የሊዝ አዋጅ ሊሻሻል ነው ተባለ

0
6326
መርካቶ አውቶብስ ተራ
Image: መርካቶ አውቶብስ ተራ by Wazema Radio

የማሻሻያ ረቂቅ ደንቡ

  • የግለሰብ ይዞታ ጋር ተቀላቅለው የሚገኙ ደቃቃ የቀበሌ ቤቶች ግለሰቦች እንዲያለሟቸው ይፈቅዳል፡፡
  • ልዩ አገራዊ ፋይዳ ይዘው ለሚቀርቡ የላቁ ባለሐብቶች መሬት ከሊዝ ደንብ ዉጭ በምደባ ይሰጣል፡፡
  • ነባር ይዞታዎችን ወደ ሊዝ ሥርዓት ለማስገባት ተጨማሪ 2 ዓመት ጊዜን ይፈቅዳል፡፡
  • በሕገወጥ ወረራ የተያዙ ቦታዎች በ2 ዓመት ዉስጥ ወደ ሊዝ ሥርዓት እንዲገቡ ያስገድዳል፡፡
  • በከተሞች ለማኑፋክቸሪንግ በተናጥል ቦታ የሚጠይቁ ባለሐብቶች እንዳይስተናገዱ ያግዳል፡፡
  • በከተሞች አንድ ግለሰብ ከአንድ በላይ የመኖርያ ቤት በሊዝ እንዳይጫረት ገደብ ይጥላል ተብሏል፡፡

ዋዜማ ራዲዮ- በ2004 ዓ.ም በብዙ ዉዝግቦች ታጅቦ ጸድቆ የነበረው የሊዝ አዋጅ 721/2004 በርካታ ክፍተቶች እንዳሉበት በመገለጹ ከአምስት ዓመት በኋላ በቅርቡ ሊሻሻል እንደሚችል የዋዜማ ምንጮች ጠቆሙ፡፡

በአዲስ አበባ መስተዳደር የከተማ መሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ በከፍተኛ ኃላፊነት የሚሠሩና በጠቅላይ ሚኒስትሩ ትዕዛዝ በተቋቋመው የሊዝ ኦዲት ኮሚቴ ዉስጥ በአባልነት የሠሩ ባለሞያ ለዋዜማ እንደተናገሩት አዋጁን ማሻሻል ያስፈለገው ለትርጉም ክፍት የኾኑ አንቀጾችን በመያዙ፣ አሁን ካለው ፈጣን የልማት ጥያቄ ጋር ባለመጣጣሙና ለአገር ከፍ ያለ ፋይዳ ያላቸው አልሚዎችን ለማስተናገድ አዋጁ ማነቆ ኾኖ በመቆየቱ ነው፡፡

ኃላፊው ጨምረው እንዳብራሩት ከሚቀጥለው ሳምንት መጨረሻ ጀምሮ ከክልሎችና ከከተማ አስተዳደሮች እንዲሁም ፈጻሚዎች ጋር በአዋጁ ማሻሻያ ላይ ሰፊ የዉይይትና የምክክር መድረክ ይከፈታል፡፡ በዉይይቱም በአገር ደረጃ መሬት ልማት ላይ የሚሠሩ ከፍተኛና መካከለኛ ኃላፊዎች ይገኛሉ፡፡ ይህም የሚደረገው አዋጁን ሲያስፈጽሙ በነበሩ አመራሮች ዘንድ ተመሳሳይ ግንዛቤን ለመፍጠርና የአዋጁን ክፍተቶች በዉይይት ለማዳበር ታስቦ ነው ብለዋል፡፡

ከተሞች ከ2004 ቀደም ባሉት ጊዜያት መሬት የሚያስተላልፉበት ወጥ አሠራር አለመኖሩ መሬት ማግኘት በግለሰቦች በጎ ፍቃድ ላይ የተመሠረተ እንዲሆን አድርጎት ቆይቷል፡፡ ከአዋጁ በኋላ ሁሉም ዓይነት የመሬት ስሪቶች በሂደት ወደ ሊዝ እንዲገቡ በማድረግና የመሬት አቅርቦትን በግልጽ ጨረታ ለአልሚዎች ለማስተላለፍ ተሞክሯል፡፡ በአንጻሩ የሊዝ አዋጁ ሁነኛ ግብና መነሻ በአነስተኛ ዋጋ ዜጎች ቦታ እንዲያገኙ ማድረግን ያለመ ነው ቢባልም በዉጤቱ መሬት የጥቂት ባለፀጎች የግል ንብረት ኾኖ እንዲቆይ አድርጓል ይላሉ ተቺዎች፡፡

READ  የኢትዮ ሶማሊላንድ መሪዎች በሁለትዮሽ ግንኙነት ዙሪያ መከሩ

የሊዝ አዋጁን ተከትሎ ባለፉት አምስት ዓመታት ከተሞችና ክልሎች የራሳቸውን የማስፈጸሚያ መመሪያና በማውጣት ሊተገብሩት ሲሞክሩ ቆይተዋል ያሉት የኦዲት ኮሚቴው አባል ኾኖም ከተሞች አዋጁን ለማስፈጸም የሄዱበት መንገድ ለዉዝግብና ለአሠራር ክፍተት የተመቸ ነበር ብለዋል፡፡

አዋጅ 721/2004 በመባል የሚጠራው የሊዝ አዋጅ አፈጻጸም የእስከዛሬ ሂደት መንግሥት በከፍተኛ ባለሞያዎች ኦዲት እንዲደረግ ካለፈው ዓመት ጀምሮ ኮሚቴ ተዋቅሮ በመጠናት ሂደት ላይ ነበር፡፡ ኮሚቴው ባካሄደው ተከታታይ የሊዝ ኦዲትና ምዘና በአሠራር ላይ ከፍተኛ ክፍተት ተገኝቶበታል፡፡ አንዳንድ ከተሞች አዋጁን ገሸሽ አድርገው በራሳቸው መንገድ መሬት ሲያድሉ ነበር ያለው የኮሚቴው ሪፖርት ሌሎች ክልሎች ደግሞ አዋጁን በሚመቻው መንገድ ሲተረጉሙት እንደነበር ተደርሶበታል ብሏል፡፡

እንደ ምሳሌም ለአገር ከፍተኛ ፋይዳ ያላቸው ፕሮጀክቶች በሊዝ ደንብ ብቻ ለማስተናገድ ምቹ ሳይሆን በሚቀርበት ሁኔታ የክልል ካቢኔዎች፣ የከተማ ከንቲባዎችና የጽሕፈት ቤት ኃላፊዎች አዋጁን በሚጻረር ሁኔታ ለፈቀዱት ባለሐብት ሰፋፊ መሬቶችን ሲሰጡ ነበር ተብሏል፡፡ ይህም “ለልማት ልዩ ፋይዳ ያላቸው ፕሮጀክቶች” ናቸው በሚል ሽፋን ሲፈጸም የቆየ ተግባር ነው፡፡

የአዋጁ ሌላው ክፍተት ኾኖ የተመለከተው ከሊዝ የወለድ ስሌት ጋር የተያያዘ እንደነበርም ተመልክቷል፡፡ ሁሉም ክልሎች በሊዝ የተላለፈ መሬት የንግድ ባንክ የወለድ ተመንን ተከትለው በየዓመቱ ስሌቱን የሚሠሩ ሲሆን የአዲስ አበባ መስተዳደር ግን ከሌሎች ከተሞች በተለየ አልሚዎችን ድርብ ወለድ (compound Interest) እንዲከፍሉ በማስገደድ ባለሐብቱ ላይ ተገቢ ያልሆነ እዳን በመቆለል ከልማት በኋላ ሊገኝ የሚችልን የግብርና የሥራ ገቢን በወለድ መልክ በአቋራጭ ለመሰብሰብ ሞክሯል ተብሏል በሪፖርቱ፡፡ ይህም አልሚዎች በግንባታ ፍጻሜ ላይ እንዳያተኩሩ አድርጓል፡፡

READ  በታንዛኒያ እስር ቤት የነበሩ 87 ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ወደ ሃገራቸው ተመለሱ

ወለድ ባልተኖረበት የሊዝ ዓመትና ባልተሠራበት የሊዝ ዘመን ወደፊት ተኪዶ ሊሰላ አይችልም ያሉት የኮሚቴው አባል እስከዛሬ በመስተዳደሩ ይሠራበት የነበረው አሠራር ሕግን ያልተከተለ እንደነበር በመርህ ደረጃ መተማመን ላይ ተደርሷል ብለዋል፡፡ የሚሻሻለው የሊዝ አዋጅ ይህን ክፍተት በመሸፈን ሁሉም ክልሎች ወጥነት ባለው መንገድ ዓመታዊ የሊዝ ገቢን እንዲሰበስቡ የሚያስችል አሠራርን ይዘረጋል ሲሉ አብራርተዋል፡፡

የሊዝ አዋጁ አመጣቸው ከሚባሉ በጎ ዉጤቶች መካከል የመሬት ብክነትን መከላከል፣ የመሬት ወረራ እንዲቀንስ ማድረግ፣ አልሚዎች በጊዜ ገደቡ ምክንያት ልማታቸውን በግዴታ እንዲያጠናቅቁ አስገዳጅ ሁኔታዎችን መፍጠር፣ እንዲሁም በዋናነት መሬት በግለሰቦች መልካም ፍቃድ የሚሰጥበትና የሚከለከልበትን እድል መቀነስ ዋናዎቹ ናቸው ተብሎ በኮሚቴው መገምገሙን የኦዲት ኮሚቴው አባል ያስረዳሉ፡፡

በተጨማሪም በሊዝ የሚተላለፉ መሬቶች ከማንኛውም የይገባኛል ጥያቄ ነጻ መሆናቸው፣ ከሞላ ጎደል የከተማ ፕላን ተከትለው መዘጋጀታቸው፣ አንጻራዊ የመሠረተ ልማት ምቹነት ያላቸው ስፍራዎች ላይ መወሰናቸው፣ እንዲሁም ልዩ የሽንሻኖ ኮድ ሳይት ፕላን የተዘጋጀላቸው ስለነበሩ ለአሠራር አመቺ ሆነው መገኘታቸው ተወስቷል፡፡

ይህ ማለት ግን ሁሉም ከተሞች በዚህ ሁኔታ የተዘጋጁ መሬቶችን ሲያቀርቡ ነበር ማለት እንዳልሆነ የኦዲት ኮሚቴው አባል ያስረዳሉ፡፡ ለአብነትም ቦታዎች በሊዝ ለባለሀብቶች ከተላለፉ በኋላ የመንገድና የአጎራባች ይገባኛል ጥያቄ በብዙ ከተሞች ላይ ይነሳ እንደነበር አልሸሸጉም፡፡

በሊዝ የሚተላለፍ መሬት ሲካሄድ የተጫራቾች ቁጥር በተመለከተ በድሬዳዋና በአዲስ አበባ ምክንያቱ በማይታወቅ የአሠራር መመሪያ አንድ ተጫራች በአንድ ዙር ከአንድ በላይ የጨረታ ሰነድ ገዝቶ መጫረት እንዳይችል የሚያግድ አሠራር እንደነበረም ኮሚቴው በኦዲት ሪፖርቱ እንደደረሰበት ተገልጧል፡፡ ይህ አሠራር በሌሎች ከተሞች የማይታወቅ ነው፡፡ ይልቁንም ግለሰቦች ያሻቸውን የጨረታ ሰነድ ገዝተው ባሻቸው መጠን መወዳደር የሚችሉበት እድል አላቸው፡፡

READ  Ethiopian Government Set to Scale up Support to the Mining Sector

በሚሻሻለው የሊዝ አዋጅ ለጨረታ የቀረበው ቦታ ለመኖርያ ቤት ከኾነ ብቻ አንድ ተጫራች ከአንድ ቦታ በላይ እንዳይጫረት፣ የመኖርያ ቤት አንድ ጊዜ በሊዝ ያሸነፉ ግለሰቦች ከዚያ በኋላ ሌላ የመኖርያ ቤት ጨረታ ላይ እንዳይሳተፉ እንደሚደረግ ሐሳብ መቅረቡን የሊዝ ኦዲት ኮሚቴ አባሉ አስረድተዋል፡፡

ይህ እንዲሆን የተፈለገው መሬት በሊዝ በመግዛትና አትርፎ በመሸጥ ሥራ ላይ የተሠማሩ የመሬት ደላሎችን ለማግለልና በከተሞች ፍትሐዊ የመሬት ክፍፍል እንዲኖር ለማስቻል ነው ተብሏል፡፡ከ13 እስከ 18 የሚኾኑ ቁልፍ ቦታዎችን በሊዝ አሸንፈው የያዙ ግለሰቦች በኦዲት ሂደት እንደተገኙ የጠቆሙት የኮሚቴ አባሉ ይህ ዉድ ሀብት የኾነን የሕዝብና የመንግሥት መሬት በአቋራጭ የጥቂቶች እየኾነ እንደመጣ ማሳያ ተደርጎ ተወስዷል ተብሏል፡፡ ኾኖም ለቅይጥና ለቢዝነስ የሚወጡ ቦታዎች ባለሐብቶች እንደፈቃዳቸው መጫረት እንዲችሉ እንደሚደረግ አልሸሸጉም፡፡ More Here

NO COMMENTS