ወደ ላልይበላ-የሀገሬ እናቶች ይሄኔ መንገድ ላይ ናቸው

0
1278
ወደ ላልይበላ-የሀገሬ እናቶች ይሄኔ መንገድ ላይ ናቸው
ተጓዡ ጋዜጠኛ ሄኖክ ስዩም የኢትዮጵያ እናቶች መንገድ ላይ ናቸው ይለናል፡፡ ላሊበላን ለመሳለም ከቀናት በፊት ጉዞ ስለጀመሩ ምዕመናን እና ስለ ደብረ ሮሐ እንዲህ ይለናል፡፡

ወደ ላልይበላ-የሀገሬ እናቶች ይሄኔ መንገድ ላይ ናቸው፡፡

(ተጓዡ ጋዜጠኛ ሄኖክ ስዩም የኢትዮጵያ እናቶች መንገድ ላይ ናቸው ይለናል፡፡ ላሊበላን ለመሳለም ከቀናት በፊት ጉዞ ስለጀመሩ ምዕመናን እና ስለ ደብረ ሮሐ እንዲህ ይለናል፡፡)
(ሔኖክ ስዮም በድሬትዩብ)

የኢትዮጵያ እናቶች መንገድ ላይ ናቸው፡፡ ከተሜዎች እየ አውቶቢሳቸው ሆነው መንገዱን አቅርበው ከየአሉበት የመኪናቸው ቴፕ እየዘመረላቸው ወደ ደብረ ሮሐ የሚያቀኑትን ያክል ከኢትዮጵያ ተራሮች አናት የተነሱት ምዕመናንም ቀናትን ተጉዘዋል፡፡ ደብረ ሮሐን የረገጡ ዐለት ጮኾ ከሚናገርባት የቅዱሱ ንጉሥ መዲና ደርሰዋል፡፡

ገና መንገድ ላይ የሆኑ አሉ፡፡ ከላስታ ሰንሰለታማ ተራሮች ማዶ የተነሱ፣ በሽሎን ከቀናት በፊት ያቋረጡ፣ የራያን ሜዳና ኮረብታ የሰነጠቁ፣ የአምባሰልን ዝንጀሮ የማይወጣው ዳገት ያሸነፉ፣ በባዶ እግራቸው፤ ንጉሥም ቅዱስም ወደ ሆነው ታላቅ አባት ደጃፍ እየተጓዙ ነው፡፡
ላልይበላ እንዲህ እንደ ልደት ደምቃ አታውቅም፡፡ ከአሸተን እስከ ብልብላ፣ ከገነተ ማርያም እስከ ይምረሃነ ልደት ቁልቁል የሚመለከቷትን ደብረ ሮሐ የሚያደምቁበት ነው፡፡

ዓለም ዛሬ ዓይኑ ወደ ቅድስቲቷ መዲና ነው፡፡ ዳግማዊት ኢየሩሳሌም ወደ ተባለላት፤ ቤተ ጎለጎታ ወደሚገኝባት ከዩርዳኖስ ወንዝ ማዶ ድንቅ ምድር ግሩም ጥበብ ሽቅብ ከተፋበት፡፡


የእናቶች ዝማሬ መሰማት ጀምሯል፡፡
“ዓይኔ ዓለም አየ እግሬ ደርሶ
ዓይኔ ዓለም አየ እግሬ ደርሶ
የድንጋይ ወጋግራ የድንጋይ ምሰሶ………”

አሁን ይሄን ቅኔ የኔ ሀገር እናቶች ካልሆኑ ማን ችሎ ይቃኘዋል፡፡ ድንጋይን ከተማ ላደረጉ ቅዱሳን ነገሥታት በልካቸው የተፈጠሩ ድንቅ ምዕመናን እናቶች ዘመናቸውን የክርስቶስን መወለድ እንደ ሰብዓ ሰገል ጓዝ ሸክፈው ለቀናት ተጉዘው ቤተልሔም እንደ ገቡት ወደ ላልይበላ የሚጓዙ……
ዛሬ መድሃኒዓለም ነው፡፡

READ  በወር አንድ ቀን ከከተማቸው ህዝብ ጋር ጎዳና ላይ ወጥተው፤ ጽዳት የሚያጸዱት የጎንደር ከንቲባ

ቤተ መድሃኒዓለም ከድንቅ አስራ አንድ ውቅር ቤተ ክርስቲያኖች አንዱና ግዙፉ ነው፡፡ ላልይበላ ሲባል ቤተ ጊዮርጊስ በማይተነተን ጥበቡ የሚገለጸውን ያክል ቤተ መድሃኒዓለም ደግሞ በውቅር ጥበቦቹ የወል መገለጫነት ስሙ ይነሳል፡፡

የላልይበላ ቀሳውስት የታጠበ ባለ ቀይ ጥለት ጥንድ ድርብ ለክት ቀን ከተቀመጠበት ወጥቷል፡፡ ይህቺን ቀን በዚህ ስፍራ መሆን መታደል ነው ብለው ያመኑ ባህር አቋርጠው መጥተው ላስታ ናቸው፡፡ እነሱ በአየር በመኪና መጥተው በእግር ኳትነው የደረሱትን የሀገሬን እናቶች ያክል
“አልጋ በአልጋ ነው መንገዱ

ቅዱስ ላልይበላ ሲሄዱ” እያሉ በደስታ አይዘምሩም፡፡ እዚህ ሁሉንም ደስታ መንፈሳዊ ስሜት ያሸንፈዋል፡፡ ነገ አማኑኤል ነው፡፡ ከነገ ወዲያ ልደት…… DIRETUBE NEWS

NO COMMENTS