ጠቅላይ ቤተ ክህነት “የፓትሪያርኩ ስም ጠፍቷል” በሚል ያቀረበውን ክስ እንዲያሻሽል ፍ/ቤቱ በየነ

0
3892
ጠቅላይ ቤተ ክህነት
Image: Patriaric

የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የቂርቆስ ምድብ ሁለተኛ ፍትሐ ብሔር ችሎት፤ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን መንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት፣ በሰንደቅ ጋዜጣ ላይ በቀረበ ጹሑፍ፤ የፓትርያርክ አቡነ ማትያስን ስም አጥፍቷል በሚል ያቀረበው ክስ፤ ከሳሽን የማይመለከተው በመሆኑ አሻሽሎ እንዲያቀርብ ፍርድ ቤቱ ብይን ሰጠ።

ፍ/ቤቱ ይህን ብይን የሰጠው፣ ጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ያቀረበውን ክስ አስመልክቶ፣ በተከሳሽ የሰንደቅ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ አቶ ፍሬው አበበ በኩል የቀረበውን መቃወሚያ እና በጠቅላይ ቤተክህነቱ በኩል የተሰጠውን መልስ መርምሮ ትናንት በሰጠው ብይን ነው።

ከሳሽ ጠቅላይ ቤተክህነት፣ ለክሱ መነሻ የሆነው፣ በዲያቆን ዳንኤል ክብረት ተጽፎ በሰንደቅ ጋዜጣ 11ኛ ዓመት ቁጥር 551 ረቡዕ መጋቢት 21 ቀን 2008 ዓ.ም፤ “ፓትርያርኩ ለኢትዮጵያ የደኅንነት ሥጋት፣ ለምዕመናን የድህነት ሥጋት” በሚል ርዕስ የታተመው ጹሑፍ፤ የፓትያርክ አቡነ ማትያስን ስም ያጠፋ ነው፤ የሚል ይዘት ያለውና ደረሰብኝ ላሉት ጉዳት የ100 ሺ ብር የሕሊና ጉዳት ካሳ የሚጠይቅ ነው።

ተከሳሽ ጋዜጠኛ ፍሬው አበበ፣ አምስት ነጥቦች ያሉት የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያውን ለፍ/ቤቱ በጹሑፍ እና በቃል ክርክር ያቀረበ ሲሆን፤ ፍ/ቤቱም፣ ጉዳዩን ግራና ቀኝ መርምሮ አንደኛውን መቃወሚያ ማለትም፣ “… ጹሑፉ ስም የሚያጠፋ ነው ቢባል እንኳን ክስ የማቅረብ መብቱ የተበደልኩ ባዩ እንጂ የሌላ አካል ሊሆን አይችልም። ስም ማጥፋት የሚፈጸመው በግለሰብ ላይ በቀጥታ በመናገር ወይም በመጻፍ ነው። በሕግ ፊት ፓትሪያርክ አቡነ ማትያስ አንድ ሰው ናቸው። በስም መጥፋት ምክንያት የደረሰባቸው የሕሊና ጉዳት ቢኖር ክስ የማቅረብ መብቱ የራሳቸው ወይም የወከሉት ሰው ነው። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን መንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት በአቡነ ማትያስ ላይ ለደረሰ የሕሊና ጉዳት ካሳ የመጠየቅ መብት የለውም።

READ  ጎንደር ያለ ሰላም ምንድን ናት? ከስናፍቅሽ አዲስ

በመሆኑም ከሳሽ ክሱ በተመሠረተበት ጉዳይ ላይ ጥቅም የለውም፤ አያገባውም…” በሚል ያቀረበውን ተቃውሞ ፍ/ቤቱ ተቀብሎታል። በዚህ መሠረት ክሱ በአጠቃላይ ከርዕሱ ጀምሮ ፓትሪያርኩን የሚመለከት በመሆኑና ጠቅላይ ጽ/ቤቱ እሳቸውን ተክቶ ክስ ሊያቀርብ እንደማይችል በመጥቀስ፣ ከክሱ ውስጥ ፓትርያርኩን የሚመለከተው ርዕሰ ጉዳይ ወጥቶ ክሱ ተሻሽሎ እንዲቀርብ ለኅዳር 16 ቀን 2009 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

በተጨማሪም ፍ/ቤቱ ጠቅላይ ቤተክህነት ባቀረበው ክስ ላይ “አመፅ ለማነሳሳት…” በሚል የጠቀሰው፤ ሆኗል ቢባል እንኳን ዐቃቤ ሕግን እንጂ ጠቅላይ ቤተክህነትን የሚመለከት ጉዳይ ባለመሆኑ ይህንንም በክስ ማሻሻያው ላይ ሰርዞ እንዲቀርብ አዟል።

በተመሳሳይ ሁኔታ በጋዜጠኛ ፍሬው አበበ ላይ በወንጀል የቀረበው ክስ፣ ኅዳር 15 ቀን 2009 ዓ.ም የመጨረሻ ውሳኔ ያገኛል ተብሎ ይጠበቃል።

(ሰንደቅ ጋዜጣ 12ኛ ዓመት ቁጥር 584 ረቡዕ ህዳር 07/2009) በጋዜጣው ሪፖርተር

NO COMMENTS