የኢትዮ-ምኅዳር ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ በአንድ ዓመት እስር እና በገንዘብ ተቀጣ

0
1518
የኢትዮ-ምኅዳር ጋዜጣ
Image: የኢትዮ-ምኅዳር ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ

የኢትዮ-ምኅዳር ጋዜጣ እና ዋና አዘጋጁ “በፓትሪያሪኩ መቀመጫ ቅዱስት ማሪያም ገዳም ምርመራ እንዲካሄድ ተጠየቀ” በሚል ርዕስ በተሰራው ዜና የስም ማጥፋት ወንጀል ተፈፅሞብኛል ስትል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተርክስቲያን በመሠረተችው ክስ ጥፋተኛ ሆነው በመገኘታቸው የገንዘብና የእስር ቅጣቱን ትናንት ማክሰኞ (ህዳር 6 ቀን 2009 ዓ.ም) የፌዴራሉ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ 6ኛ ወንጀል ችሎት አስተላለፈ።

በመንበረ ፓትሪያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም አስተዳደር ፅህፈት ቤት በኩል በኢትዮ-ምኅዳር ጋዜጣና በዋና አዘጋጁ ጌታቸው ወርቁ ላይ የተመሰረተው የክስ ዝርዝር እንደሚያስረዳው፤ ተከሳሾቹ በሌላ ሰው መልካም ስም ላይ ከባድ ጉዳት ለማድረስ አስበው ኢትዮ-ምኅዳር በተባለው ጋዜጣ ቅፅ 03 ቁጥር 107፤ በግንቦት 22 ቀን 2007 ዓ.ም በታተመው ዜና፣ የግል ተበዳይ የሆነችውን የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ የመንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅድስት ማሪያም ገዳም ስም አጥፍቷል በሚል ያትታል።

የወንጀል ዝርዝሩ እንደሚያስረዳው፤ 1ኛ በገዳሙ የሚገኘው ታሪካዊ እንጦንስ ጽላት በአርተፊሻል ተቀይሯል፤ ጥንታዊያን የብራና መፃህፍት እና የወርቅ ጽንሐት ወጥተዋል፤ የስዕለት እና የስጦታ ወርቅና የብር ጌጣጌጦች በየመሸታ ቤቱ እየተሸጡ ነው። ይህም ድርጊት የሚፈፀመው በአሳቻ ጊዜ በማውጣት በዕቃ ማጣሪያና ሽያጭ ሰበብ፤ እንዲሁም ሰነዶችን በመደለዝና በማጥፋት እንደሆነ፤ ከበጎ አድራጊዎች ለገዳሟ በስለት የተበረከቱ ላፕቶፕና ፕሮጀክተር በግለሰቦች ተሸጧል የሚለው ይገኝበታል።

በሁለተኛ ደረጃ በክሱ በዝርዝር የቀረበው ጉዳይ ጋዜጣው በዜና የሰራው የገዳሟ የንብረት ቁጥጥር ክፍል ኃላፊዎች የውጪ ኦዲት እንዲካሄድ በፓትርያርኩ የተሰጠውን መመሪያ የተለያዩ ስልቶችን በመከተል ተግባራዊ እንዳይሆን እያደረጉ ነው፤ “የመልከዓ ብስራት አባ ገብረስላሴ ስም ከቄስ ገበዝ አባ ሳሙኤል ቀለሙና ሌላ ካህን ጨምሮ ለምንኩስና ስርዓት በማይስማማ ተግባር አልባሌ ቦታ መገኘት፤ እንዲሁም መነኮሳቱም ልናጠምቅ ነው በሚልና በምግብ አብሳይነት ሰበብ በገዳሙ ቅፅር በሚገኘው ማረፊያ ቤታቸው የሚገቡ ሴቶች እስከመንፈቀ ሌሊት እየቆዩ በቤተክርስትያን በሚያስነቅፍ ነገር በመፈፀም፤ በየግሮሰሪው አምባጓሮ እየፈጠሩ ከአስተናጋጆች ጋር ለድብድብ በመጋበዝ በስካር ወደገዳሙ በመግባት ቅፅሩን የአሉባልታና የአድማ መናኸሪያ በማድረግ አስነቅፈዋል ሲል ያትታል።

READ  በአዲስ አበባ አብነት አካባቢ የድንጋይና አፈር ክምር ተደርምሶ የ4 ሰዎች ህይወት አለፈ

በሶስተኛ ደረጃ “የፓትሪያርኩ ልዩ ፀሐፊ ንቡረ እድ ኤልያስ ለችግሩ መባባስ ተጠያቂ ተደርገዋል በማለትና ሌሎች በጋዜጣው ላይ የተጠቀሱ የስም ማጥፋት ይዘት ያላቸው ፅሁፎች ማጣራት ሳይደረግባቸው ሰፍረዋል ሲል በክሱ ይዘረዝራል።

ቤተክርስትያኗ ለመሠረተችው ክስ ያስረዱልኛል ያለቻቸውን የሰውና የሰነድ፤ ማስረጃዎች ለችሎቱ ያቀረበች ሲሆን፤ የጋዜጣዋ ዋና አዘጋጅ ጌታቸው ወርቁ ለቀረበበት ክስም በጠበቃ በኃይሉ ተስፋዬ በኩል፤ የመከላከያ ምስክሮችን ከማቅረቡም ባሻገር በአስተዳደራዊ፣ በፋይናንስና በስነ-ምግባር ዙሪያ ለክሱ ምላሽ ይሆናሉ ያላቸውን ሃሳቦች የፅሁፍ ማስረጃ ጭምር ለችሎቱ አቅርበዋል።

የፌዴራሉ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት 6ኛ ወንጀል ችሎትም፤ የግራ ቀኙን ክርክር ሲያደምጥ ቆይቶ ውሳኔውን አስተላልፏል። በዚህም የኢትዮ-ምኀዳር ጋዜጣን እና የጋዜጣዋን ዋና አዘጋጅ ጥፋተኛ ናቸው ሲል ባሳለፍነው ጥቅምት 24 ቀን 2009 ዓ.ም የወሰነበት ሲሆን፤ በትናንት ውሎውም የህግ ሰውነት ባለው በኢትዮ-ምኅዳር /ሁለንታ ህትመትና ማስታወቂያ ኃ/የተ/የግ/ማህበር ላይ የ10 ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ የወሰነ ሲሆን፤ የፍርዱን ግልባጭ ለመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት እንዲላክ ችሎቱ ወስኗል።

የጋዜጣው ሕትመት የሚቀጥል ከሆነ ቅጣቱን ተከታትሎ እንዲያስፈፅምም ትዕዛዝ ሰጥቷል። እንዲሁም በዋና አዘጋጁ ላይ የአንድ ዓመት እስር እና የ1ሺህ 500 ብር የገንዘብ መቀጫ ወስኖባቸዋል።

ከቅጣት ውሳኔው በኋላ ጋዜጠኛ ጌታቸው ወርቁ በችሎቱ ለነበረው ሰው ሁሉ እንዲሰማ አድርጎ “እኔ የታሰርኩት ለእውነት ነው፤ የጋዜጣችንም መርህ ያንን ያመለክታል” ሲል ተደምጧል። ጠበቃ በኃይሉ በበኩላቸው የችሎቱን የቅጣት ውሳኔ እንዳልጠበቁት ገልጸው፤ በቀጣይ ቀናትም ይግባኝ እንጠይቃለን ብለዋል። (ሰንደቅ ጋዜጣ 12ኛ ዓመት ቁጥር 584 ረቡዕ ህዳር 07/2009) | በጋዜጣው ሪፖርተር

NO COMMENTS