አሸተን ማርያም-የነአኩቶ ለአብ ድንቅ ስራ

0
637
አሸተን ማርያም-
አሸተን ማርያም-የነአኩቶ ለአብ ድንቅ ስራ

አሸተን ማርያም-የነአኩቶ ለአብ ድንቅ ስራ፤

(ተጓዡ ጋዜጠኛ ሄኖክ ስዩም ከላሊበላ ከተማ አቅራቢያ የምትገኘውን ታሪካዊ ስፍራ ሊያስጎበኘን ወደ አሸተን ማርያም ይዞን ተጉዞ ነበር፡፡ አስደናቂውን የተራራ ስንጥቅ መንገድ አልፎ ከአሸተን ማርያም ደጃፍ ቆሟል፡፡ ዛሬ ከዐለት ወደ ተሰራችው ታሪካዊ መካነ ቅርስ ይዞን ገብቶ የነአኩቶ ለአብ ድንቅ ስራ ሲል አሸተን ማርያምን እንዲህ ያስጎበኘናል፡፡) (ሔኖክ ስዮም በድሬትዩብ)

የዛጉኤ ነገስታት ዓለምን አስደምመዋል፡፡ ዐለት እንደ ሸራ ተአምር ሲሳልበት አሳይተዋል፡፡ ኢትዮጵያውያን ቋጥኝ ከተማ የሚያደርጉ አባቶች እንደነበራቸው ያሳዩ ጥበበኞች ነበሩ፡፡ እነ ላሊበላ፣ እነ ይምረሐነ፣ እነ ነአኩቶ ለአብ ዛሬም ዓለም እጁን አፉ ላይ ጭኖ ቃል መናገር እስኪያቅተው የተደመመባቸው ቅርሶችን ትተው አልፈዋል፡፡

አሸተን ነኝ፡፡ አናቷን ከዝናብ እና ጸሐይ ለመታደግ የማያምር የቆርቆሮ ጣሪያ እንደ ጥላ ጋርደውላታል፡፡ ከስር ከነሞገሷ ውቅሯ አለች፡፡ ከ1207 እስከ 1247 ዓ.ም. የነገሰው ነአኩቶ ለአብ ለነፍሱ ካስቀመጣቸው የታሪክ አሻራዎች አንዷ ይህች ድንቅ ውቅር ናት፡፡

እንዳያሳስታችሁ ስትገቡ በቀኝ የሚገኘው እና ግዙፉ የአራት መዐዘን ቅርጽ ያለው ውቅር ነው በነአኩቶ ለአብ የታነጸው፤ በስተግራ ያለው የመጣንበትን ዐለት መንገድ ያደረጉት አባ ገብረ ሥላሴ ወይም አባ ደበሎ የሚባሉ አንድ አባት የሰሩት ነው፡፡ በዐፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመን፡፡

አሸተን አሰራሯ እጅግ ይደንቃል፡፡ የዐለቱ ጥንካሬ እና ዓይነት ደግሞ እንደምን ተወቀረ የሚያሰኝ ነው፡፡ ዛሬ ላይ ላስበው ላለ ደግሞ አሸተን የተሰራችበትን ዐለት የተሸከመ እስኪመስለው ሊከብደው ይችላል፡፡ በዚህ ድንቅ አራት መዐዘን ግዙፍ አለት ውስጥ ታሪካዊቷ ቤተ ክርስቲያን አለች፡፡ የተሰራችበት ዐለት ከምድር የሚገናኘው ወለሉ ብቻ ነው፡፡

READ  Esmeralda Farms Closes Down following Attack

መላው አካሏ ቀድሞ ከነበረችበት ዐለት ተላቋል፡፡ የእንጨት በሯ ግዙፍ እና የተለየ ጥበብ ባለው መልኩ የታነጸ ነው፡፡ ወደ ውስጧ ሲገባ የሚቀበለው በማዕዘኑ ላይ የሚገኙት ጌጦች እና ቅኔ ማህሌቷ ነው፡፡ አሸተን ውብ እና ድንቅ የቅብ ጥበብ ባላቸው ቅዱሳት ስዕሎች ያሸበረቀች ናት፡፡

በርካታ የገበታ ላይ ስዕሎች እና ከእንጨት የተሰሩት የስዕል መጽሐፎች ለጎብኚ ይታያሉ፡፡ ቅዱሳኑ ነገስታት መስቀሎችም ይገኙባታል፡፡ ጎብኚዎች የፈለጉትን የሚጠይቁበት ለሚጠይቁበት መልስ የሚያገኙበት ስፍራ ነው፡፡ የውጪ ጎብኚዎች ላሊበላን ከረገጡ አሸተን አይቀሩም፡፡ እንደ አለምነው ያሉ ትጉ ገበሬዎች የመስከረም ማርያም አሸተንን የረገጠ ደጃፋችንን ሳይረግጥ አያልፍባትም የሚሉባት የደጋጎች ሀገር፡፡

ከጀርባችን አራቱ ነገስታት የጸለዩበት ዋሻ ይገኛል፡፡ ዋሻው ሽቅብ የጎነችዋ ተራራ አናት ላይ ያረፈ ነው፡፡ እሱን አልፎ ሽቅብ ወደ ሚታየው አናት መውጣት የሚፈልግ አርሴማን ያገኛል፡፡ አርሴማ ቀደምት ከሚባሉ የአካባቢው ቤተክርስቲያናት የአንዱ መገኛ ነበረች፡፡ በፍርስራሹ ስፍራ አዲሷን ደብር ተክለውባታል፡፡ እዚያ ሆኖ ሩቅ የለም ከእመኪና አቡነ ዮሴፍ፣ ከላስታ ተራሮች እስከ ስሜን አናት ይታያል፡፡

ይሄንን ሁሉ ለመድረስ ግን አሸተን መምጣት ግድ ነው፡፡ DIRETUBE NEWS

NO COMMENTS