረውን ቦታ ከለቀቁ ሦስት ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ 122 የሚሆኑት የአክሲዮን ማኅበሩ አባላት በሚሰጣቸው ቦታ ላይ ግንባታ ለማካሄድ 24 ሚሊዮን ብር በማዋጣት በባንክ አስቀምጠው ቢጠባበቁም፣ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አገልግሎት ማግኘት አልቻሉም፡፡

በሊዝ አዋጁ ከመልሶ ማልማት ቦታዎች የሚነሱ ነጋዴዎች በተለይም የቀበሌ ወይም የመንግሥት የንግድ ቤት ተከራዮች፣ በአማካይ በነፍስ ወከፍ 25 ካሬ ሜትር እንዲሰጣቸው ተፈቅዷል፡፡ ነገር ግን ይኼ ድንጋጌ ተፈጻሚ መሆን ባለመቻሉ ቅሬታ እየተፈጠረ ይገኛል፡፡

ለችግር መዳረጋቸውን ከሚገልጹ ሌሎች አክሲዮን ማኅበራት መካከል ‹‹ተደንጓ የመልሶ ማልማት አክሲዮን ማኅበር›› ይገኝበታል፡፡ ይህ ሥፍራ የሚገኘው ከዋቢ ሸበሌ ሆቴል ጀርባ በሚገኘው የመልሶ ማልማት ፕሮግራም ቦታ ሲሆን በጠቅላላው 10.6 ሔክታር ይሸፍናል፡፡ ከዚህ ቦታ ላይ የተፈናቀሉ 124 ነጋዴዎች ላቋቋሙት አክሲዮን ማኅበር 19 ሚሊዮን ብር አዋጥተው፣ ቦታውን ላለፉት ሦስት ዓመታት መጠበቃቸውን ይናገራሉ፡፡

READ  እስራኤል ለመጀመሪያ ጊዜ ቤተእስራኤላዊያንን በዳኝነት ሾመች

ነገር ግን ቦታውን ማግኘት ባለመቻላቸው ለተለያዩ ችግሮች እንደተዳረጉ፣ አንዳንድ የአክሲዮን ማኅበሩ አባላት ከንግድ ሥራ ውጪ መሆናቸውም እየተገለጸ ነው፡፡

የተደንጓ የመልሶ ማልማት አክሲዮን ማኅበር ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ዓብይ ገብረ ዮሐንስ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ቦታውን በወቅቱ ተረክበው ግንባታ ማካሄድ ባለመቻላቸው በርካታ የአክሲዮን አባላት ለከፍተኛ ችግር እየተዳረጉ ነው፡፡

ከአዲስ አበባ መሬት ልማትና ከተማ ማደስ ኤጀንሲ የተገኘ መረጃ እንደሚጠቁመው፣ በአካባቢው ሲካሄድ የቆየው የአካባቢ ልማት ፕላን (LDP) በወቅቱ ተጠናቆ፣ ሽንሻኖ በማካሄድ ወደ ልማት ማስገባት አልተቻለም፡፡

‹‹በአሁኑ ወቅት ግን የአካባቢ ልማት ፕላን የተጠናቀቀ በመሆኑ በቅርቡ ለአክሲዮን ማኅበራቱ ቦታ ማስረከብ ይጀምራል›› ሲሉ ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ የኤጀንሲው ባለሙያ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ ethiopianreporter

NO COMMENTS