በተጠናቀቀው 2016 በኢራቅ ከ6 ሺህ በላይ ሰላማዊ ዜጎች መሞታቸውን የመንግስታቱ ድርጅት አስታወቀ

0
91
በመንግስታቱ ድርጅት ለኢራቅ ድጋፍ ሰጭ ቡድን፥ በጥቂቱ 6 ሺህ 878 ንጹሃን ዜጎች መገደላቸውን ይፋ አድርጓል

በመንግስታቱ ድርጅት ለኢራቅ ድጋፍ ሰጭ ቡድን፥ በጥቂቱ 6 ሺህ 878 ንጹሃን ዜጎች መገደላቸውን ይፋ አድርጓል።

ከሞቱት በተጨማሪም በትንሹ 12 ሺህ 388 ሰዎች ላይ የአካል ጉዳት መድረሱንም ነው ቡድኑ የሃገሪቱን ሰብዓዊ ቀውስ በዳሰሰበት ሪፖርቱ የገለጸው።

እንደ ቡድኑ ገለጻ፥ በሃገሪቱ የደረሰው የጉዳት መጠን ዝርዝር አለመታወቁን ተከትሎ የሟቾቹ ቁጥር ከዚህ በእጅጉ ሊጨምር ይችላል።

ቡድኑ በሪፖርቱ በምዕራባዊቷ የአንባር አውራጃ፥ በፈረንጆቹ ግንቦት፣ ሃምሌ፣ ነሃሴ እና በተጠናቀቀው የታህሳስ ወር የደረሱ ጉዳቶችን አላካተተም።

ባለፈው ታህሳስ ወር ብቻ ደግሞ በኢራቅ 386 ንጹሃን ዜጎች ሲሞቱ፥ 1 ሺህ 66 ዜጎች ደግሞ ቆስለዋል ነው የተባለው።

ኒኔቫህ አውራጃ ደግሞ አይ ኤስን ከሃገሪቱ ጠራርጎ ለማስወጣት በሚደረገው ዘመቻ እጅጉን የተጎዳች አካባቢ ሆናለች።

በዚህ አካባቢ ባለፈው ታህሳ ወር ብቻ 208 ሰዎች ሲገደሉ 511 ደግሞ ቆስለዋል።

ዋና ከተማዋ ባግዳድ ደግሞ 109 ሞት እና 523 ጉዳት በማስመዝገብ፥ የታህሳስ ወር ሁለተኛውን ከፍተኛ ጉዳት ያስመዘገበች ከተማ ሆናለች።

ከፈረንጆቹ 2008 ጀምሮ ደግሞ ኢራቅ ወደ 54 ሺህ የሚጠጉ ንፁሃን ዜጎቿን በጦርነት እና ጥቃት ሳቢያ ተነጥቃለች።

ከቀድሞ መሪዋ ሳዳም ሁሴን ህልፈት በኋላ አገሪቱ የጦር አውድማ መሆኑ ለደረሰው ጉዳት ዋናውን ድርሻ ይወስዳል።

በተለይም ጽንፈኛው ታጣቂ ቡድን አይ ኤስ የሚፈጽማቸው አጥፍቶ ጠፊ ጥቃቶች እና ከመንግስት ወታደሮች ጋር በሚያደርገው ውጊያ በርካቶች ለህልፈት ተዳርገዋል።

በአሜሪካ የሚደገፉት የመንግስት ወታደሮችም ቡድኑን ከኢራቅ ለማስወጣት ጠንካራ ያሉትን ዘመቻ እያደረጉ ነው።

ጠንካራ ይዞታው ከሆነችው የሞሱል ከተማ ለማስለቀቅ የሚያደርገው ጥረት ግን ከቡድኑ ጠንካራ መከላከል ገጥሞታል።

READ  በእሥራኤል ትውልደ ኢትዮጵያውያን ደም እንዳይለግሱ ተጥሎባቸው የነበረ እገዳ ተነሳላቸው

 

NO COMMENTS