በካናዳ የኢትዮጵያ አምባሳደር በጉዲፈቻ የወሰዱትን ልጅ ጥለው መሔዳቸው አወዛገበ

0
12366
በካናዳ የኢትዮጵያ አምባሳደር
Image: በካናዳ የኢትዮጵያ አምባሳደር
  • የሴቶችና ሕፃናት ጉዳይ ሚኒስቴር የአምባሳደሯ ተግባር ሕገወጥ ነው ብሏል

በፋኑኤል ክንፉ

በካናዳ የኢትዮጵያ አምባሳደር ወ/ሮ ብርቱካን አያኖ ዳዲ በ07/12/2005 ዓ.ም. በሱሉልታ ወረዳ ፍርድ ቤት ከባለቤታቸው ከአቶ ዮሃሐስ አድማሱ ጋር በጋራ ቀርበው የአብ ፍቅሩ የተባለ እድሜው 6 አመት የሆነውን በ07/09/2005 ዓ.ም. በተደረገው የጉዲፈቻ ውል ከአቶ ፍቅሩ ስለሺ እና ከወ/ሮ መሳዬ ማስረሻ የተረከቡትን ሕፃን ጥለው ወደ ካናዳ መሔዳቸው ታውቋል።

ሰንደቅ ጋዜጣ በሴቶችና ሕፃናት ሚኒስትቴር ያነጋገራቸው የሕግ ጉዳዮ ዳሬክቶሬት ዳሬክተር አቶ ደረጀ ተግይበሉ መረጃው እንደረሳቸው አምነው፤ ሕፃኑን ወደ ቤተሰቡ እንዲመለስ ለውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ደብዳቤ መፃፉን ገልጸዋል።

አቶ ደረጀ ተግይበሉ ስለደብዳቤው ፍሬ ነገር በአጭሩ እንዳስቀመጡት፣ “በ11/02 2009 ደብዳቤ ጽፈናል። በካናዳ የኢትዮጵያ አምባሳደር የሆኑት ወ/ሮ ብርቱካን አያኖ እና ባለቤታቸው አቶ ዮሃንስ አድማሱ ሕፃን የአብ ፍቅሩን በጉዲፈቻ ለማሳደግ በሱሉልታ ፍርድ ቤት አመልክተው ፍርድ ቤቱ ጉዲፈቻውን ያጸደቀ መሆኑን ሕፃኑንም ለማሳደግ ከወሰዱት በኋላ የሀገራችን የጉዲፈቻ ሕግ ከሚፈቅደው በተቃራኒ ሕፃኑን ለቀድሞ ቤተሰብ መልሰው መሔዳቸው ለሚኒስትር መስሪያቤቱ መረጃ ደርሷል።

ይህንን በተመለከተም በሕፃኑ እና ጉዲፈቻ ባደረጉት መካከል ቋሚ የሆነ የልጅና የወላጅ ግንኙነት የሚመሰረት በመሆኑ ውጤቱም የተፈጥሮ ልጅ ካለው መብት ጋር እኩል መሆኑን ሕጉ ይደነግጋል።

ስለሆነም አምባሳደሯ ሕፃኑን ለቤተሰቡ መልሰው መሄዳቸው የህፃኑን መሰረታዊ ጥቅሞች ከመጉዳቱም በላይ፣ ሌሎች ከሀገራችን ሕፃናትን በጉዲፈቻ የወሰዱ እንዲህ አይነቱ መረጃ ሲደርሳቸው ተመሳሳይ ድርጊት እንዲፈጽሙ የሚያበረታታ ከመሆኑ በላይ የሀገር ገጽታ የሚጎዳ ተግባር ነው። አምባሳደሯ ሕፃኑን መልሰው የሚወስዱበትን ሁኔታ ሚኒስትር መስሪያ ቤቱ የሚያመቻችበትን ሁኔታ እንጠይቃለን የሚል ፍሬ ነገር ያለው ደብዳቤ ነው የፃፍነው” ብለዋል።

READ  በጎንደር ከተማ አመፅና ሁከት አስነስታለች የተባለች ግለሰብ የሽብር ወንጀል ክስ ተመሠረተባት

የሰንደቅ ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል ለተከበሩ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ በአድራሻቸው በኢሜል ለቀረበባቸው ክስ ምላሽ እንዲሰጡ ጥያቄ ያቀረበላቸው ቢሆንም አምባሳደሯ ምላሽ ለመስጠት ፈቃደኛ አይደሉም።

የሕፃን የአብ ፍቅሩ ወላጅ አባትን አነጋግረናቸው የሰጡን ምላሽ “ምንም የምለው ነገር የለም። ሁሉንም ነገር ፈጣሪ እያየው ነው” ብለዋል።

በአሁኑ ሰዓት ሕፃን የአብ ፍቅሩ ካናዳ የጀመረውን ትምህርት አቋርጦ ይገኛል። ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም፡:

NO COMMENTS