የአፍሪካ ዝሆኖች ምድር-ጨበራ ጩርጩራ ብሔራዊ ፓርክ

0
859
የአፍሪካ ዝሆኖች ምድር
ጋዜጠኛ ሄኖክ ስዩም በደቡብ ክልል የሚገኘውን አስደናቂ ብሔራዊ ፓርክ ሊያስጎበኘን ነው፡፡

የአፍሪካ ዝሆኖች ምድር-ጨበራ ጩርጩራ ብሔራዊ ፓርክ፤

(ተጓዡ ጋዜጠኛ ሄኖክ ስዩም በደቡብ ክልል የሚገኘውን አስደናቂ ብሔራዊ ፓርክ ሊያስጎበኘን ነው፡፡ የአፍሪካ ዝሆኖች መኖሪያ የሆነውን አስደናቂ መስህብ ለቀናት ቆይቶበታል፡፡ የአፍሪካ ዝሆኖች መኖሪያ ሲል ጨበራ ጩርጩራ ብሔራዊ ፓርክን እንዲህ ያስጎበኘናል፡፡) (ሔኖክ ስዮም በድሬትዩብ)

ደስ የሚልና ወይና ደጋማ አየር ንብረት ባላት ከተማ ውስጥ ነኝ፡፡ እዚህ የመጣሁት ከአዲስ አበባ በጅማ 465 ኪሎ ሜትር ተጉዤ ነው፡፡ አመያ ነኝ፡፡ አመያ የኮንታ ልዩ ወረዳ መዲና ናት፡፡ ደን ሸፍኗታል፡፡ አቀማመጧ ትንግርት ነው፡፡ ለቅንጡ ሎጂዎች ምቹ በሆነ መልከዓ ምድር ያረፈች ከተማ፡፡ ወደ ጨበራ ልሄድ ነው፡፡

ጨበራ የጨበራ ጩርጩራ ብሔራዊ ፓርክ ዋና ጽ/ቤት መገኛ ናት፡፡ ቀበሌዋ ግማሽ ሰዓት ያክል በመኪና ታስጉዛለች፡፡ ከአስደናቂው የተፈጥሮ መስህብ በራፍ የምትገኝ ቀበሌ፡፡ አገሩ ስስት አያውቅም፤ አፈሩ ቸር ነው፡፡ ለአዳም የተሰጠው የመጀመሪያ ምድር ምናልባትም ይሄን የሚመስል ድንግል ምድር ሳይሆን አይቀርም፡፡ ለግቤ አራት ግድብ ፕሮጀክት የተሰራው መንገድ የጨበራን ጉዞ ቀላል አድርጎታል፡፡

ጨበራ ደረስን፤ ይህቺ ትንሽ ቀበሌ ከካፋ ጫፍ እስከ መሎ ከጩርጩራ እስከ ባርቦ ለተሰገሰገው ድንቅ የተፈጥሮ ሀብት ወደብ ናት፡፡ ቀላል እና ደስ የሚል አየር ንብረት ያላት፤ የምትሞቅ ግና ሙቀቱ ሰውን የማይፈታተን፡፡ በፍራፍሬዎቿ ልግስና የደከመውን የምትታደግ፣ በሙዝ ጣዕሟ ከትዝታ ጋር የምትኖር፣ በማንጎዎቿ ፍሬዎች የረገጠ የማይረሳት፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ በህዝብ ጥያቄ የተከለለ ብሔራዊ ፓርክ ደጃፍ ነኝ፡፡ የዳውሮ እና የኮንታ ህዝብ ስካውት ሆኖ ተፈጥሮን ለመታደግ ዘብ የቆመበት የተፈጥሮ ሀብት ከበራፉ የሚናገረው አንዳች ነገር አለ፡፡ ጉዞአችንን ልንጀምር ነው፡፡ መነሻችን አሁን የደረስንባት የፓርኩ ጽ/ቤት ናት፡፡ አዳነ ጸጋዬ የጨበራ ጩርጩራ ብሔራዊ ፓርክ ዋርደን ነው፡፡ እነ ኡቴ እና እነ ጌታሁን ዱር ውለው ዱር የሚያድሩ የጨበራ ጩርጩራ ፓርክ ስካውቶች ናቸው፡፡ አለቃቸው በቀለ ስምሪቱን ሰጥቶ ወደ ዝሆኖቹ ምድር ጉዞአችንን ጀምረናል፡፡

READ  በአዲስ አበባ ባለፉት 20 ቀናት በተደረገ ፍተሻ 263 አሽከርካሪዎች ጠጥተው ተገኝተዋል

በጨበራ አድርገን በቶሺማ ፍል ውሃ…. ከሩቅ የሚታየው ጥቅጥቅ ደን ነው፡፡ የእድሜ ጠገብ ሀገር በቀል እጽዋት ቅርንጫፎች ምድርን ሸሽገዋል፡፡ እዚህ ብዙ ዓይነት ምድር አለ፡፡ አንድ ፓርክ ነው፤ ግን ከረዣዥሞቹ ሳሮች ስትወጡ ግዙፍ ዘንባባዎች ይቀበሉዋችኋል፡፡ እዚህ ህይወት አይሰለችም፡፡ የዝሆኖቹን ግዛት እየተጓዝንበት ነው፡፡

የጨበራ ጩርጩራ ብሔራዊ ፓርክ ፓርክ ሆኖ የተከለለው በ1997 ነበር፡፡ ያኔም ህዝቡ ጠይቆ ነው፡፡ ዛሬም ህዝቡ ታድጎት የሚኖር ነው፡፡ 1400 ካሬ ኪሎ ሜትር የሚሰፋውን፣ በመካከለኛው ኦሞ ሸለቆ ዳውሮ ዞን እና ኮንታ ልዩ ወረዳ መካከል የሚገኘውን ይህንን ድንቅ ተፈጥሮ ማሰስ ጀምረናል፡፡ ሲደክማችሁ እናርፋለን፡፡

ከግዙፍ የዋንዛ ዛፎች ስር፣ ለዓይን ከሚርቁ ረዣዥም የዘንባባ ደኖች መሀል የልብ ምታችን ከድካም በደስታ እስኪደልቅ እናርፋለን፡፡ ጥም የሚቆርጡ ምንጮች ዳርቻ እናርፋለን፡፡ እንደ ቧንቧ የሚጠጡ እንደ ከተማ ውሃ አተት የማይሰጋባቸው ወንዞች ገብተን እንታጠባለን፡፡ እዚህ ተፈጥሮ ንጹህ ነው፡፡

እዚህ እውነተኛው አየር ይሳባል፡፡ እጽዋቱ የመኪና ጢስ አያውቁም፡፡ እናም በእግር እየተጓዝን ነው፡፡ የመጀመሪያ መድረሻችን ነጭ ውሃ ናት፡፡ በለምለም መስክ በጠራ ውሃ ዳር ዝሆን እየረገጠ በቀየሰው መንገድ፤ እውነት ሀገሬ ይሄን የመሰለ ከክፉ ባለመጥረቢያ እጆች የታደገችው ደን አላት? እያልን ጉዞአችንን ቀጥለናል፡፡ ነጭ ውሃን ጠጥተን ኤርፓ ዝሆኖቹ ሰፈር እንወርዳለን፡፡ DIRETUBE NEWS

NO COMMENTS