ድሬቲዩብ ለድምጻውያን በዩቱብ ገቢ እንዲያገኙ በማድረግ ከፍተኛ እገዛ እያደረገ ነው

0
2186
ድሬቲዩብ
  • በ7 ወር ውስጥ 5 ሚ.ተመልካች ያገኘ የሙዚቃ ቪዲዮ ከ100ሺ ብር በላይ ተከፍሎታል – ድሬቲዩብ
  • ዝነኛዋ አቀንቃኝ ሪሃና ዓምና ከዩቲዩብ 55 ሚ.ዶላር አግኝታለች

የዛሬ ሁለት ዓመት የተለቀቀው የኮሪያዊው የፖፕ አቀንቃኝ PSY “ጋንጋም ስታይል” የተሰኘ ዝነኛ የቪዲዮ ሙዚቃ በዩቲዩብ ከ2 ቢሊዮን በላይ ተመልካች ያገኘ የመጀመሪያው ቪዲዮ ነበር፡፡ አቀንቃኙም በአንድ ነጠላ ቪዲዮ ቱጃር ለመሆን የበቃ ሲሆን ከዩቲዩብ 2 ሚ.ዶላር (50 ሚ.ብር ገደማ) ተከፍሎታል፡፡ በምዕራቡ ዓለም ታዋቂ ዘፋኞች በዩቲዩብ በሚሊዮን የሚቆጠር ተመልካች ያያቸዋል፡፡

ይሄ ደግሞ የገንዘብ ሃብታቸውን ይጨምርላቸዋል፡፡ ዝነኛው ካናዳዊ ዘፋኝ ጀስቲን ቢበር በየዓመቱ በአማካይ 16 ሚ.ዶላር ገቢ ያገኛል – ከዩቲዩብ። ሌላዋ ዝነኛ አቀንቃኝ ሪሃና ደግሞ ባለፈው ዓመት በዩቲዩብ ላይ ከለቀቀቻቸው የሙዚቃ ቪዲዮዎች 55 ሚ.ዶላር አግኝታለች፡፡ ሌዲ ጋጋ እንዲሁ ዓምና ከዩቲዩብ 23 ሚ. ዶላር ወደ ካዝናዋ አስገብታለች።

የኢትዮጵያ ድምጻውያንስ ከዩቲዩብ ምን ያህል እየተጠቀሙ ነው?

ወጣቷ ድምፃዊት ቤቲ ጂ. “ናና ድማዬ” እና “አስብሃለሁ” የተሰኙ የሙዚቃ ቪዲዮዎቿን በዩቲዩብ ለቃለች- በድሬ ቲዩብ በኩል፡፡ ነገር ግን ክፍያው በተመልካቹ መጠን የሚሰላ በመሆኑ ገንዘብ ለመጠየቅ ወደ ድሬ ቲዩብ አለመሄዷን ትናገራለች፡፡ ‹‹የተመልካቹ ቁጥር ብዙ ስላልሆነ ክፍያ አልጠየቅሁም›› ብላለች-ድምፃዊቷ፡፡ አርቲስቱ በተለያዩ መድረኮች በሚሰራው ስራ እንጂ እንደዚህ አይነት ክፍያዎችን እየጠበቀ ይኖራል ብዬ አላስብም ያለችው ቤቲ፤ በእንደነዚህ አይነት ሚዲያዎች ዘፈንን መልቀቅ ከገንዘቡ ይልቅ እውቅናው እንደሚልቅ ለአዲስ አድማስ ገልፃለች፡፡

ድምፃዊ ሄኖክ መሀሪም እንዲሁ፤ “የኔነሽ”፣ “እወድሻለሁ” እና “የኪራይ ቤት” የተሰኙ ሶስት የሙዚቃ ቪዲዮዎችን ከድሬቲዩብ ጋር በመዋዋል ዩቲዩብ ላይ መልቀቁን ይናገራል፡፡ ሆኖም በዩቲዩብ ከታየው ይልቅ በድሬቲዩብ የታየው ይበልጣል ይላል፡፡ “ለምሳሌ አንዱ ዘፈኔ በድሬ ቲዩብ መቶ ሺህ፤ በዩቲዩብ ደግሞ 20ሺህ ሰው ተመልክቶታል፤ ክፍያ የሚገኘው በዩቲዩብ ስለሆነ በአብዛኛው ተጠቃሚው አርቲስቱ ሳይሆን እንደ ድሬ ቲዩብ ኤጀንት ሆኖ የሚሰራ ድርጅት ነው” ብሏል – ድምፃዊው፡፡ በእንደነዚህ አይነት ነገሮች ተማርሬያለሁ የሚለው ሄኖክ፤ ኤጀንቶችን በመተው ኒውዮርክ በሚገኙ ዘመዶቹ በኩል ቀጥታ ከጎግል ጋር በመዋዋል ዘፈኖቹን በዩቲዩብና አማዞን ላይ መልቀቁን ይገልፃል፡፡ ይሁን እንጂ ይህም የራሱ ፈተና አለው፤ ይላል ሄኖክ፡፡ “በዘመዶቼ በኩል እንደ ዩቲዩብና አማዞን ያሉ የኦንላይን ግብይቶች ላይ ዘፈኖቼን ብለቅም የእኔ ሙዚቃዎች አማርኛ በመሆናቸውና ተመልካቹ የእንግሊዝኛ ዘፈን አድማጭ በመሆኑ ብዙም ውጤታማ አልሆነም›› ሲል አስረድቷል።

በቅርቡ ባወጣው “ከራስ ጋር ንግግር” በሚል አልበሙ በአጭር ጊዜ ውስጥ ከፍተኛ ተቀባይነትን ያገኘው ድምፃዊ ሳሚ ዳን በበኩሉ፤ “ፍቅር ሰላም”፣ “ጠፋ የሚለየን” እና “አንቺ የኔ” የሚሉ ሦስት ዘፈኖቹን በተመሳሳይ መንገድ በዩቲዩብ መልቀቁን ይናገራል። የተመልካቹ ቁጥር አንድ ሚሊዮን ሲሞላ 20ሺህ ብር እንደሚከፈለኝ ከድሬ ቲዩብ ጋር ተስማምቻለሁ የሚለው አርቲስቱ፤ነገር ግን እስካሁን የተገኘው ተመልካች ብዙ ስላልሆነ ክፍያ አልጠየቅሁም ብሏል፡፡ “እኔ ከገንዘቡ በላይ ፕሮሞሽኑ ይበልጣል ባይ ነኝ” የሚለው ሳሚ ዳን፤ አሁን አሁን ክፍያ መጣ እንጂ ቀድሞ በነፃ ዩቲዩብ ላይ ዘፈን በመልቀቅ ሥራዬን አስተዋውቅ ነበር ብሏል፡፡

READ  የመኖሪያ ቤት የማግኘት መብትን ለማረጋገጥ በከተሞች 75ዐ ሺ አዳዲስ ቤቶች ግንባታ ይከናወናል

ድሬ ቲዩብ የሙዚቃ ቪዲዮችን በዩቲዩብ ከመልቀቁም በላይ ሥራዎችን በራሱ ሳይት ላይ በደንብ ያስተዋውቃል ያለው ድምፃዊው፤እጅግ ግልፅና ተአማኒነት ባለው መልኩ የሚሰራም ለአርቲስቱም ድጋፍ የሚያደርግ ብቸኛው ተቋም ነው ሲል ድሬ ቲዩብን አሞካሽቷል። ከዚህ ቀደም ከተለያዩ ተቋማት ጋር ስምምነት ለመፈጸም ሞክሮ እንደነበር ያወሳው ሳሚ ዳን፤ ውሎቹ የተሳሰሩና የተወሳሰቡ ከመሆናቸውም በላይ ለአርቲስት የማይመጥኑና ለተቋማቱ ጥቅም ብቻ የሚያደሉ እንደሆኑ መታዘቡን ለአዲስ አድማስ ጠቁሟል። መቀመጫው በአገር ውስጥ የሆነ፣ በህጋዊ መንገድ ተመዝግቦ የሚንቀሳቀስ፣ አርቲስቱ የሥራው ባለመብት ሆኖ እንዲቀጥልና እንዲጠቀም የሚያደርግ እንዲሁም አንድ ቪዲዮ ክሊፕ በዩቲዩብ ታይቶ ያመጣውን ክፍያ በየሶስትና ስድስት ወሩ በኢ-ሜይል የሚያሳውቅ ተቋም ነው ይላል-ድሬ ቲዩብን፡፡ “እኛ አልበሙን በቅርቡ እንደ መስራታችን ዩቲዩብ ላይ የለቀቅነውም በቅርቡ ነው፤ አሁን ለምን ክፍያ አልመጣም ወይም አላደገም ብለን አናዝንም” ያለው አርቲስቱ፤ “ሁሉም በጊዜው ጥሩ ነገር ይዞ ይመጣል፤ አሁን ድሬ ቲዩብ ጥሩ ስራዎችን እየሰራ ነው” ሲል አስተያየቱን ሰንዝሯል፡፡
ስሟ እንዲጠቀስ ያልፈለገች አንጋፋ ድምፃዊት ግን በዩቲዩብ ጥሩ ተከፋይ ነኝ ትላለች፡፡

በዩቲዩብ የለቀቀችው አንድ የሙዚቃ ቪዲዮ በአንድ ዓመት ውስጥ ከ1.7 ሚሊዮን በላይ ተመልካች በማግኘቱ ከድሬ ቲዩብ ጠቀም ያለ ክፍያ ማግኘቷንም ለአዲስ አድማስ ገልፃለች፡፡ ‹‹በአገራችን ብዙ ጥሩ ጥሩ የሙዚቃ ቪዲዮዎች ቢኖሩም በዩቲዩብ አይለቀቁም፤ ለዚህም ምክንያቱ የአርቲስቶች የግንዛቤ ችግር ነው” ባይ ነች፤ ድምፃዊቷ። በዩቲዩብ ከፍተኛ ተከፋይ ለመሆን አንድም አርቲስቱ በቂ ግንዛቤ ኖሮት እንደነ ድሬ ቲዩብ ባሉ ሚዲያዎች ሥራውን መልቀቅ አለበት፤ ሁለትም ጥሩ የሙዚቃ ቪዲዮ መስራት ያስፈልጋል ያለችው ድምጻዊቷ፤ “አርቲስቶች በዚህ ዙሪያ በቂ መረጃና ግንዛቤ በመጨበጥ ምርጥ የሚሏቸውን ሥራዎች አንቀው ከመያዝ በዩቲዩብ ላይ ቢለቁ ከትውውቁ በተጨማሪ ጥሩ ገቢ ያገኙበታል። እዘረፋለሁ ወይም እጭበረበራለሁ ከሚል ፍርሀት መውጣት አለባቸው” ስትል መክራለች፡፡

READ  በቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ቃጠሎ እንዲነሳ በማድረግ 23 ታራሚዎችን ደብድበዋል በተባሉ ተከሳሾች ላይ ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጠ

የድሬ ቲዩብ መስራችና ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ ቢኒያም ነገሱ ከአርቲስቶች ጋር የሚፈፅሙትን ስምምነት በተመለከተ ከአዲስ አድማስ ተጠይቀው ሲመልሱ፣ ‹‹ዩቲዩብ የጎግል ኩባንያ ሌላው ድርጅት ነው፤ ማንኛውም የቪዲዮ ባለቤት ነኝ የሚል ድርጅትም ሆነ ግለሰብ በራሱ ኢ-ሜይል ዩቲዩብ ላይ ጭኖ ተጠቃሚ የሚሆንበትን ስርዓት አመቻችቷል፤ ይህም አሰራር “ሰልፍ ሞኒታይዜሽን” ይባላል፡፡ ሌላው “ፕሪሚየም ሞኒታይዜሽን” የሚባለው ደግሞ ለድርጅቶች ብቻ የሚሰጥ ነው፤ ይህ አሰራር ኢትዮጵያ ውስጥ ለማንኛውም ድርጅት አልተሰጠም፤ ድሬ ቲዩብ ይህንን መብት ለማግኘት ገና በሂደት ላይ ነው” ብለዋል፡፡

ድርጅቱ መብቱን ሳያገኝ እንዴት ከአርቲስቶች ጋር ውል ይፈፅማል የሚል ጥያቄ የቀረበላቸው አቶ ቢኒያም፤ ድርጅታቸው ይህንን ስራ ለመስራት እንዲያስችለው ኬንያ ከሚገኝ “ኒኖግማ” የተባለ ድርጅት ጋር ስምምነት መፈራረሙን ይናገራሉ፡፡ ድርጅቱ የአንድን አርቲስት የኮፒ መብት ከዘረፋና ከማጭበርበር የሚጠብቁ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን የሚያቀርብ ሲሆን ድሬ ቲዩብ ደግሞ ዲጂታል ማኔጅመንቱን በመያዝ፣ራሱንም ሆነ አርቲስቶችን ተጠቃሚ በማድረግ የሚሰራ ብቸኛው ኢትዮጵያዊ ተቋም ነው ብለዋል፡፡

ድሬ ቲዩብ አንድ የሙዚቃ ባለቤት የሰጠውን ቪዲዮ ሌላ ህገ – ወጥ አካል የራሱ አድርጎ ሌላ ሳይት ላይ ወይም ዩቲዩብ ላይ እንዳይጭነው ወዲያው ‹‹ብሎክ አድርግልን፤ እኛ እያስተዳደርነው ነው” ብለን ለመናገር የሚያስችለንን አቅምና ሥልጣን የኬንያው ኩባንያ ይሰጠናል ብለዋል፡፡ ይህ ደግሞ የሙዚቃ ቪዲዮዎችን፣ ፊልሞችንና ተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማዎችን ባለቤቶች መብት ጭምር እንድንጠብቅ የሚያስችለን አቅምና መብት ያጎናጽፈናል ያሉት ማኔጂንግ ዳይሬክተሩ፤ በዚህ መንገድ ከመቶ በላይ ከሚሆኑ ድምፃዊያን ጋር ስምምነት ፈፅመው እየሰሩ መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡

ለመሆኑ ከዚህ ስምምነት ድሬ ቲዩብ ምን ይጠቀማል? ድምጻውያኑስ? የተቋሙ መሥራች እንዲህ ያስረዳሉ፡- “ድሬ ቲዩብ የጥበብ ስራዎችን ከዘረፋና ከመጭበርበር ለማዳን ከኬንያ ኩባንያ ጥበቃ የሚያደርገውን መሳሪያ አምጥቶ እያስተዳደረ በመሆኑና በተመልካች ብዛት እየለካ አርቲስቱን ተጠቃሚ ስለሚያደርግ ለሚሰራው ስራ የራሱን ጥቅም ከጎግል ያገኛል፤ ጎግል ደግሞ እነዚህ ቪዲዮዎች በሚታዩበት ወቅት ማስታወቂያዎችን በመልቀቅ ከሚገኘው ገቢ ለአርቲስቶች ከፍሎ የራሱን ድርሻ ይወስዳል” ብለዋል፡፡

በሰባት ወር ውስጥ 5 ሚሊዮን ተመልካች ያገኘ አንድ ኢትዮጵያዊ የሙዚቃ ቪዲዮ ባለቤትም ከድሬ ቲዩብ ከመቶ ሺህ ብር በላይ እንደተከፈለው አቶ ቢኒያም ለአብነት ጠቅሰዋል፡፡ “የሙዚቃ ቪዲዮዎችን በዩቲዩብ ከመልቀቃችን በተጨማሪ በድሬ ቲዩብና በዚሁ ዌብ ሳይት የፌስ ቡክ ገፅ ላይ በደንብ እናስተዋውቃለን” የሚሉት ማኔጂንግ ዳይሬክተሩ፤ አንዲት ወጣትና አዲስ ድምፃዊት በአጭር ጊዜ ውስጥ በዩቲዩብ ባገኘችው ተቀባይነት ከፍተኛ ክፍያ ከማግኘቷም በላይ ሌላ ሙዚቃ በላቀ የጥራት ደረጃ እንድትሰራ ድሬ ቲዩብ በቅድሚያ ሙሉ ክፍያ እንደከፈላት ተናግረዋል፡፡

READ  የቀድሞው የሰማያዊ ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ሀላፊ አቶ ዮናታን ተስፋዬ የክስ መከላከያውን አቀረበ

የአርቲስቱን የክፍያ መጠን ከፍና ዝቅ የሚያደርጉ ምክንያቶች ሁለት ናቸው ይላሉ – አቶ ቢኒያም፡፡ “አንዱ የእይታ መጠን ወይም የተመልካች ቁጥር ሲሆን ሁለተኛው ጥሩ ሙዚቃ የመስራትና ያለመስራት ጉዳይ ነው›› ብለዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት አብዛኞቹ ተወዳጅነትን የተቀዳጁ ወጣት ድምጻውያን በዩቲዩብ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ተመልካች እያገኙ መሆኑን ጠቅሰው፣ አንጋፋዎቹም ብዙም ባይሆኑ ቪዲዮዎቻቸው በብዛት እየታየላቸው ነው ይላሉ፡፡

በተመልካች ብዛት በዩቲዩብ እየመሩ ከሚገኙት ኢትዮጵያውያን ዘፋኞች መካከል አርቲስት ዳዊት ነጋ ይገኝበታል፡፡ ድምፃዊው “ወዛመይ” የተሰኘውን የትግርኛ ዘፈኑን በ7 ወራት ውስጥ 5 ሚሊዮን 9ሺህ 166 ሰዎች የተመለከቱለት ሲሆን ድምፃዊ ታምራት ደስታ ደግሞ “ሰሊና” የተሰኘ ዘፈኑን በአንድ ዓመት ውስጥ ከ2.2 ሚ. በላይ ሰዎች ተመልክተውለታል፡፡ ድምፃዊት ሰላማዊት ዮሃንስ እንዲሁ ከ8 ወር በፊት የለቀቀችው “በልጃሎ” የተሰኘ የሙዚቃ ቪዲዮ ከ2.7 ሚሊዮን በላይ ተመልካች ያገኘላት ሲሆን “በባይተዋር ጎጆ” የተሰኘው የታረቀኝ ሙሉ ዘፈን በአንድ አመት ውስጥ ከ1.7 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ተመልክተውለታል፡፡ “የኛ” በሚል የሚታወቁት አምስት ሴት ድምጻውያን ከአንድ ዓመት በፊት የለቀቁት “ስደት” የተሰኘ የሙዚቃ ቪዲዮ እንዲሁ ከ1.1 ሚ. በላይ ሰዎች የተመለከቱት ሲሆን ድምጻ ጃኪ ጎሲ ከአንድ ወር በፊት የለቀቀው “ዋንኮ” የሚል የኦሮምኛ ዘፈን ቪዲዮ በአንድ ወር ውስጥ 732 ሺ 637 ተመልካች ማግኘቱን ለማወቅ ችለናል፡፡ “አንዳንድ ህገ ወጥ ድርጅቶች ቪዲዮ እንሰራላችኋለን፤ ይህን ያህል እንከፍላችኋለን እያሉ አርቲስቶችን በማጭበርበር ቪዲዮውን የራሳቸው ንብረት ያደርጋሉ” ያሉት የድሬ ቲዩብ መሥራች፤አርቲስቶች ከእንደነዚህ አይነት ህገ ወጦች ራሳቸውን መጠበቅ እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡

ድሬ ቲዩብ ከማኔጅመንቱ፣ ከፕሮሞሽኑና የባለመብትን ንብረት ከዘረፋ ከመጠበቅ ባሻገር ቪዲዮው ሲታይ የሚለቀቁ ማስታወቂያዎች የብልግና እንዲሁም የሞራል ልዕልናን የሚነኩና ከስርዓት ውጭ እንዳይሆኑ እንደሚቆጣጠር ጠቁመው፤ ተቋማቸው እስከዚህ ድረስ ለደንበኞቹ እንደሚጠነቀቅና ህጋዊነቱን በጠበቀ መልኩ እንደሚንቀሳቀስ አስረድተዋል። ድርጅቱ በዚህ ዘርፍ ለበርካታ አመታት የተሰማራ ቢሆንም እስካሁን ድረስ አንድም ቅሬታም ሆነ ክስ ከደንበኞቹ ቀርቦበት አያውቅም ብለዋል፡፡

ሬቲዩብ በየዓመቱ ስኬታማ አርቲስቶችን እንደሚሸልምና ባለፈው አመትም ለሶስተኛ ጊዜ መሸለሙን ጠቁመው ሽልማቱና ማበረታታቱ ቀጣይ መሆኑን አቶ ቢንያም ገልፀዋል፡፡ Addis Admas

NO COMMENTS