ዶናልድ ትራምፕ ቀጣዩ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት በመሆን ተመረጡ

0
15547
ዶናልድ ትራምፕ
Image: ዶናልድ ትራምፕ

ዶናልድ ትራምፕ ትናንት በተካሄደ የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ አሸናፊ ሆኑ። ለ19 ተከታታይ ወራት ሂላሪ ክሊንተን ዴሞክራቶችን በመወከል እና ዶናልድ ትራምፕ ደግሞ ሪፐብሊካኖችን በመወከል የዚያች ልዕለሀያል አገር 45ኛ ፕሬዚዳንት ሆነው ለመመረጥ ሲቀሰቅሱ ቆይተዋል።

ጊዜው ደርሶም ትናንት በተሰጠ ድምፅ ዶናልድ ትራምፕ ቀጣዩ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ሆነው ተመርጠዋል።

በአሜሪካ የምርጫ ህግ በመላው አገሪቱ በሚገኙ ግዛቶች 538 የምርጫ ድምፆች /electoral college/ ያሉ ሲሆን፥ ከእነዚህ ውስጥ አንድ የፕሬዚዳንታዊ ምርጫው እጩ ቢያንስ 270 ድምፆችን ማግኘት ይጠበቅበታል።

ዶናልድ ትራምፕ በምርጫው ከ270 በላይ ድምፅ በማግኘት አሸናፊነታቸውን አረጋግጠዋል። እስካሁን በተደረገ ቆጠራም 288 ያህል የምርጫ ድምፆችን አግኝተዋል። ተቀናቃኛቸው የነበሩት ሂላሪ ክሊንተን ደግሞ 218 የምርጫ ድምፆችን ነው ያገኙት።

ትራምፕ በዋና ዋናዎቹ ግዛቶች ፍሎሪዳ፣ ኦሃዩ፣ ፒንሲልቫኒያ እና ሰሜን ካሮሊና አሸንፈዋል። ክሊንተን በበኩላቸው ከፍተኛ ዋጋ ካላቸው ግዛቶች በቨርጂኒያ ብቻ ነው ማሸነፍ የቻሉት።

ተመራጩ ፕሬዚዳንት ይህን ብለዋል

“ለሁሉም አሜሪካዊ ፕሬዚዳንት እሆናለሁ” ያሉት ተመራጩ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ፥ ሂላሪ ክሊንተን የእንኳን ደስ ያለህ መልዕክት እንዳስተላለፉላቸው ተናግረዋል።

በኒውዮርክ ለተሰባሰቡ ደጋፊዎቻቸው ባሰሙት ንግግር፥ “አሜሪካውያን አንድነታችንን የምናጠናክርበት ጊዜ አሁን ነው” ብለዋል።

ዴሞክራቶች ሂላሪ ክሊንተን ትራምፕን በቀላሉ ያሸንፋሉ የሚል ግምት የነበራቸው ቢሆንም፥ የሪፐብሊካኑ እጩ በተለይም ከነጭ አሜሪካውያን እና ከገጠሩ ነዋሪ የተሻለ ድምፅ ማግኘት ችለዋል።

ሂላሪ ክሊንተን ከአፍሪካ አሜሪካውያን፣ ከኤዥያ አሜሪካውያን እና ሂስፓኒክ ከሚባሉት የህብረተሰብ ክፍሎች ድጋፍ ቢያገኙም፥ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ሲመረጡ ከእነዚህ የህብረተሰብ ክፍሎች ካገኙት ድምፅ ያነሰ ነው ያገኙት።

ዶናልድ ትራምፕ
Image: ዶናልድ ትራምፕ VOTE MAP

ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሪፐብሊካኖቹ 235 መቀመጫዎችን ያገኙ ሲሆን፥ ዲሞክራት ፓርቲ ደግሞ 182 አግኝተዋል።

READ  Asgedom Leads Soldiers Home from Sudan

ከ100 የህግ መወሰኛ ምክር ቤት መቀመጫዎች ሪፐብሊካን ፓርቲ 51 ሲያገኝ፤ ዴሞክራት 45 መቀመጫዎችን ማግኘት ችሏል።

ዶናልድ ትራምፕ ከቀናት በኋላ የመንግስታቸውን ካቢኒ ማዋቀር እና ለፖሊሲዎቻቸው የበለጠ ቅርፅ የመስጠት ስራን ያከናውናሉ ተብሎ ይጠበቃል።

በእነዚህ ቀናትም ተሰናባቹ እና በአሜሪካ ታሪክ የመጀመሪያው ጥቁር የአገሪቱ ፕሬዚዳንት በመሆን ታሪክ ሰርተው የሚያልፉት ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ በፕሬዚዳንትንት ዘመናቸው ላከናወኗቸው እና ስማቸውን ለሚያቆዩ ስራዎቻቸው መልክ እየሰጡ ከዋይት ሀውስ የእርሳቸው የሆኑትን እቃዎች መሸከፍ ይጀምራሉ።

በሚቀጥለው ጥር ወር ላይም ዶናልድ ትራምፕ በፕሬዚዳንትነት ቃለ መሃላ በመፈፀም በይፋ ስራቸውን ይጀምራሉ ተብሎም ነው የሚጠበቀው። (ኤፍ.ቢ.ሲ)

ለዶናልድ ትራምፕ እንኳን ደስ ያልዎት እንላለን። ለኢትዮጵያ ምን ይፈይዱ ይሆን?

NO COMMENTS