የሰው ልጅ ሰውን ያውቀው ዘንድ አምላክ ሰው ሆነ ?

0
1100
መልካም የገና በዓል
እንኳን ለጌታችና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የልደት መታሰቢያ በዓል አደረሳችሁ!!!

እንኳን ለጌታችና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የልደት መታሰቢያ በዓል አደረሳችሁ!!!
መልካም የገና በዓልን እመኝላችኋለሁ።የሰው ልጅ ሰውን ያውቀው ዘንድ አምላክ ሰው ሆነ ?
(መላኩ አላምረው በድሬቲዩብ)

ውይይይይይይ የሰው ልጅ…..
የሰው ነገር አያንገሸግሽም? ምንም ምን ብታደርጉለት… ትንሽ ስህተት ሲገኝባችሁ ሁሉንም በዜሮ አባዝቶና
አጥንት የሚሰብር ቃል ተናግሮ ልብ የሚያደማ ሀዘንን ይተክልባችኋል። ክፉ ላለመናገርና እርሱን ላለማስልዘን
በመጠንቀቅ ዝም ስትሉት እንደ ጅል ይቆጥራችኋል። ብቻ ምንም መልካም ያላችሁትን ሁሉ ብታደርጉለት ለወቀሳ
ምክንያት አያጣላችሁም። ባደረጋችሁለት ነገር በራሱ ይከሳችኋል። ነጩን አጥቁሮ ብርሃኑን አጨልሞ ይወቅሳችኋል።
በእውነት የሰውን ጸባይ ችሎ እንደመኖር ያለ ትልቅ አቅም ይኖራልን?
.
ሰውን ከሰው በቀር ማን አስቀየመው? የትኛው ፍጥረት ልቡን በሀዘን ሰበረው? ተክሎ ያሳደጋቸው እጽዋት? ወይስ
የሚጠብቃቸው እንስሳት ክፉ አደረጉበት? የዱር አራዊትስ ሳይሄድባቸው መጥተው ረበሹት? ንቦች ናቸው ቀፏቸውን
ነካክቶ ማራቸውን ሳይቆርጥ የነደፉት? እባብስ ቢሆን ሰው ሳይደርስበት በመርዝ ይወጋዋልን? በፍጹም። እጽዋትን
ብናሳድጋቸው ሕይወታችንን ያለመልሙልናል። እንስሳትም በተንከባከብናቸው መጠን ያፈቅሩናል፤ ለቤታችን ጌጥ ለኑሯችን
ድጋፍ ይሆናሉ። ሰው ግን እንደዚህ አይደለም። መልካም ነገር ላይ ሳይሆን ክፉው ላይ ይወዳል። የተረገለትን
ሳይሆን የጎደለበትን ይቆጥራል።
.
ለነገሩ ድከም ቢለኝ እንጅ ሊያድነው የተወለደን ጌታ ለመስቀል የማይመለስ÷ ዐይነ ስውራንን ማብራቱን፣ ሽባ
መተርተሩን፣ ጎባጣ ማቅናቱን… ሳይሆን ሰንበትን መሻሩን ተመልክቶ በመክሰስ ሞት የፈረደበት ሰው…. ለእኛ
ከምንም ለማይቆጠር በጎ ሀሳባችን ክፉ ቢመልስ አያስደንቅም።

“የአምላክ ትዕግስቱ ~ በምን ያስታውቃል?”
በሰው ልጆች ዓለም ~ ብርሃንን ይለቃል።
.
እንደ ሕጉ ቢሆን ~ እንደ ሥርዓቱ
ጨለማ ነበረ ~ ለሰው የግብር ቤቱ።

.
“አምላክ ለምን ሰው ሆነ?” ለሚለው ጥያቄ አንዱ መልስ ይህ ይመስለኛል። “ከሰው ልጆች መካከል መልካምና
ያለነቀፋ የሚገኝ ስለጠፋ ሰው መሆን ምን ማለት እንደሆነ ለማሳየት” የሚለው። እርሱ ሰው ባይሆን ኖሮ የአዳም
ዘር ሁሉ አርአያ የሚያደርገው፣ የሰውን በደል የማይቆጥር፣ ለሚገድሉት የሚጸልይ… ማን ይኖር ነበር? ፍቅርን
በተግባር መስዋእትነት የሚያሳይ፣ የሚጠሉትን የሚያፈቅር፣ ለተራቡት ሲያበላ የማይሰስት-የማያልቅበትም፣ ለህሙማን
ፈውስን ሲሰጥ ዋጋ የማይከፈለው፣ ከሰው ምንም በጎ ነገርን ሳይጠብቅ መልካም ነገሮችን ሁሉ ያለገደብ
የሚያደርግለት… ማን ይኖር ነበር? በተግባር ማድረጉ ይቅርና ይህንን የፍቅር ሕይወት ያለ አድሎና ያለ ብድራት
የሚሰብክስ ማን ነበር? ማንም።

“በብዙ ምክንያት ሰው ቢያሳምመኝም
ከሰው የተሻለም መድኃኒት የለኝም።”

.
አምላክ ሰው ሆኖ መድኃኒት ባይሆነን ኖሮ፣ ሰው ለሰው መድኒት እንደሚሆን ባያሳይና ጥቂት መጽናኛ ደጋግ ሰዎች
በምድር ባይኖሩ ኖሮ… ዓለምን አስባችኋታል?
አምላክ ሆይ! እንኳንም ሰው ሆነህ ተወለድህ!!!
.
እንኳን ለጌታችና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የልደት መታሰቢያ በዓል አደረሳችሁ!!!
መልካም የገና በዓል! DIRETUBE NEWS

READ  የጥምቀትን መገለጫ/መለያ የረሱ የጥምቀት ማስታወቂያዎች ! (መላኩ አላምረው @DireTube)

NO COMMENTS