አትሌት አልማዝ አያና የዓመቱ ምርጥ አትሌት ለመባል ከመጨረሻዎቹ ሶስት አትሌቶች አንዷ ሆነች

0
7549
አትሌት አልማዝ
Image: አትሌት አልማዝ IAAF Credit

አትሌት አልማዝ አያና የዓመቱ ምርጥ አትሌት ለመባል ከመጨረሻዎቹ ሶስት አትሌቶች አንዷ ሆነች

አትሌት አልማዝ አያና በ2016 የዓለም ምርጥ ሴት አትሌት ለመባል ከመጨረሻዎቹ ሶስት አትሌች መካከል አንዷ ሆነች።

የዓለም አቀፉ አትሌቲክስ ፌደሬሽኖች ማህበር የ2016 የዓመቱ ምርጥ ስድስት አትሌቶችን ዛሬ ይፋ አድርጓል።

ማህበሩ ምርጥ ስድስት አትሌቶችን ይፋ ያደረገው የአይዳብል ኤኤፍ ቤተሰቦችና የአትሌቲክስ ደጋፊዎች በማህበራዊ ሚዲያ በሰጡት ድምጽ ነው።

በሪዮ ኦሊምፒክ በ10 ሺህ ሜትር ክብረ ወሰን በመስበር ለኢትዮጵያ የወርቅ ሜዳሊያ ያስገኘችው አትሌት አልማዝ አያና የዓመቱ ምርጥ አትሌት ለመባል ከጫፍ ደርሳለች።

በአጭር ርቀት የኦሊምፒክ አሸናፊ ኢሊን ቶምሶን ከጃማይካ እና የመዶሻ ወርዋሪዋ አኒታ ሎዳሪዝኪ ከፖላንድ በሴቶች ምድብ ምርጥ ሶስት ውስጥ የተካተቱ ስፖርተኞች ናቸው።

በወንዶች ምድብ ጃማይካዊው የአጭር ርቀት ንጉስ ዩሴን ቦልት፤ ደቡብ አፍሪካዊው በ400 ሜትር የዓለም ክብረ ወሰን ባለቤትና የወቅቱ የኦሊምፒክ ሻምፒዮን ዋይዳ ቫን ኒከርክ እንዲሁም እንግሊዛዊው የ5 ሺህ እና የ10 ሺህ ሜትር የኦሊምፒክ አሸናፊ ሞ ፋራህ በወንዶች ምድብ ተመርጠዋል።

ከስድስቱ አትሌቶች መካከል የዓመቱ ምርጥ አትሌት የሚሆኑ አንድ ወንድና አንድ ሴት አትሌት በታህሳስ መጀመሪያ በፈረንሳይ ሞናኮ ከተማ ይፋ እንደሚደረግ አይ ዳብል ኤፍ አስነብቧል።

በሴቶች ምድብ አትሌት ገንዘቤ ዲባባ ከኢትዮጵያ፣በወንዶች ደግሞ አሜሪካዊው የዲክታሎን ተወዳዳሪ አሽቶን ኢቴን የ2015 የዓመቱ የዓለም ምርጥ አትሌቶች ተብለው መመረጣቸው ይታወሳል። ENA

READ  በሁከት ተጠርጥረው የተያዙ ተጠርጣሪዎች የሚገኙባቸው ማዕከላት ይፋ ሆኑ

NO COMMENTS