ኮሜዲያን አስረስ በቀለ የመጀመሪያው ሚሊየነር ኮሜዲያን

0
5716
ኮሜዲያን አስረስ በቀለ
Image: ኮሜዲያን አስረስ በቀለ & Almoudi

ከቁም ነገር

‹ከአንድ ቁጥር ቀጥሎ ይህንን ያህል ዜሮ ተፅፎ አይቼ አላውቅም›

ብዙዎች የኢትዮጵያ ልጆች የተረት አባት የሆኑት የአባባ ተስፋዬ ደቀ መዝሙር አድርገው ይቆጥሩታል ኮሜዲያን አስረስ በቀለን፡፡ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የህፃናት ፕሮግራም ላይ የቼሪ ገፀ ባህሪን ተላብሶ ብርካታ ህፃናትን ሲያዝናና የኖረው አስረስ ከቴሌቪዥን ስክሪን ከተለየ በኋላም የህፃናትን ነገር አልተወም፡፡

የህፃናትን ጠባይ የሚያንፁና የሚያዝናኑ ስድስት ያህል መፅሀፍትን ያሳተመው አስረስ ሰሞኑን የዓመታት ልፋትና ድካሙን ዋጋ የሚሰጥ ስጦታ ተበርክቶለታል፡፡ ከኮሜዲያን አስረስ በቀለ ጋር ስለዚሁ ጉዳይ ያደረግነው አጠር ያለ ቃለ ምልልስ ይህንን ይመስላል፡፡

ቁም ነገር፡- በቅድሚያ እንኳን ደስ ያለህ;
አስረስ፡- እንኳን አብሮ ደስ አለን፤

ቁም ነገር፡- ሰሞኑን አንድ ለየት ያለ ያልተጠበቀ ነገር/ሰርፕራይዝ/ ገጥሞሃል ይባላል፤ ምንድነው?
አስረስ፡- ልክ ነው፤ እግዚአብሔር ስለተመለከተኝ ነው፤ እግዚአብሔር ይስጣቸውና ክቡር ሼህ መሐመድ አሊ አላሙዲን ናቸው ሰርፕራይዝ ያደረጉኝ፤ ተጠርቼ የአንድ ሚሊየን ብር ቼክ ተሰጥቶኛል፡፡

ቁም ነገር፡- የምታውቀው ነገር ነበር?
አስረስ፡- በፍጹም፤ የማውቀው ነገር የለም፤ አላሰብኩም፤ግን አንድ ቀን እግዚአብሔር ያየኛል የሚል እምነት ስላለኝ ሁል ጊዜ ፀሎት አደርግ ነበር፡፡ እስከ ዛሬ ድረስ ስራ ስሰራም እንዲህ አይነት ነገር ይደረግልኛል ብዬ ሳይሆን መስራት ስላለብኝ ነበር የምሰራው፡፡ ግን የሚያይ እግዚአብሔር ስላለ በሼህ አላሙዲን በኩል ድካሜን አይተው ይኸው ይህንን ነገር አድርገዋል፡፡

ቁም ነገር፡- በምን መልኩ ነው ከእሳቸው ጋር የተገናኘከው?
አስረስ፡- ከእሳቸው ጋር አልተገናኘሁም ፤ ብቻ ወደ ቤቴ ልገባ ስል ስልክ ተደውሎ ተጠራሁ፤

ቁም ነገር፡- የት?
አስረስ፡- ሸራተን፡፡

ቁም ነገር፡- ማነው የደወለልህ?
አስረስ፡- ሰራዊት ፍቅሬ መጀመሪያ ላይ ሲደውልልኝ ገርሞኝ ነበር፤ ምክንያቱም ሰሞኑን የኤፍ ኤም ሬዲዮ ፈቃድ ተሰጥቶታል ተብሎ ስለነበር ለዚያ ጉዳይ የደወለ ነበር የመሰለኝ፤ ከዚያ እሱም ራሱ ‹እንኳን ደስ ያለህ የሬዲዮ ፈቃድ አገኘሁ› አለኝ፤ እንኳን ደስ ያለህ አልኩት ፡፡ ከዚያ ሰሞኑን አንድ ሰርፕራይዝ አለህ፤ ለመሆኑ ፀሎት ታደርጋለህ ወይ? አለኝ፤ ምን ማለትህ ነው ?ከፀሎት ተለይቼ አላውቅም፤ከፈለክ ለአንተም ደርቤ እፀልይልሃለሁ፤ እኔም ሆንኩ ቤተሰቦቼ እግዚአብሔርን ከማመስገን የታቀብንብት ቀን የለም አልኩት፡፡ ከዛ ሸራተን ና ተብዬ ስደርስ አርቲስት ማህደር አሰፋ አለች፡፡ ምንድነው? ስል ‹ትዝ ይልሃል ያኔ የልጆች ጊዜ ፕሮግራም ላይ ስታሰራን ነበር› አለችኝ፤ አስታውሳለሁ እሷ ብቻ ሳትሆን ብዙ ልጆችን ወደ ኢትዮጵያ ቴሌቪዥን እየወሰድኩ የህፃናት ፕሮግራም እንዲሰሩ አደርግ ነበር፡፡ ማህደር እንደውም ፊልሟ ሁሉ አለ፤ በጣም ጎበዝ ነበረች፤ ከስድስት ወራት በፊት እንደውም እናቷን አግኝቻት ‹ማህደር ሁልጊዜ ነው የምታስታውስህ› ብላኛለች፤ ከዛ ‹ይህንንማ እንዴት እረሳለሁ አስታወሳለሁ› ስላት ቦርሳዋን ላጥ አድርጋ ከፍታ ‹ሼህ መሀመድ አላሙዲ ለእስከዛሬው ድካምህና ልፋትህ እንዲሆን በማለት ይህንቺን ቼክ ልከውልሃል› አለቺኝ፤

READ  Ethio-Djibouti Railway Set to Ease Transport

ቁም ነገር፡- ምን ተሰማህ በወቅቱ?
አስረስ፡- ምን ይሰማኛል፤ ያው ደስታ ነዋ፤ በህይወቴ ከአንድ ቁጥር ቀጥሎ ይህን ያህል ብዙ ዜሮ ተፅፎ አይቼ አላውቅም/ሳቅ/ ያው ተሳስቀን ተለያየን፤የታገሰ ሰው መቼም የእግዚአብሔርን ጥበብ ማየቱ አይቀርም፡፡

ቁም ነገር፡- ምስጋናህን ምን ብለህ ገለፅክላቸው ?
አስረስ፡- በፅሁፍ ፅፌ ይህንን ወረቀት ፊታቸው ቆመሽ አንብቢልኝ ብዬ ደብዳቤ ሰጠኋት፤ እንግዲህ ከዛ በኋላ አልተገናኘንም፡፡

ቁም ነገር ፡- ቼክህን እንደተቀበልክ መጀመሪያ ለማን ተናገርክ?
አስረስ፡- አንድ ኮንትራክተር ወንድሜ አለ፤ ዮሴፍ ወንድሙ የሚባል፤ ባለቤቱ ሎዛ ትባላለች፤ ገና እንደተጠራሁ ለእነርሱ ነበር የተናገርኩት፤ እንዴት ሊጠሩን ቻሉ ብዬ ሳመነታ ቆይቼ ነበር የሄድኩት ፤ እነርሱ ናቸው ያወቁት፤ ከዛ ቤት ገብቼ ቼኩን መጀመሪያ ኮፒ አደረኩት፤ ከዛ አሳድጌ በፍሬም ውስጥ አደረኩትና ለባለቤቴ ስደውል ጓደኛዋ ወደ ውጪ ሀገር ልትሄድ ስለነበር ልትሸኛት እዛ እሷ ጋር ናት፤ ደውዬ ሰርፕራይዝ አለ፤ ስላቸው ምንድነው? አሉኝ፤ አሁን አልናገርም ኑ አልኳቸው፤ ጓደኛዋ የዛን እለት ስለሆነ በረራዋ ንገረኝ እኔ ልሄድ ነው አለችኝ፤ በረራሽን የምቀይሪ ከሆነ ነው የምነግርሽ ስላት መቀየር አልቻለችም ገርኳቸው፡፡ ከዛ ለሌሎችም ጓደኞቼ እየደወልኩ ነገርኳቸው፡፡

ቁም ነገር፡- ብሩን ቆጥረህ ለመጨረስ ተቸግረህ ነበር ይባላል?
አስረስ፡- ከዳሸን ባንክ ነው የወሰድኩት፤ እነሱ ይጨነቁበት ብዬ አንድ ሌሊት ሙሉ ሲቆጥሩ ነው ያደሩት፡፡ ይህን ስነግረው ኮሜዲያን ደረጄ የመጀመሪያው ሚሊየነር ኮሜዲያን ሆነህልናል ብሎኛል፡፡ በነገራችን ላይ የሚያውቀኝ ሰው ሁሉ ራሱ የተሸለመ ያህል ነው ደስታው፤ መላ የኢትዮጵያ ህዝብ በእኔ ደስተኛ እንደሆነ ይሰማኛል፤

ቁም ነገር፡- ይህ ስጦታ በስራህ ላይ ምን ይጨምራል ከዚህ በኋላ ?
አስረስ፡- ያው እንደምታውቀው ከዚህ በፊትም አንተ ኢንተርቪው አድርገኸኛል፤ እኔ ደስተኛ የምሆነው ለህፃናት ከህፃናት ጋር ስራ ስሰራ ነው፡፡ እንደምታውቀው ኮሜዲያንም ነኝ፤ ግን የበለጠ ደስታ የሚሰጠኝ ከልጆች ጋር ስስራ በመሆኑ የያዝኳቸውና የጀመርኳቸው የተለያየ ስራዎች አሉኝ እነርሱን እሰራለሁ፡፡

READ  ብሪታኒያ ለየኛ ፕሮጀክት የምትሰጠውን ገንዘብ አቋረጠች

ቁም ነገር፡- መፅሐፍት ናቸው?
አስረስ፡- አዎ፤ አሁን እጄ ላይ ወደ ሰባት ያህል መፅሐፍት አሉ፤ ህትመት የሚጠብቁ፤

ቁም ነገር፡- የህፃናት ናቸው?
አስረስ፡-አንዱ ብቻ ነው የአዋቂ ልብ ወለድ፤ ሌሎቹ የህፃናት መፅሐፍት ናቸው፡፡ አንድ ጊዜ እንደውም ምን ሆነ መሰለህ? የሆነ ቦታ ቁጭ ብለን ደረጀ ኮሜዲያን የሆነ ብር አገኘና የልብ ወለድ መፅሐፍህን እኔ ላሳትምልህ አለኝ፤ ‹አይ መፅሀፍ ለማሳተም ልብህ ከፈቀደ የህፃናት መፅሐፍ ፅፌ ስዕል ለማሳያ ብር ቸግሮኛል፤ እሱን አስልልኝ› አልኩት፤ ይህን ስናወራ አብረውን አዩ/ሀይለስላሴ፤ሶስና ደርበው ገበየሁ ዘሩ የሚባሉ ሰዎች ነበሩ ፤ ምን ያህል ነው ስዕል ማሳያ ሲሉኝ ‹ለአንዱ አምስት ሺህ ብር ›አልኳቸው፤ እኔ አንዱን እኔ ደግሞ አንዱን እንችልሃለን አሉኝ፡፡ ለካ የስዕል ማሳያ ዋጋ እኔ የማውቀው ከአምስት ዓመት በፊት የነበረውን ነበር፤ ብሩ ሁሉንም ስዕል ለማሳያ ሳይበቃ ቀረ፤ አሁን ግን እየጨረስኩት ነው፡፡እንዲህ እንዲህ አይነት ሰዎች ሁሌም ከጎኔ ናቸው፡፡ በኑሮዬ ደስተኛ ነኝ፡፡ በቤተሰቤ በልጆቼ ደስተኛ ነኝ፡፡ እኔ እግዚአብሔር ከጎኔ እንደሆነ የሚሰማኝ በዓመት በዓል እንኳ በግ ፤ ጤፍ ከክፍለ ሀገር ጭነውልኝ የሚመጡ ሰዎችን አኔ አላውቃቸውም፤ ሁሌም ከጎኔ የማይለዩ በጣም ብዙ ሰዎች አሉ፡፡ እንደነ ሰለሞን ተክለማርያም የካሳንችስ ግሩፕ አይነት ወዳጆች አሉኝ፡፡

ቁም ነገር፡- እስካሁን ስንት የልጆች መፃህፍትን አሳትመሃል?
አስረስ፡- ስድስት በአማርኛ አንድ ደግሞ በስፖት ላይት ድርጅት አማካይነት አንድ የኦሮሚኛ መፅሐፍት ታትመዋል፡፡ አሁንም ይቀጥላል፡፡

ቁም ነገር፡- የድካሜን ዋጋ በስተመጨረሻ አገኘሁ ትላለህ?
አስረስ፡- እንደምታውቀው ሙሉ ጊዜዬን ለህፃናት ሰጥቼ ስሰራ ነው የኖርኩት፤ አባባ ተስፋዬ ጋር አብሬ መስራቴ ለዚህ ስሜት መፈጠር ትልቁን ድርሻ ይይዛል፡፡እንደምትመለከተው ፀጉሬ ወደ ኋላ እየገባ ነው፡፡ በዘራችን ራሰ በራ የለም፡፡ ይሄ የሆነው ቼሪን ስሰራ ነው ፀጉሬ የተመለጠው፡፡ ማንም ሰው ይህንን አያውቅም፡፡ በእኛ ጊዜ በብዙ ችግር ነበር የምንሰራው፡፡

READ  በአንድ ሕፃን ላይ በተፈጸመ የሕክምና ስህተት ሳቢያ ከ3.2 ሚሊዮን ብር በላይ ካሳ ተፈረደ

ቁም ነገር፡- ልደትህን በሸንኮራ ማክበርህን ሰምቻለሁ፡፡ እውነት ነው?
አስረስ፡- አዎ፤ ያው ስጦታው የመጣ ሰሞን ስለነበር ልደቴን ሚያዝያ 7 ሰብሰብ ብለን በሸንኮራና በሌሎችም ነገሮች አክብረነዋል፡፡ ሸንኮራ ያው ትንቧለልን ስሰራ የምታወቅበት ስለሆነ ነው ግር አይበልህ/ሳቅ/

ቁም ነገር፡- በመጨረሻስ?
አስረስ፡- በመጀመሪያ የማመሰግነው ልዑል እግዚአብሔርን ነው፡፡ ጥበቡን ያሳየኝ አምላክ ነው፡፡ ሙሉ ቤተሰቦቼን፤ ሼህ መሐመድ አሊ አላሙዲን ከነመላው ቤተሰባቸው ይባርካቸው፡፡ አርቲስት ማህደር አሰፋ፤ የሙያ ጓደኞቼን ደረጀ ሐይሌ፤ መልካሙ ደምሴ፤ መልካም ዘር ስነወርቅ፤ ማንን ጠርቼ ማንን ልተው? ሰይፉ ፋንታሁን፤ ጋሽ አያልነህ ሙላት ፤ ሮዛ ወርቁ እና ባለቤቷ አቶ ዮሴፍ ፤ሰለሞን ተክለማርያም የካሳንችሱ፤ ገብረመድህን ጥላሁን (ገሬ)፣ የታክሲ ሾፌሮች ገንዘብ የለኝም ስላቸው በነፃ ቤቴ ድረስ የሚያደርሱኝ፤ ወዘተ በጣም ብዙ ወዳጆች ናቸው ያሉኝ፤ የማንን ስም ጠርቼ የማንን ተልተው ? ልታጣላኝ ነው አይደል? ብቻ ለሁሉም እግዚአብሔር ይስጥልኝ እላለሁ፡፡

ቁም ነገር፡- አመሰግናለሁ፡፡ 

NO COMMENTS