ኢትዮጵያ የሳተላይት መንኮራኩር የማመንጠቅ ፕሮጀክት እየከወነች ነው

0
734
ኢትዮጵያ የሳተላይት መንኮራኩር

ኢትዮጵያ የራሷን የሳተላይት መንኮራኩር ወደ ጠፈር የማመንጠቅ ፕሮጀክት እየከወነች መሆኑን የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ገለጸ።

የሚኒስቴሩ የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ወንድወሰን አንዱዓለም ለኢዜአ አንደገለጹት ኢትዮጵያ በሚቀጥሉት ሶስት ዓመታት የራሷን ሳተላይት አምርታ ወደ ጠፈር ታመጥቃለች።

ለመጀመሪያ ጊዜም መለስተኛ የሳተላይት መንኮራኩር ማመንጠቅ የሚያስችል ፕሮቶታይፕ ወይም ምስለ ናሙና በመስራት ቅድመ ዝግጅት መደረጉን ጠቁመዋል።

ከልማት አጋር አገሮች በሚደረግ የዕውቀትና የቴክኖሎጂ ሽግግር ሳተላይቱን የመስራት አቅም እየተገነባ መሆኑንም ተናግረዋል።
መለስተኛ ሳተላይቱ በአገር ውስጥ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲዎችና በሌሎች ተቋማት ትብብር እንደሚመረት ጠቅሰው የማመንጠቂያ መንኮራኩር በአገር ውስጥ ለመስራት ጥረት መጀመሩንም ገልጸዋል።

“በአሁኑ ወቅት የሕዋ ሳይንስ ጉዳይ እንደ ቅንጦት የሚወሰድበት ዘመን አብቅቶለታል” ያሉት ዳይሬክተሩ መሰረታዊ የመገልገያ ቁሳቁሶች ከህዋ ሳይንስ ጋር የተያያዙ በመሆናቸው የዓለም አገራት ለዘርፉ ትኩረት መስጠታቸውን አክለዋል።

የአገር ደህንነት ማስጠበቅን ጨምሮ ተንቀሳቃሽ ስልክ፣ ቴሌቪዥን፣ የአየር ትንበያ መረጃና ሌሎች አገልግሎቶችን ለአብነት አንስተዋል።
እነዚህ አገልግሎቶች ቅንጦት ባለመሆናቸው የዚህ ሁሉ የመረጃ ምንጭ የሆነው የህዋ ሳይንስ ቴክኖሎጂ አስፈላጊነት ላይ ተመሳሳይ ግንዛቤ መኖሩን ነው ያብራሩት።

“ከዚህ አንጻር የህዋ ሳይንስ ከኢትዮጵያ ህልውና ጋር የተያያዘ ነው” የሚሉት አቶ ወንድወሰን ሚኒስቴሩ የህዋ ሳይንስ እንደ ማንኛውም ሳይንስ ለሕዝብ ይጠቅማል በሚል ትኩረት እንደሰጠው ተናግረዋል።

የህዋ ሳይንስ ምክር ቤትና ኢንስቲትዩት መቋቋሙንና ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝም የምክር ቤቱ ሰብሳቢ መሆናቸውን አክለዋል።
ምክር ቤቱና ኢንስቲትዩቱ በአጭር ጊዜ የስራ ኃላፊዎች ተመድበውላቸው ወደ ስራ መግባታቸውንም አብራርተዋል።

ኢትዮጵያ ለምድር ወገብ ባላት ቅርበትና በጠራ ሰማይዋ ምክንያት ለጠፈር ምርምር አጓጊ መሆኗን ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን የሚያወሱት ነው።

READ  በተጭበረበረ ሰነድ 1.2 ሚሊዮን ብር ወስደዋል የተባሉ ሁለት የባንክ ሰራተኞች ተቀጡ

በአሁኑ ወቅት በምድር ወገብ አካባቢ ሳተላይቶችን በማመንጠቅ ስፍራ የመሻማት አዝማሚያ እየተበራከተ መምጣቱን የጠቀሱት አቶ ወንድወሰንም ኢትዮጵያ በአጭር ጊዜ መለስተኛ መንኮራኩር ማመንጠቅ የሚያስችላት ተግባር ውስጥ መሆኗን ገልጸዋል።

ምንጭ፡-ኢዜአ

NO COMMENTS