አቡነ ዮሴፍ የኢትዮጵያ ህዋ ሳይንስ መጻኢ መቼት

0
1449
አቡነ ዮሴፍ የኢትዮጵያ ህዋ ሳይንስ መጻኢ መቼት
(ተጓዡ ጋዜጠኛ ሄኖክ ስዩም በኢትዮጵያ ሦስተኛው ተራራ ላይ ወጥቶ ከተመለከታቸው ነገሮች አንዱ የስፔስ ሳይንስ ጥናት ጅማሮን ነው፡፡ ይህ ስፍራ መጻኢው የኢትዮጵያ ህዋ ሳይንስ መጻኢ መቼት ነው ሲል ሦስት ዩኒቨርስቲዎች በጥምረት የሚያደርጉትን የተራራ ላይ ሳይንሳዊ ትግል እንዲህ ያስጎበኘናል፡፡

ተጓዡ ጋዜጠኛ ሄኖክ ስዩም በኢትዮጵያ ሦስተኛው ተራራ ላይ ወጥቶ ከተመለከታቸው ነገሮች አንዱ የስፔስ ሳይንስ ጥናት ጅማሮን ነው፡፡ ይህ ስፍራ መጻኢው የኢትዮጵያ ህዋ ሳይንስ መጻኢ መቼት ነው ሲል ሦስት ዩኒቨርስቲዎች በጥምረት የሚያደርጉትን የተራራ ላይ ሳይንሳዊ ትግል እንዲህ ያስጎበኘናል፡፡ (ሔኖክ ስዮም በድሬትዩብ)

ይሄ ማማ የኢትዮጵያ ሶስተኛው ተራራ ነው፡፡ አቡነ ዮሴፍ ይባላል፡፡ ሪም ገደል የተራራው የመጨረሻ ጫፍ ነው፡፡ በረዶ እንደ ኩታ ካጣፋው ተራራ ስር ደግሞ የመቐለ፣ የባህር ዳር እና የወልዲያ ዩኒቨርሲቲዎች ለህዋ ሳይንስ ጥናት ብለው በቀለሱት ጎጆ ከውርጭ እየታገሉ ሰማያትን ይፈትሻሉ፡፡

ህዋ ሳይንስ ሞኝነት ለሚመስለው የሀገሬ ሰው መልእክቱን ባደርስ ብለው ይነግሩኝ ጀምረዋል፡፡ በእርግጥ ግብርናውም፣ የአይሲቲ ግንኙነቱም፣ የወታደራዊ እንቅስቃሴውም የሲቪል አቪዬሽን ስራውም ከሳተላይት ጋር የተገናኘ ነው፡፡ እዚህ ግዙፉን ቴሌስኮፕ ወድረው ከሪም ገደል በታች ሽቅብ ወደ ሰማይ ምሽቱን አፍጠው የሚያደሩት ባለሙያዎች የቦታውን ለዚህ ዓላማ መስማማት አለመስማማት ለመለየት ጥናት ላይ ናቸው፡፡

መልካቸው በውርጭ የተቀየረው ተመራማሪዎች አንድ ቀን አቡነ ዮሴፍ የህዋ ሳይንስ የምርምር ማዕከል ሆኖ ስሙ እንደሚገን ተስፋ ያደርጋሉ፡፡ ሌት ተቀን ያንን ስኬት ከማምጣት እየሰሩ ነው፡፡ ከፍተኛው የአቡነ ዮሴፍ ማማ ቁልቁል የተከዜ ሸለቆ የሚታይበትን ያክል አሁን ደግሞ እንዲህ በረቀቀ ዘዴ በሳይንሳዊ መነጥር ሰማይ የፈሰሱ ከዋክብትን ለማየት ምቹ እንደሆነ እና እንዳልሆነ የሚደረገው ጥናት ቀጥሏል፡፡

4284 ሜትር ከፍታ ካለው ተራራ ስር በሳር ጎጆ አርፈው ምሽቱን የሚመለከቱት ቴሌስኮፕ ከከዋክብት የሚያነጋግራቸው የሦስት ዩኒቨርሲቲ አጥኚዎች ውጤት እየተጠበቀ ነው፡፡ የጥናቱ ግኝት አቡነ ዮሴፍ ለከዋክብት ምልከታ ጥሩ ቦታ ሆኖ ከተገኘ የኢትዮጵያ ህዋ ሳይንስ ምርምር ቀጠና ይሆናል፡፡ እዚህ ብርቅዬው ቀይ ቀበሮ ከሚኖርበት፣ ጭላዳ እና ሰው በቃል ኪዳን ከተስማሙበት፣ ከዋግ እስከ ቆቦ፣ ከስሜን ጫፍ እስከ ራያ ምድር ቁልቁል ከሚታይበት አስደናቂ የተፈጥሮ መስህብ ሌላ አዲስ የቱሪዝም ምርት ሊፈጠር አፋፍ ላይ ነው፡፡

READ  በጎንደር ከተማ አመፅና ሁከት አስነስታለች የተባለች ግለሰብ የሽብር ወንጀል ክስ ተመሠረተባት

ፊታቸውን ውርጭ አመድ ያደረጋቸው ተመራማሪዎች የምርምር ውጤት እንደ አሰቡት ከሰመረ አቡነ ዮሴፍ መምጣት ማለት በረዶን ተንሸራቶ፣ በጅብራው ተመስጦ፣ በቀይ ቀበሮው ተአምር ብሎ መመለስ ብቻ ሳይሆን ወደ ሰማየ ሰማያት በጥበብ ተጉዞ የከዋክብትን ድንቅ ስነ ተፈጥሮ ለመመልከት የሚችሉበት የምርምር ቱሪዝም መዳረሻ ሆነ ማለት ነው፡፡

እዚህ ሆኜ አሸተን ማርያምን እያየሁ ነው፡፡ ደግሞ ወደ እሷ አብረን እንጓዛለን፡፡ አራቱ ነገሥታት በጸለዮበት ዋሻ መገኛ አድርገን ወደ አርሴማ እንጓዛለን፡፡ አስደናቂውን የዐለት ጥበብ ፍለጋ፡፡ DireTubeNews/diretube

NO COMMENTS