ጨበራ ጩርጩራ ብሔራዊ ፓርክ-የኢትዮጵያ ታላቅ ሀብት

0
631
ጨበራ ጩርጩራ ብሔራዊ ፓርክ-የኢትዮጵያ ታላቅ ሀብት
የጨበራ ጩርጩራ ውበት ሙሉው አይጻፍም፡፡ ፊደል የሌላቸው፣ ቃላት የማይገልጹዋቸው ምትሃቶች በዝተውብኛል፡፡ ነጭ ውሃ ስር ነኝ፡፡

(ተጓዡ ጋዜጠኛ ሄኖክ ስዩም ደቡብ ክልል ጨበራ ጩርጩራ ብሔራዊ ፓርክ ይዞን ተጉዟል፡፡ የዝሆኖቹ ሰፈር ደርሶ ይህ የኢትዮጵያ ታላቅ ሀብት ነው ይለናል፡፡ ዛሬም እዚያው ውብ ደን ውስጥ ነን ሲል ጨበራ ጩርጩራ ብሔራዊ ፓርክን እንዲህ ያስጎበኘናል፡፡) (ሔኖክ ስዮም በድሬትዩብ)

ዛሬም እዚሁ ውብ ደን ውስጥ ነን፡፡ የማየውን ሳይሆን የምነግራችሁ ቀንሼ ነው፡፡ የጨበራ ጩርጩራ ውበት ሙሉው አይጻፍም፡፡ ፊደል የሌላቸው፣ ቃላት የማይገልጹዋቸው ምትሃቶች በዝተውብኛል፡፡

ነጭ ውሃ ስር ነኝ፡፡ ምንጭ እንደ ጩጫን የሚርመሰመስበት ፓርክ ነው፡፡ እዚህ ጥም የለም፡፡ ነጭ ውሃ በጨበራ ከሚገኙ ምንጮች አንዷ ናት፡፡ እድሏ ሆኖ ስሟ ገኖ እንጂ እንዲህ ያሉ ምንጮች እዚህ ቁጥርም ክብርም የላቸውም፡፡ እዚህም እዚያም ምንጭ ነው፡፡ ጣዕሙ እንደ ስፍራው የሚለያይ ምንጭ፤ እዚህ እንደ አምቦ አይነት የማዕድን ውሃ በየጥሻው አለ፡፡

እዚህ ቀዝቃዛ ሆኖ የሚንተከተክ ምንጭ እንደ ልብ ነው፡፡ ነጭ ውሃን የሚለያት ሰፈሯ ነው፡፡ የዝሆኖቹ መዋያ ከሆነው አካባቢ አቅራቢያ መገኘቷ፤ ይህቺን ምንጭ ያገነናት ከዝንባባዎቿ ጥላ ስር መንጭታ ነፍስ የሚያሳርፍ ቅዝቃዜን መታደሏ ነው፡፡ ወደ ኤርፓ ጉዞአችንን ቀጥለናል፡፡

በሳር ውስጥም መንገድ አለ የሚለውን ለመቀበል ሳሩ ሳይቃጠል ጨበራ ጩርጩራ መምጣት ነው፡፡ ሰው ከረዣዥሞቹ የሳር ተክሎች ስር እንደ ደብረ ሲና ዋሻ ተሸሽጎ የሚሄድበት የተለየ ምድር፡፡ እዚህ ቶሎ ቶሎ አቅጣጫ ቢጠፋ አይገርምም፤ ምስራቅና ሰሜኑን እንዳንለየው ያደረጉን የሳር ደኖች ዋጋ እያስከፈሉን ነው፡፡ ኤርፓ ደረስን፤ እንደ አሰብነውም ዝሆኖቹ እዚህ ናቸው፡፡

ግዙፍ ግንድ የጣለ ዝሆን ቁርስ ቢጤ ቀመስ ሲያደርግ አየን፡፡ ምድሩ ረግረግ ነው፡፡ ጭቃው መንገድ መሪ ካላገኘ ያስቀራል፡፡ ጉልበቱን የተማመነው ዝሆን ረግረጉን ረግጦ በደለደለው ጭቃ ወደ መሀል ተጠጋን፤ ብዙ ዝሆኖች ናቸው፡፡ የጨበራ ሳር ብርቱ መሆኑ የገባኝ ዝሆን መዋጥ ሲችል ነው፡፡ ይሄ የአፍሪካ ዝሆን ነው፡፡ አመል አለው፤ እያየን እንዳላየን ያልፈናል፡፡ ካልነኩት እንደማይነካ ቢነገረንም ሀሳቡን እንዳይቀይር ጥንቃቄ አልተለየንም፡፡ ግዙፉን ዛፉ ጠቅለል አድርጎ ያጋድመዋል፡፡ ጦጣዎቹ ዛፋቸው ላይ ሆነው ይንጫጫሉ፤ መሀላቸው መገኘታችንን የወደዱት አልመሰለኝም፡፡

READ  የሜቄዶንያ መስራች ወጣት ቢንያም ‹‹በሽታ ሃብት ነው›› ይለናል

ይህ ድንቅ ፓርክ 39 የሚደርሱ ትላልቅና መካከለኛ እንዲሁም 18 ትናንሽ እስከአሁን በተደረገ ጥናት 57 የሚሆኑ አጥቢ የዱር እንስሳት መኖሪያ መሆኑን የፓርኩ ሃላፊ አዳነ ጸጋዬ ገልጾልኛል፡፡ የዝሆኑን ብዛት ሳይ ዳውሮና ኮንታን አደነቅሁ፤ ሲፈልገው መንደር ገብቶ እያመሰ፤ ሲያሻው ሰው ሳይቀር እየተጋጨ፤ ታግሰውት ጨበራ ጩርጩራን እንዲህ የአፍሪካ ዝሆኖች መቦረቂያ አድርገውታል፡፡

አራት መቶ የሚጠጉ ዝሆኖች መኖሪያ የሆነው ፓርክ ያለ እረፍት የአእዋፍ ድምጽ የሚሰማበት 137 የሚደርሱ የአእዋፍ ዝርያዎች መኖሪያ ነው፡፡ ስድስት በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኙ አእዋፍም ይዟል፡፡ ይሄ ደን ዝም ብሎ ቁጥቋጦ አይደለም፡፡ 106 የሚደርሱ እጽዋት ይገኙበታል፡፡ ስድስቱ በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኙ ናቸው፡፡

ከዚያም ሲያልፍ ዘሩ ያልተቀላቀለ የዝንጅብል፣ የቡና፣ የኮረሪማ፣ የእንሰት፣ የእጣን፣ የጌሾ ዝርያዎች ባንክ ነው፡፡ ማዳበሪያ የማያውቁ፣ ከተፈጥሮ ያልተጣሉ ዝርያዎች መሸሸጊያ ነው፡፡ ጨበራ ጩርጩራ ሰፊ ነው፤ ከኽረና አናት እስከ ያርፎ፤ ከመቃ ደን እስከ ሺታ ሐይቅ እናስሰዋለን፡፡ ቡሎ ሐይቅ ደርሰን ባርቦ ፏፏቴ እናድራለን፡፡ ገና ምኑ ተነካና!! DIRETUBE NEWS

NO COMMENTS