የዘገየውና ያልተሟላው ፍትህ

0
1074
የዘገየውና ያልተሟላው ፍትህ
ለሕዝብ ጥቅም ሲባል ከይዞታው የሚለቅ ሰው በቅድሚያ ተመጣጣኝ ካሳ የማግኘት ሕገ መንግሥታዊ መብት አለው፡፡

 

ለሕዝብ ጥቅም ሲባል ከይዞታው የሚለቅ ሰው በቅድሚያ ተመጣጣኝ ካሳ የማግኘት ሕገ መንግሥታዊ መብት አለው፡፡ በህገ መንግሥቱ አንቀጽ 40(8) «የግል ንብረት ባለቤትነት መብት እንደተጠበቀ ሆኖ፣ መንግሥት ለህዝብ ጥቅም አስፈላጊ ሆኖ ሲያገኘው ተመጣጣኝ ካሳ በቅድሚያ በመክፈል የግል ንብረትን ለመውሰድ ይችላል» ይላል። ይህንን መርህ ተግባራዊ ለማድረግ በወጣው አዋጅ ቁጥር 455/97 በአንቀጽ 7 ላይ የገጠር መሬት ካሳ አከፋፈል ቀመር ተደንግጓል፡፡ ይህ ድንጋጌ ህገ መንግሥቱን መሰረት በማድረግ የወጣ በመሆኑ ሁሉም መንግሥታዊ ተቋማት ሊተገብሩት ይገደዳሉ። ሆኖም ከህገ መንግሥታዊ መርህና ከአዋጁ ድንጋጌ ባፈነገጠ መልኩ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣንን ለአሥር ዓመታት የካሳ ክፍያን እንዳልፈጸመ አዲስ ዘመን አረጋግጧል።

በኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግሥት ባሌ ዞን የጋሰራ ወረዳ ባሎ ሀበቤ ቀበሌ አርሶ ዓደሮች ከአሥር ዓመት በፊት በነበራቸው መሬት ላይ ቡና፥ ጫትና የተለያዩ ፍራፍሬዎችን እያመረቱ ለገበያ ያቀርቡ ነበር፡፡ በዚህም ቤተሰባቸውን ጠንቅቀው ማስተዳደር ከመቻላቸውም በላይ በየዓመቱ አንድ አርሶ ዓደር እስከ 200ሺ ብር በማግኘት ለመንግሥትም ዳጎስ ያለ ግብር ሲከፍሉ ኖረዋል።ይህ ሂደት ግን ህዝብን ተጠቃሚ ለማድረግ በኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን የእንደንቶ-ጋሰራ መንገድ ሥራ ፕሮጀከት ምክንያት መቀጠል አልቻለም። ነገሩ ወዲህ ነው።

በመንገድ ስራው ምክንያት በመስኖ ስራ ህይወታቸውን ይመሩ የነበሩ 250 አርሶ ዓደሮች /ባለስልጣኑ 55 ናቸው ይላል/ ያለ ካሳ ከማሳቸው ተፈናቅለው ለችግር ተዳርገዋል። ይህ ለህዝብ ልማት እየሰራሁ ነው ከሚል ተቋም የማይጠበቅ ነው። 250ውም ቀርቶ ባለስልጣኑ በራሱ ላመነባቸው 55 አርሶ ዓደሮች እንኳን የአሥር ዓመት ካሳ መስጠት ሲገባው በወቅቱ/ፕርጀክቱ ሲጀመር 1999ዓ.ም/ የአንድ ዓመት ካሳ ብቻ መስጠቱም ተገቢ ያልሆነና የአርሶ ዓደሮቹ ህገ መንግሥታዊ መብት የጣሰ መሆኑ ሊታወቅ ይገባል። ይህ ጥሰት የህግ ተጠያቂነት የሚያስከትል ቢሆንም እስካሁን በባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ላይ የተወሰደ እርምጃ የለም። ለምን? ይህ ተግባር በየትኛውም መስፈርት ትክክል ስላልሆነ አስቸኳይ የማስተካከያ እርምጃ መወሰድ አለበት።

READ  38,000 Houses to be handed over to Owners during Ethiopian New Year

አቤቱታ ያላቸው አርሶ ዓደሮች በወኪሎቻቸው አማካይነት ወረዳ፣ ዞን፣ የኦሮሚያ ፕሬዚዳንት ፅህፈት ቤት፣ የህዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም እና የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ድረስ አቤቱታቸውን አቅርበዋል። በተለይም የዴሞክራሲ ተቋም የሆነው የህዝብ ዕንባ ጠባቂ የአርሶ ዓደሮቹ አቤቱታን ትክክለኛነት አረጋግጦ ለ250ውም አርሶ ዓደሮች ካሳ ይከፈላቸው የሚል ውሳኔ አሳልፎ እያለ ባለስልጣኑ በእምቢተኝነቱ ፀንቷል። ለመሆኑ የመንገዶች ባለስልጣን መስሪያቤት ከህግ በላይ ነውን? አይደለም፤ ሊሆንም አይችልም። ስለሆነም የአርሶ ዓደሮቹ የ10 ዓመታት አቤቱታ በአስቸኳይ መልስ ሊሰጠው ይገባል።

አርሶ ዓደሮች የልማታዊ ዴሞክራሲያዊ ስርዓቱ ማህበራዊ መሰረት መሆናቸው ባለስልጣኑ የዘነጋው ይመስላል። ለህዝብ ተጠቃሚነት የሚተገበር ልማት ህዝብን አስኮርፎ መሆን የለበትም። ይህ ፀረ ዴሞክራሲያዊነት ነው። ከመንግሥት ፍላጎትና ዓላማ ውጭም ነው። ስለሆነም ባለስልጣኑ ያለበቂ ምክንያት ካሳው ይገባቸዋል ላላቸው 55 አርሶ ዓደሮች (ዘግይቶም ቢሆን ለአርሶ ዓደሮቹ የዘጠኝ ዓመት ሂሳብ በኮሜርሻል ኖሚኒስ በኩል በ26/3/09 ክፍያ መላኩን ገልጿል) ጨምሮ የ250 አርሶ ዓደሮችን ህገ መንግሥታዊ መብት ባለማክበሩ መጠየቅ አለበት። ይህንን የምንለው ከምንም ተነስተን አይደለም፤ ዕንባ ጠባቂ ተቋም በባለሙያ አስጠንቶ ይገባቸዋል በሚል ካሳለፈው ውሳኔ ተነስተን እንጂ። ህገ መንግሥቱም ካሳ ቅድሚያ ይሰጣል ይላል። ባለስልጣኑ ግን ለ55 አርሶ ዓደሮችም ቢሆን የዘጠኝ ዓመት ካሳ ልኬአለሁ የሚለው ገና ዘንድሮ መሆኑ ህገ መንግሥቱን ስለመጣሱ ማስረጃ ነው። ስለሆነም ለሌሎች ተቋማትም ማስተማሪያ ይሆን ዘንድ ህጋዊ እርምጃ ሊወሰድበት ይገባል።

እንደ ዕንባ ጠባቂ ተቋም፣ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመሳሰሉት ተቋማት ከህገ መንግሥቱ መርህ ባፈነገጠ መልኩ የስርዓቱ ማህበራዊ መሰረት የሆኑትን አርሶ ዓደሮችን ካሳ ባዘገየው መንግሥታዊ ተቋም ላይ ከደብዳቤ ልውውጥ የዘለለ ጠንከር ያለ እርምጃ የሚወሰድበት አግባብ መፍጠር አለባቸው። የተሰጣቸውን ህዝባዊ ኃላፊነት መውጣት የሚችሉትም ህገ መንግሥቱን በማስከበርና አስተዳደራዊ በደል በሚፈፅሙ ተቋማትና ግለሰቦች ላይ አስተማሪና የማያዳግም እርምጃ በመውሰድም ጭምር መሆን አለበት። ይህ ካልሆነ ግን ደብዳቤ መፃፃፍ ብቻውን ፈጣን ምላሽ የማያስገኝ መሆኑን የጋሰራ ወረዳ አርሶ ዓደሮች የአሥር ዓመት ሂደት ማሳያ ነው።

READ  የዶክተሮች ዓመት-ከምሁራን እፍ ያለው አዲሱ የፓለቲካችን ፍቅር

አሁንም ቢሆን ለ55 አርሶ ዓደሮች የዘጠኝ ዓመት ሂሳብ ተሰልቶ ካሳ ተልኮላቸዋል ተብሏል። ይህ የዘገየ ፍትህ ነው። የቀሪዎቹ 195 አርሶ ዓደሮች ጥያቄም ገና መፍትሄ አላገኘም። በዚህም ምክንያት የተሰጠውን ፍትህ ያልተሟላ ያደርገዋል። ስለሆነም ፍትህ ያዘገየ እና ያልተሟላ ፍትህ የሰጠው አካል ተጠያቂ መሆን አለበት። የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ የእንባ ጠባቂ ተቋምና የኦሮሚያ ፕሬዚዳንት ፅህፈት ቤት ስራቸውን በተገቢው መንገድ በመሥራት ያልተሟላውን ፍትህ የተሟላ ለማድረግ መሥራት አለባቸው።ethpress.gov.et/addiszemen

NO COMMENTS