በአዲስ አበባና አካባቢዋ ከፍተኛ የኬሚካል ከምችት መኖሩ በጥናት ተረጋግጧል

0
1395
የኬሚካል ከምችት
Image: ዋና ዳይሬክተር አቶ ይገዙ ዳባ

በአዲስ አበባና አካባቢዋ የአገልግሎት ጊዜያቸው ያለፈባቸው ኬሚካሎች ከፍተኛ ክምችት መኖሩን የመንግስት ግዥና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት ባካሄደው ጥናት አረጋገጠ።

ጥናቱ የተካሄደው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአገሪቱ የሚገኙ ያገለገሉ ኬሚካሎችን አያያዝና አወጋገድ፣ ባለቤት የሌላቸው መሆኑንና ክምችቱን እንዲያጠና ለመንግስት ግዥና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት በተሰጠው ትዕዛዝ መሰረት ነው።

ድርጅቱም በአዲስ አበባና አካባቢዋ የፌዴራል መስሪያ ቤቶችና የልማት ድርጅቶች ላይ ያካሄደውን ጥናት ውጤት ይፋ አድርጓል።

አገልግሎቱ ሶስት ቡድኖችን የያዘ ኮሚቴ በማዋቀር የዳሰሳ ጥናቱን ያካሄደ ሲሆን በጥናቱ ከተካተቱት 166 መስሪያ ቤቶች 21ዱ ከፍተኛ የኬሚካል ክምችት ተገኝቶባቸዋል።

ኬሚካሎቹ የተለያየ ይዘትና ባህሪ ያላቸው በመሆናቸው በአንድ መለኪያ ለመግለፅ የሚያስቸግሩ ቢሆኑም ከ1 ሺህ 700 ኪሎ ግራም በላይ ጠጣር፣ ከ800 በርሜል በላይ የተለያዩ ኬሚካሎችና ሌሎች ጥንቃቄ በጎደለው መልኩ በመጋዘን ውስጥ መኖራቸው ተረጋግጧል።

የአገልግሎቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ይገዙ ዳባ ለኢዜአ እንዳስታወቁት ኬሚካሎቹ በአይነት ከ25 በላይ ቢሆኑም መጠናቸው እጅግ ከፍተኛና በተገቢው መንገድ ያልተያዙ በመሆናቸው ፈጣን መፍትሄ ካልተሰጣቸው ጉዳታቸው የከፋ ሊሆን ይችላል።

“ጥናቱ በዋናነት ምን ያህል ያገለገሉ ኬሚካሎች እንደሚገኙ ማወቅ ላይ ያተኮረ ነው” ያሉት ዳይሬክተሩ ኮሚቴው ባካሄደው ጥናት መሰረት ለሚመለከተው አካል የውሳኔ ሃሳብ ለማቅረብ ዝግጅት ማጠናቀቁን ገልጸዋል።

የውሳኔ ሃሳቡ ከቀረበ በኋላ ያገለገሉ ኬሚካሎችን አወጋገድና አያያዝ በተመለከተ ኃላፊነት የሚሰጠው አካል ሊቋቋም እንደሚገባም ጠቁመዋል።

ኬሚካሎቹ ሊያደርሱ ስለሚችሉት ጉዳትና ስለሚወገዱበት ሁኔታ ዝርዝር ጥናት ማድረግ እንደሚያስፈልግም አስታውቀዋል።

ጥናቱ በአገር አቀፍ ደረጃ የሚካሄድ ሲሆን ኮሚቴው ከአዲስ አበባ ውጭ በሚገኙ ባለበጀት የመንግስት መስሪያ ቤቶችና የልማት ድርጅቶች ላይ ጥናቱን የሚቀጥል ይሆናል። ENA

READ  Ethiopia, Djibouti Seals Deal to Construct Pipeline

NO COMMENTS