ማንነቱ ያልታወቀ ግለሰብ በቆሻሻ ገንዳ ውስጥ በእሳት ተቃጥሎ ሞተ

0
2860
NEWS.ET
Image: Garbage Collection in Addis Ababa

በአዲስ አበባ የካ ክፍለ ከተማ ወረዳ አንድ ለግዜው ማንነቱ ያልታወቀ ግለሰብ ታህሳስ 13 ቀን 2009 ዓ.ም ንጋት ላይ በአካባቢው በሚገኝ የቆሻሻ ገንዳ ውስጥ በእሳት ተቃጥሎ ህይወቱ ማለፉን የአይን እማኞችን ጠቅሶ አዲስ አድማስ ጋዜጣ ዘግቧል፡፡

ጋዜጣው በአካባቢው በጥበቃ ስራ ላይ የተሰማሩ ናቸው ያላቸው አቶ ተሾመ የተባሉ የአይን እማኝ ከእሳቸው በቅርብ ርቀት ላይ በሚገኝ የቆሻሻ ገንዳ ውስጥ ከንጋቱ 12 ሰዓት አካባቢ ከፍተኛ መጠን ያለው እሳት ሲነድ መመልከታቸውን እና ወደ ገንዳውም ተጠግተው ሲመለከቱ የሚቃጠለው ሰው መሆኑን መገንዘባቸውን እና የሚቃጠለው ሰውም ሰውነቱን ሲያወራጭ መመልከታቸውን ነግረውኛል ብሏል፡፡

የአይን እማኝ የተባሉት የጥበቃ ሰራተኛም ከሌላ ባልደረባቸው ጋር በመሆን ለፖሊስ ማመልከታቸውን እና ፖሊስም በአካባቢው ፈጥኖ በመድረስ እሳቱን በውሃ ቢያጠፋም የግለሰቡን ህይወት ማትረፍ እንዳልተቻለ ጨምረው እንደተናገሩም ጋዜጣው በዘገባው አመልክቷል፡፡

በሌላ በኩል በአካባቢው በቆሻሻ ገንዳ ጥበቃ እና ቁጥጥር ስራ ላይ ተሰማርተው እንደሚገኙ የተገለጸው ሌላው የጋዜጣው የአይን እማኝ አቶ ሸበላው ከበደ በጥበቃ ማረፊያ ቤታቸው ውስጥ እንዳሉ የሰው ጩኸት መስማታቸውን እና በፍጥነት ከቤት ሲወጡ በቅርባቸው ያለው የቆሻሻ ገንዳ በእሳት ተያይዞ መመልከታቸውን እንዲሁም የሚቃጠለውም ሰው መሆኑን ሲረዱ በድንጋጤ ጉዳዩን ለፖሊስ ማመልከታቸውን እንደገለጹም በጋዜጣው ተጽፏል፡፡

ፖሊሶች እሳቱን በውሃ አጥፍተው የግለሰቡን አስክሬን ከገንዳው ቢያወጡትም የሟች ማንነት መለየት በማይቻልበት ሁኔታ መቃጠሉን አስክሬኑም ለምርመራ መወሰዱን እኚሁ የአይን እማኝ ለጋዜጣው አስደርተዋል ተብሏል፡፡

ጋዜጣው ግለሰቡ እራሱን በራሱ አቃጥሎ ይሁን አሊያም በሌላ ምክንያት አደጋው እንደደረሰ እንዳልተረጋገጠ የፖሊስ ምንጮች ጠቁመውኛል ብሏል፡፡ Addis Admas

READ  ተፈናቃይ አርሶ አደሮች ለዓመታት ታጥረው የተቀመጡ ቦታዎቻቸው ኪሳራ ተሰልቶ ካሳ እንዲከፈላቸው ጠየቁ

NO COMMENTS