ካስትሮ እኮ የኛ ነው፤ ከማንዴላም ይቀርበን ነበር

0
1538
የኩባ ወታደሮች ለኢትዮጵያ ሉዓላዊነት
ኩባ ለኢትዮጵያ እስከ ሞት ተላልፎ የተሰጠ ፍቅር ያለው ህዝብ ሀገር ናት፡፡ ይሄ ህዝብ የሚወደው መሪ ሞት ከኩባውያን እኩል የኢትዮጵያውያን ሀዘን በሆነ፤ እንዴት ካስትሮ የእኛ ሆኖ ከእኛ ልብ ወጣ፡፡

ካስትሮ እኮ የኛ ነው፤ ከማንዴላም ይቀርበን ነበር፡፡ (ከስናፍቅሽ አዲስ)
ዓለም አሁን ሌላ ጉዳይ የለውም፡፡ የሚያወራው ስለ ታላቁ አብዮተኛ በጉልበት ሳይሆን በፍቅር ህዝብን አንበርክከው ስለኖሩት ፊደል ነው፡፡ ፊደል ካስትሮ ሞተ የሚለው መርዶ ለኩባውያን ብቻ ሳይሆን ለእኛ ለኢትዮጵያውያንም መሪር ነው፡፡ እኒህ ሰው ብዬ አልጽፍም፡፡ ካስትሮን ማራቁ ደስ አይልም፡፡ ካስትሮ ይሄ ሰውዬ የሚባል ነው፡፡ እንደ ኩባውያን ሁሉ ለኢትዮጵያውያን የቀረበ ወንድም፤ እንደ ሃቫና ሁሉ አዲስ አበባ ልታለቅስለት የሚገባ አብዮተኛ፡፡

ማንዴላ ሲሞት ጥልቅ ሀዘን ላይ መሆናችንን ዓለም እንዲያውቅልን ጥረን ነበር፡፡ ማንዴላ የነጻነት ታጋይ የጥቁር ህዝቦች አብነት ነበር፡፡ ማንዴላ ያሰበውን እንዲያሳካ ኢትዮጵያ ከጎኑ ቆማለች፡፡ አይዞህ ብላለች፣ ለዓላማው ልቧን ሰጥታለች፡፡ ያም ሆኖ ግን ደቡብ አፍሪካውያን የኢትዮጵያውያን ውለታ ያለባቸው ህዝቦች ናቸው እንጂ ኢትዮጵያ የደቡብ አፍሪካን ውለታ ቀርጥፋ የበላች አይደለችም፡፡

unnamed-8የኩባ ግን ይለያል፡፡ ኩባ የሚል ስም ያላቸው ኢትዮጵያውያን ዛሬም መታወቂያቸው ላይ ያንን ዘመን እየመሰከረ የሚኖር የእውነት አሻራ ታትሟል፡፡ ወንድም ሀገር ብለን ርቀቱ ሳይገድበን የተወዳጀንው የኩባ ህዝብ አሳፍሮን አያውቅም፡፡ ኢጣሊያ ኢትዮጵያን በወረረች ጊዜ ዓለም ለኢጣሊያ ሲወግን አንድ ኩባዊ ለኢትዮጵያ ካልተዋጋሁ ብሎ ከአሜሪካ መጣ፣ እንግሊዛዊ ዜግነት ያለው ይህ ኮለኔል ከራስ ሙሉጌታ ጦር ጋር አበሳውን ያየ የቀይ አንበሳ ደራሲ ነበር፡፡

በሱማሊያ ወረራ የዚያድ ባሬን ገደብ የለሽ ምኞት ልናከሽፍ ሆ ስንል ድምጻችን ውስጥ የኩባ ህዝብ ነበር፡፡ የኩባ ወታደሮች ለኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ተሰውተዋል፡፡ የኩባ ወዳጅነት ወረቀት ላይ ብቻ አይደለም፤ የኩባ አጋርነት ብር በባንክ መላክም አይደለም፡፡ ኩባ ለኢትዮጵያ እስከ ሞት ተላልፎ የተሰጠ ፍቅር ያለው ህዝብ ሀገር ናት፡፡

READ  አሜሪካ ኩባንያ ከመከላከያ ኮንስትራክሽን ድርጅቶች ጋር ጥምረት ፈጠረ

ይሄ ህዝብ የሚወደው መሪ ሞት ከኩባውያን እኩል የኢትዮጵያውያን ሀዘን በሆነ፤እንዴት ካስትሮ የእኛ ሆኖ ከእኛ ልብ ወጣ፡፡ የወዳጅ ሀገር መሪ ብቻ ሳይሆን ወዳጅ እና የአንድ ዜጋን ያክል ለኢትዮጵያ የሚጠነቀቅ አብዮተኛ ነበር እኮ፡፡ የያኔዎቹ ብርቱ የግብርና ባለሙያዎችን ማን ቀርጾ የሀገራቸው ሰው አደረጋቸው፡፡ እነኛን ጎበዝ ሀኪሞችስ ያስተማረው ማን ነበር፡፡

ፊደል መቼም ከኩባውያን ልብ የማይጠፋ የመሪና የተመሪ ፍቅር መገለጫ ነው፡፡ ዛሬ የለም፡፡ ኩባውያን የምንወደውን መሪ አጣን ብለው ሀዘን ተቀምጠዋል፡፡ ዓለም ሀዘኑን ሀዜን አድርጌዋለሁ እያለ ነው፡፡ ኢትዮጵያስ? የኢትዮ ኩባ ወዳጅነት የሚል አደባባይ ያላት ሀገር እንዴት ለኩባ እና ለአብዮተኛ መሪዋ ጀርባዋን ሰጥታ ከኖረችው አሜሪካ ዘግይታ ካስትሮን ለመዘከር፣ ህዝቧ ሀዘኑን እንዲገልጽ እድል መስጠት አቃታት?

ፊደል ካስትሮ ለኢትዮጵያአሁንም ግን አልረፈደም፡፡ ካስትሮ ሁሌ በኢትዮጵያውያን ልብ እንደ ኩባውያን ሊኖር የሚገባው ሰው እንደሆነ ጠልቀን የምንረዳበት ጊዜ ሊመጣ ይችላል፡፡ የተሰወረውን ትተው የካስትሮን የሲጃራ አጫጫስ የሚስብኩ ሚዲያዎቻችን ሚዲያ ሲሆኑ የወዳጅ ሀገር መሪው ወዳጃችን እና አጋራችን ካስትሮን የሚረዳ አዲስ ትውልድ ይመጣል፡፡ ያኔ ከስልጣናቸው ሉዓላዊነት ይልቅ ለኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ዋጋ የከፈሉ በሚታወሱበት ወርቃማው ዘመን አብሮ ስሙ ይነሳል፡፡

እኔ ግን አዲስ አበቤዎችን እላለሁ፡፡ እኛ እንደ ሀቫና ሰዎች ካስትሮን ለመዘከር በተዘጋጀው ሥነ-ሥርዓት ላይ ታድመን የወዳጅ ሀገርን ሀዘን ልንጋራ ይገባል፡፡

DireTube News

NO COMMENTS