ጨበራ ጩርጩራ ብሔራዊ ፓርክ-የሐይቆቹ ምድር

0
753
ጨበራ ጩርጩራ
(ተጓዡ ጋዜጠኛ ሄኖክ ስዩም በጨበራ ጩርጩራ ብሔራዊ ፓርክ ደኖች ውስጥ ከትቶናል፡፡ በደቡብ ክልል የሚገኘውን የጨበራ ጩርጩራ ብሔራዊ ፓርክ የተፈጥሮ ሀብት እያስጎበኘን ነው፡፡ ዛሬ ደግሞ የሐይቆቹ ምድር ሲል ወደ ፓርኩ ሐይቆች ወስዶ እንዲህ ያስጎበኘናል፡፡)

ጨበራ ጩርጩራ ብሔራዊ ፓርክ-የሐይቆቹ ምድር፤

(ተጓዡ ጋዜጠኛ ሄኖክ ስዩም በጨበራ ጩርጩራ ብሔራዊ ፓርክ ደኖች ውስጥ ከትቶናል፡፡ በደቡብ ክልል የሚገኘውን የጨበራ ጩርጩራ ብሔራዊ ፓርክ የተፈጥሮ ሀብት እያስጎበኘን ነው፡፡ ዛሬ ደግሞ የሐይቆቹ ምድር ሲል ወደ ፓርኩ ሐይቆች ወስዶ እንዲህ ያስጎበኘናል፡፡) (ሔኖክ ስዮም በድሬትዩብ)

ሕይወት ያለው እዚህ ነው፡፡ ጥምን ለቀናት የሚቆርጡ ንጹህ አፍላጋት የሚንቀዠቀዡበት፣ በድምጻቸው የሚያንበረክኩ የፏፏቴ ድምጾች ትዝታ ሆነው የሚቀሩበት፤ ጨበራ ጩርጩራ ብሔራዊ ፓርክ ነኝ፡፡ 1400 ካሬ ኪሎ ሜትር የሚሰፋው ይህ ፓርክ የሐይቅ ሀብታም ነው፡፡ ሾሺማ ወንዝን ይመስል ይህንን ድንቅ ፓርክ እየተሽከረከርነው ነው፡፡

ሾሺማ ጨበራ ጩርጩራን የሚርመሰመስ፣ የፓርኩ ህይወት ለመሆን የበቃ ዋናው ወንዝ ነው፡፡ ስለ ጨበራ ጩርጩራ ሳትሰሙ መቅረታችሁ፤ አልያም አለማወቃችሁ የራሳችሁ እንጂ የዚህ ታላቅ ሀብታችሁ ችግር አይደለም፡፡ ከ49 በላይ ከፓርኩ የሚፈሱ ወንዞች ኦሞ ገብተው መብራት የሚሆኑበት ድንቅ ምድር ነው፡፡ 16 ኪሎ ሜትር ያክል በእግር ተጉዘን የደረስንበት ቡሎ ሃይቅ የጨበራ ውበት ከሚባሉት አንዱ ነው፡፡ ትናንሽ ኮረብታዎችን እና ረዣዥም የሳር ደኖችን ጥሰን እዚህ ደርሰናል፡፡

ከአምስቱ የጨበራ ሐይቆች አንዱ ይሄ ነው፡፡ ቡሎ ይባላል፡፡ እነ ባሂ እነ ሺታ እነ ከረቤላ ብቻ ምን አለፋችሁ፤ ጨበራ ጩርጩራ የሐይቆች ምድር ነው፡፡ ከእነዚህ ሐይቆች በአንዱ የተገኘው የአሳ ዝርያ ብርቅዬ ነው በሚሉ ሊቃውንት እውቅና አግኝቶ ዝናው ወደ ዓለም ሊቃውንት ሄዷል፡፡ የአሳው ሳይንሳዊ ስምም ጋራ ጨበራ (Gara chebra) ለመባል በቅቷል፡፡

ቡሎ እጅግ አስደናቂ በሆነ ስፍራ ያረፈ የተፈጥሮ ሐይቅ ነው፡፡ አዳነ ጸጋዬ የብሔራዊ ፓርኩ ሃላፊ ነው፤ ጨበራ ጩርጩራን የአምስት ሐይቆች ሀብታም በመሆኑ ቢኮራበትም ቡሎ ሃይቅ ግን የመድረቅ ስጋት እንዳጠላበት እና መጠኑ እየቀነሰ እንደሆነ ነው የሚናገረው፡፡ ጉማሬዎቹ በጠለቁበት ሆነው ድምጽ ያሰማሉ፡፡

READ  Italy to Invest in Ethiopia, Says Italy Foreign Minister

ጉማሬን እንደልብ ለማየት የሚሻ ቡሎ እና ከረቤላ ምሽቱን ጎራ ይበል፤ አየሩ ቀዝቀዝ ሲል የሚወጡት ጉማሬዎች ቁጥር የላቸውም፡፡ እድሜ ጠብ ዛፎች እና ቅርንጫፈ ግዙፍ ሀገር በቀል እጽዋት ቡሎን አጅበውታል፡፡ ከቡሎ ወደ ባርቦ ነው የምንጓዘው፣ ቢደክመን እናርፋለን፡፡ 14 ኪሎ ሜትር ገደማ የእግር ጉዞ አለው፡፡

አስደናቂውን የተፈጥሮ ፏፏቴ ልንመለከተው ነው፡፡ መንገዱ አይሰለችም፡፡ ህዝብ የሚጠብቀው ፓርክ ለመሆኑ ለቀናት ጨበራ ጩርጩራ ስትከርሙ የቤት እንስሳ ሲናፍቃችሁ፤ ጎጆ ቤት ማየት ዘበት ሲሆን፣ ጠምዶ የሚያርስ ገበሬ ጭራሽ ለዓይን ሳይታይ የምትጎበኙት ፓርክ ነው፡፡ በእርግጥ ኮንታዎች በእርግጥም ዳውሮዎች ተፈትኖ ባለፈ የተፈጥሮ ጥበቃ ባህላቸው ሊደነቁ ይገባል፡፡

ባርቦ ደርሰናል፡፡ ድምጹ ነው የተቀበለን፤ ከሰማይ ተወርውሮ ምድር የሚያርፈው የውሃ ድምጽ መንገድ ለጠፋው እየመራ ባርቦ ያመጣል፡፡ እንዲህ ነው የመጣነው፤ ስንደርስ የጨበራ ጩርጩራ ሌላ ውበት ፍንትው አለ፡፡ ድምጹን ሰብሮ የሚያሸንፍ ውበት፤ ረዥሙ ፏፏቴ ስር ነን፡፡

ጨበራ ጩርጩራን አንድ ፓርክ ማለት፤ በአንድ ስም መጥራት፣ እንደ ቻሉት መግለጽ ከባድ መሆኑን አምኜአለሁ፡፡ ጨበራ ጩርጩራን ጎብኙት ይባላል እንጂ ይሄንን ጎበኘሁበት ብሎ መተረክ ልክ አይመጣም፡፡ የሚሸተት፣ የሚደመጥ፣ የሚታይ ብሔራዊ ፓርክ ውስጥ ነኝ፡፡ ባርቦ ፏፏቴ ዳርቻ፤ DIRETUBE NEWS

NO COMMENTS