ያልቀዘቀዘው የቱሪዝም ገቢ የሞቀ ውሸት ወይስ የተለየ አጋጣሚ

0
1740
ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር
Image: Land of Origins

ከስናፍቅሽ አዲስ

ሰሞኑን ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር መግለጫ ሰጠ፡፡ መግለጫው ከጠበቅንውም ከገመትንውም ውጪ ነው፡፡ በእርግጥ ማመን አቃተን አልን እንጂ ነገሩስ የሚያስደስት ነበር፡፡ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ሀገሪቱ በብጥብጥ የከረመችበት ሩብ በጀት አመት ስኬታማ ነበር ሲል ግን እንዴት ማለት ሀጢአት አይመስለኝም፡፡

ከሀምሌ 1-መስከረም 30 ባለው ጊዜ ስኬታማ የቱሪዝም ስራ ተሰርቷል የሚለው ሪፖርት ራሱን ከአምናው ጋር አነጻጽሮ ከሰላሙ ጊዜም የተሻለ ነበር ማለቱ አወዛጋቢ ያልሆነበት የለም፡፡ “ቁጥርን ማመን ቀብሮ ነው” የሚሉ ሰዎችን ጭምር “ይሄዋ ድሮስ ምን ብለን ነበር” አሰኝቷል፡፡

እነኚህ የክረምቱ ሁለት ወራትና እንደ ኢሬቻው ያሉ መጥፎ አጋጣሚዎችን ያስተናገደው መስከረም በሀገራችን ቱሪዝም ላይ መጥፎ ጥላ ማጥላቱ በወቅቱ ሲነገር ነበር፡፡ ፋሲል ጊቢ ጭር አለ፣ ሐመር ድርቅ መታው፣ ሐረር ተጓዥ ጠፋ፣ ባህር ዳር ሆቴል ጦሙን አደረ ሲባል ሰንብቷል፡፡ በሰላም የበራው የላሊበላ ደመራ ያለ ጎብኚ ያለፈ ነው እየተባለ ሰንብቶ ጥቅምት ሲሸኝ ወቅቱ ጥሩ ነበር ቅናሹም ቢሆን አንድ በመቶ ያልሆነ ነው የሚል ዜና መስማት አነጋጋሪ ነው፡፡

አንድ በመቶ ማለት በማናቸውም ወቅት ሊከሰት የሚችል የቱሪስት መቀነስ ስሌት ነው፡፡ በዚህ ከባድ እና ፈተና ነበር በተባለ ወቅት፤ ጎንደር በሳምንት ሁለት ቀን ስራ ማቆም አድማ ስትጠራ በሰነበተችበት፤ አንዳንዴም መንገዱ ተዘጋ እየተባለ የሀገር ውስጥ ጎብኚ እንኳን መንቀሳቀስ ባልቻለበት ከ233 ሺ በላይ የውጪ ጎብኚ ኢትዮጵያን ጎብኝቶ 872 471 808 የአሜሪካ ዶላር ተገኘ መባሉ አነጋጋሪ ሆኗል፡፡

አንዳንዶች ይህ ቁጥር አዲስ አበባን ረግጦ፣ አፍሪካ ህብረት ጉዳይ ሊያስጨርስ የመጣ አሊያም የውጪ መሪዎችን ተከትሎ ጎራ ያለ እንግዳን በጅምላ በማስላት ደጋግሞ የሚመጣውን መደበኛ የውጪ ዜጋ በመቁጠር የመጣ ስሌት ነው በሚል መግለጫውን ተጠራጥረውታል፡፡

READ  የኢትዮጵያ መንግስት ለ140 የኤርትራ ስደተኛ ተማሪዎች የከፍተኛ ትምህርት ዕድል ሰጠ

በዚህ ሁሉ ሁኔታ ውስጥ ግን አሁንም የሀገሪቱ የውጪ ጎብኚዎች ቁጥር መቀነስ በሴክተሩ የተሰማራውን ባለድርሻ አሳስቦታል፡፡ ለገና በላሊበላ እና ለጥምቀት በጎንደር የነበሩ ከፍተኛ የመኝታ ዋጋ ጭማሪዎች እና የማረፊያ ክፍል እጥረቶች እንደወትሮው ከአሁኑ ጀምሮ ምልክት አላሳዩም፡፡

በአክሱምም ቢሆን የሪዘርቬሽኑ እንቅስቃሴ ደካማ መሆኑ ነው የሚገለጸው፤ አስጎብኚዎች መጠንኛ ለውጥ አለው የሚሉት ያሳለፍናቸው ሁለት ሳምንታት የሰሜን እና ደቡብ የጉብኝት ጉዞዎች ቀጣይነት ይኖራቸዋል ወይስ መልሰው ይደበዝዛሉ በሚል ስጋት ተውጠዋል፡፡ በባንክ ብድር ሴክተሩን ተማምነን የገነባነው ሆቴል ለኪሳራ ዳረገን የሚሉ ባለሀብቶችን ማድመጥም ብርቅ አይደለም፡፡

አሁን በወትሮው የኢትዮጵያ የቱሪዝም ልማት ሞቅ ያለ ገበያ ያለበት ጊዜ ነበር፡፡ ነበር ብለን የምናልፈውን ይህንን ወቅት አስጎብኚ ድርጅቶች ቢያማሩትም ከወትሮው በተለየ ገበያው በጣም አለመቀዝቀዙን ነው የባህል እና ቱሪዝም ሚኒስቴር መስሪያ ቤት የሚገልጸው፡፡ ኢትዮጵያን እንደ አስጎብኚዎቹ ሳይሆን እንደ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ያክርማት ከማለት ውጪ ምን ይባላል፡፡

DireTube.com

NO COMMENTS