በሙስና ወንጀል የተጠረጠሩ 125 ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር አውሎ በምርመራ እያጣራ መሆኑን የፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ

0
2591
የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን
በሙስና ወንጀል የተጠረጠሩ 125 ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር አውሎ በምርመራ እያጣራ መሆኑን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ

በመዲናዋ እየተከናወኑ የሚገኙ የልማት እንቅስቃሴዎች በሚፈለገው ፍጥነትና የህዝብ እርካታን ሊያመጣ በሚችል አቅጣጫ እንዳይጓዝ እንቅፋት ከሆኑ የመልካም አስተዳደር ችግሮች ውስጥ በተለያዩ የመንግስትና የአስተዳደር አካላት፣ በአንዳንድ የመንግስት ሰራተኞች በተለያየ ደረጃ የሚፈፀሙ የሙስና ወንጀሎች ዋነኛዎቹ እንደሆኑ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

ችግሮቹን በመሰረታዊነት ለመቅረፍ መንግስት በተለይ ከቅርብ ጊዘ ወዲህ የጀመራቸው የመልካም አስተዳደር እና የጥልቅ ተሃድሶ ንቅናቄ በማድረግ ላይ እንደሚገኝ ይታወቃል ብሏል ኮሚሽኑ በላከው መግለጫ፡፡

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት የተጀመረውን ሰፊ ንቅናቄ መነሻ በማድረግ አርብ ታህሣስ 7 ቀን 2ዐዐ9 ዓ.ም ባደረገው ኦፕሬሽን በተለያዩ የከተማው አስተዳደር መሥሪያ ቤቶች ውስጥ በተፈፀመ የሙስና ወንጀል የተጠረጠሩ 125 ግለሰቦች በቁጥጥር ስር አውሎ ምርመራ እያጣራ እንደሚገኝ አስታውቋል፡፡

በፖሊስ ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር የዋሉት 22 አመራሮች ፣ 99 ሰራተኞች እና 4 ግለሰቦች መሆናቸውን ከኮሚሽኑ የተገኘው መረጃ ያስረዳል፡፡

የመንግስትን ቤት ወደ ግለሰቦች እንዲዞር ማድረግ፣ በህገ ወጥ መንገድ የተሽከርካሪ ሰሌዳ መስጠት፣ በሌሉ ሰዎች ስም መንጃ ፍቃድ መስጠት፣ የመንግስት ገንዘብ ማጉደል፣ ከህግና አሰራር ስርአት ውጪ ለግለሰቦች ያለጨረታ ስራዎችን መስጠት ግለሰቦቹ ከተጠረጠሩባቸው ወንጀሎች ውስጥ እንደሚገኙ ኮሚሽኑ ገልጿል፡፡

የከተማው ነዋሪ በተለያዩ መድረኮች የሚያነሣቸው የመልካም አስተዳደር ችግሮች እንዲባባሱ ያቀጣጣይነት ሚና ያላቸው እነዚህ የወንጀል ድርጊቶች በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የህብረተሰቡን ፍትሃዊ ተጠቃሚነት የሚያሳጡ መሆናቸውን ህዝቡ ተገንዝቦ ህገ-ወጥነትን ለመከላከል ኮሚሽኑ የሚያደርገውን ጥረት በመደገፍ በከተማ ውስጥ የሚፈፀሙ የሙስና ወንጀሎችን በማጋለጥና መረጃ በመስጠት ህዝቡ እያደረገ ያለውን ትብብር አጠናክሮ እንዲቀጥል ኮሚሽኑ ጥሪውን አቅርቧል፡፡

የሙስና ወንጀል ድርጊቶችን በኮሚሽኑ ስልክ ቁጥር ዐ111 56 83 11 ወይም በአካል ቀርቦ መጠቆም እንደሚቻል የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አስታውቋል፡፡ebc

READ  ለ25 ታላላቅ አርበኞች የመታሰቢያ ቴምብሮች ታተሙ

NO COMMENTS